Connect with us

Entertainment

የሚስቴን ባህሪ የምትችል የቤት-ሠራተኛ መፈለጌን ትቼ፣ …

Published

on

የሚስቴን ባህሪ የምትችል የቤት-ሠራተኛ መፈለጌን ትቼ፣ የሠራተኛዬን አመል የምትቋቋም ሚስት ልፈልግ ይሆን??

የሚስቴን ባህሪ የምትችል የቤት-ሠራተኛ መፈለጌን ትቼ፣ የሠራተኛዬን አመል የምትቋቋም ሚስት ልፈልግ ይሆን??
(አሳዬ ደርቤ)

እሜቴ ከወለደችበት ጊዜ አንስቶ አራት የቤት ሰራተኛዎችን አባርራ በባለፈው አምስተኛዋን ቀጥራለች፡፡ ከእነዚህ መሃከል ሁለቱ በራሳቸው ጥያቄ መሰረት መልቀቂያ አስገብተው የተሰናበቱ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ባለቤቴ ‹‹በቃችሁኝ›› ብላ የሸኘቻቸው ናቸው፡፡

ይሄም ሆኖ ግን እማወራዬን ቀና ብሎ የመናገር መብቱ የለኝም፡፡ የእኔ የሥራ ድርሻ ሰራተኛ አፈላልጌ ማምጣት ሲሆን የመቆጣጠሩና የማሰናበቱ ድርሻ የእሷ ነው፡፡

አሳዛኙ ነገር ታዲያ ከቤታችን የሚለቁት ሰራተኞች ገና ከብሎኩ ወጣ ከማለታቸው አንዱ ደላላ እጃቸውን ለቀም አድርጎ በተሻለ ደሞዝ ሲያስቀጥራቸው፣ እኔ ግን ሌላ ሰራተኛ ለማግኘት ረዥም ጊዜ የሚፈጅብኝ መሆኑ ነው፡፡ ደግሞ እኮ እንዲህ ተንከራትቼ የማመጣቸው ሰራተኞች ከሚስቴ ጋር የሚስማሙና ‹‹ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ›› የማይባሉ ቢሆኑ ሸጋ ነበር፡፡

አንዳንድ ጊዜ እንደውም በፍለጋዬ መሃከል ቆም እልና ‹‹በባለቤቴ መስፈርት መሰረት ጥሩ ሰራተኛ ከማግኘት ይልቅ ሰራተኞቹ የሚፈልጓትን አይነት ሚስት ማግባቱ ይሻል ይሆን?›› የሚል ጥያቄ አነሳለሁ፡፡

ይሄንንም ሳብራራው እኛ ቤት የሚቀጠሩ ሰራተኞች ከሙያቸው ባለፈ ብዙ ነገሮችን ማሟላት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ያህል በባህሪያቸው እሷን ቀና ብለው የማያዩ እና በመልካቸው እኔ ቀና ብዬ የማላያቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡ ሲቀጥል ደግሞ ህጻን ልጃችንን የሚንከባከቡ፣ ጓዳችንን የማይሰልቡ፣ ከዚህ በፊት ሰው ቤት ተቀጥረው የማያውቁ፣ ያልተፈቀደላቸውን ነገር የማይሰርቁ፣ ንጽህናቸውን የሚጠብቁና የእሜቴን ባህሪ የሚቋቋሙ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡

ሰራተኞቹ ደግሞ ወደ ቤታችን ከመምጣታቸው በፊት ከደሞዛቸው ቀጥሎ አጥብቀው የሚጠይቁት ነገር የቤቴንና የትዳሬን ሁኔታ የሚያጣራ ነው፡፡ ወደ ቤቴ የምወስዳቸው ለሰራተኝነት ሳይሆን ለሚስትነት ይመስል ‹‹ቤትህ ስንት ክፍል ነው? ቴሌቪዥንህ ምን አይነት ነው? የኑሮ ደረጃህ ምን ይመስላል? ሐይማኖትህስ ምንድን ነው? ባለትዳር ነህ ወይስ ወንደላጤ?›› በማለት ይጠይቁኛል፡፡

እናም ባለቤቴን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅኋት እለት የዋሸሁትን ውሸት በእጥፍ በማሳደግ የምኖረውን ሳይሆን የምመኘውን ሕይወት እንዲህ በማለት እተረተርላቸዋለሁ፡፡

