Connect with us

Africa

የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት መንገድ የጠረገ ነው

Published

on

የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት መንገድ የጠረገ ነው

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከ32 ዓመታት አገልግሎት በኋላ በአፍሪካ ኅብረት ሲቀየር አፍሪካ አንድ ታሪካዊ ሽግግር የፈፀመችበት ወቅት ተደርጎ ተውስዷል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ሽግግር ደግሞ የኢትዮጵያ አስተዋፅኦ የጎላ ነበር፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም የመጀመሪያው መገለጫ በራስ ተፈሪያን እንቅስቃሴ በቦብ ማርሌ የሬጌ ሙዚቃ ስልተ ምት ተንፀባረቀ፡፡ የዓድዋ ጦርነት ድል የኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ የፓን አፍሪካኒዝም የመጀመሪያ ደረጃ መገለጫ ተደርጎም ተወሰደ፡፡

የቅኝ ግዛት አስከፊነት፣ የእጅ አዙር አገዛዝ ተፅዕኖ እና የምጣኔ ሀብት ጥገኝነት በመጀመሪያው የፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ የፍልስፍና መርሆ ሆኑ፡፡

ከ1960ዎቹ እስከ 1970ዎቹ አጋማሽ ድረስ ከፕሬዝዳንት ክዋሜ ንክሩማህ እስከ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ከጁልየስ ኔሬሬ እስከ ጆሞ ኬኒያታ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመመሥረት እስከ ቃል ኪዳን ቻርተር መፈራረም ድረስ አፍሪካውያን የማይረሱት የመሪነት ሚናን ተጫወቱ፡፡

የመሪዎቹ ጥረት ከንቱ አልቀረም፡፡ ጊዜው ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ከሌሊቱ 7፡30 ላይ ነበር፤ 32ቱ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ታሪካዊ ስምምነት ላይ ፊርማቸውን በማስቀመጥ የአፍሪካን ቻርተር በመፍጠራቸው፤ አፍሪካ ወደ አንድ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ተሸጋገረች፡፡ ይህ ታሪካዊ እና አህጉራዊ አንድነት እንዲሳካ በካዛብላንካ እና በሞኖሮቪያ ቡድኖች መካከል የነበረውን የሐሳብ ልዩነትና ውጥረት በማስታረቅ ኢትዮጵያ ጉልህ ሚና ነበራት፤ በዚህም ለዘመናት ትታወሳለች፡፡

ከወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር ከተማ ይፍሩ ኢትዮጵያን በመወከል በአፍሪካ ከተሞች የሠሯቸውን የዲፕሎማሲ ሥራዎች ታሪክ ሲዘክራቸው ይኖራል፡፡

አፍሪካውያን አህጉራዊ ትስስር ፈጥረው ወደ አንድነት እና ኅብረት ለመምጣት ያደረጉት ጉዞ አልጋ ባልጋ አልነበረም፡፡ እርስ በእርስ ግጭቶች፣ የመንግሥታት ሽኩቻ፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና የጎሳ ግጭቶች አህጉሪቷ ወደ አንድ እንዳትመጣ ሳንካዎች ነበሩ፡፡

በአልጀሪያና በሞሮኮ፣ በማዕከላዊ አፍሪካና በዛየር፣ በኢትዮጵያና በሱማሊያ፣ በጊኒና በኮት ዲቯር፣ በጋቦንና በኢኳቶሪያል ጊኒ፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ፣ በአንጎላና በሞዛንቢክ፣ በሩዋንዳና በቡርንዲ እንዲሁም በሰሃራዊ ዓረብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና በሞሮኮ መካከል የተፈጠሩትን ቁርሾዎች በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመፍታት፤ በተጨማሪም በልማት መስክ አፍሪካን ግንባር ቀደም ለማድረግ ራዕያቸውን በአዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት (ኔፓድ) እስከ መመሥረት በየዘመኑ የተነሱ ኢትዮጵያውያን መሪዎች አፍሪካን አንድ ለማድረግ ቀን ከሌት ሠርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ሥርዓትና የመንግሥት የስልጣን ዘመን ለአፍሪካ ሕዝቦች አንድነትና ነፃነት በፅናት ታግላለች፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም ከተፈረመ በኋላ ኢትዮጵያ የድርጅቱ ዋና መቀመጫ ሆና የተመረጠችው በዳካር በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጉባኤ በነሐሴ ወር 1955 ዓ.ም ነበር፡፡

በተመሳሳይ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከተመሠረተ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላ ሐምሌ 2 ቀን 1994 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ደርባን በ38ኛው እና የመጨረሻው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ድርጅቱ ወደ አፍሪካ ኅብረት ተሸጋገረ፡፡ ኅብረቱ የመጀመሪያ ጉባኤውንም በዚያው በደርባን ደቡብ አፍሪካ አካሄደ፡፡ በቶጎ ሎሜ ደግሞ የኅብረቱ መቀመጫ በድጋሜ አዲስ አበባ ሆና ተመረጠች፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ዓላማ በአፍሪካ ሀገሮች ሕዝቦች መካከል ያለውን የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሀብታዊና የማኅበራዊ ኅብረትና አንድነትን ማጠናከር ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የራሱ አርማ ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር አለው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ማቋቋሚያ ሰነድ በ33 አንቀፆች የተከፋፈለ ሲሆን የኅብረቱ ዋና አካላትም 12 ናቸው፡፡

ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራቾች ውስጥ አንዱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተር ሲፈረም ከግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 1956 ዓ.ም እና በድጋሜ ከሕዳር 1958 ዓ.ም እስከ መስከረም 1959 ዓ.ም ድረስ ድርጅቱን በሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡

ኅብረቱ ምንም እንኳን ለመሥራቹ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የሰጠው ዕውቅና ቢዘገይም በ32ኛው የድርጅቱ ስብሰባ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ግቢ ውስጥ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያቆመላቸውን ሀውልት በይፋ ተመርቋል፡፡

(ምንጭ፡- የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት -በታዘብ አራጋው)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close