‹‹ሚስቴ ሰው በልቶ የሚጠግብ የማይመስላት ጨዋ ሴት ስትሆን ትዳራችን ‹‹የአብርሐምና የሳራ›› የሚባል ነው፡፡ ቤታችን ደግሞ ፈረስ ባያስጋልብ እንኳን ለእኛ የሚጠብ አይደለም!›› እያልኩኝ የቴሌቪዥኔን መጠን ከሳሎኔ ጋር እኩል አድርጌ በመናገር አግባብቼ እወስዳቸዋለሁ፡፡ ሆኖም ግን ቤቴ ደርሰው የነገርኳቸውን እና የሚታያቸውን ነገር ሲያወዳድሩ ከሰራተኛው ከወለደው አብርሐም ውጭ ለመቀጠር የሚያነሳሳ ተስፋ አጥተው ሲቸገሩ አያቸዋለሁ፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላም እንደ አመጣጣቸው ይመለሳሉ፡፡

ለምሳሌ ያህል ለመጀመሪያ ጊዜ የቀጠርናት ሰራተኛ ከመልኳ ፍንጋነት ጋር የእኛ ማባበል ተጨምሮበት ለአርባ ቀን ያህል መቆየት ችላ ነበር፡፡ የሆነ ሌሊት ላይ ታዲያ እኔና ሚስቴ በሕይወታችን ያጣነውን እርካታ፣ ከገላችን ላይ ለመሸመት እየተጣጣርን ሳለ… ሰራተኛዋ የመኝታ ቤታችንን በር አንኳኩታ ‹‹እየረበሻችሁኝ ስለሆነ ድምጻችሁን ቀንሱልኝ›› የሚል ቅሬታ አቀረበች፡፡ በዚህን ጊዜም ባለቤቴ ‹‹በገዛ ቤቴ’ማ ታፍኜ አልሞትም›› ብላ ስትመልስላት፣ እኔ ደግሞ ‹‹ለአርባ ቀን ያህል ተራርቀን ስለከረምን እንጂ ከዚህ በኋላ ትንፍሻችን ቀርቶ ኮቴያችን አይሰማሽም›› በማለት ነገሩን ለማብረድና ከተሳፈርኩበት መንኮራኩር ላይ ለመውረድ ስሞክር፣ በእሜቴ በኩል ታላቅ ተቃውሞ ተነሳብኝ፡፡ ስለዚህም የሰራተኛችን ቅሬታ ትቼ የሚስቴን እርካታ ለማስቀጠል ተገደድኩኝ፡፡

በማግስቱ ታዲያ ከመኝታ-ቤታችን ስንወጣ ሰራተኛችንን ያገኘናት ፌስታሏን ቆጣጥራ ነበር፡፡ እናም ‹ጃንደረባ› ባለመሆኔ እየተቆጨሁ ‹‹ሥራ በዝቶብሽ ነው ወይስ ደሞዝ አንሶሽ?›› በማለት ጠየኳት፡፡

አንገቷን አጠፍ አድርጋ ‹‹ሥራችሁ ሳይሆን እርካታችሁ በዝቶብኝ ነው›› አለችኝ፡፡

‹‹ታዲያ ገዳም ካልገባሽ በቀር አንቺ የምትፈልጊው አይነት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ ይገኛል ብለሽ ነው?›› ባልኳት ጊዜም ‹‹ወንደላጤ ቤት እቀጠራለሁ›› ብላኝ ደሞዟን ተቀብላ ወጣች፡፡

ከስንት ልፋት በኋላ ደግሞ ወደ ቤታችን የገባችው ሰራተኛ እሜቴ ባደረገችው የኦዲት ሪፖርት መሰረት የተሰናበተች ስትሆን፣ በበኩሌ የእንጀራ፣ የዘይት፣ የበርበሬና የሽሮ ማለቅ ሰራተኛ ለማባረር የሚያበቃ ምክንያት መስሎ አልታየኝም ነበር፡፡ እናም ለኦዲተር መሥሪያ-ቤቱ ‹‹ልጃችንን መንከባከብ እስከቻለች ድረስ የፈለገችውን ታድርግ›› ብዬ አቋሜን ለመግለጽ ብሞክርም ‹‹ በ15 ቀን ውስጥ ይሄን ሁሉ አስቤዛ ለመጨረስ ከማይጠግብ ሆድ በተጨማሪ የመስለብ ጥበብ ያስፈልጋል›› በሚል ውሳኔ ተሰናበተች፡፡

ይህ ሁኔታ ከተከሰተ ከወራት በኋላ ግን ‹‹በአንበሳ አውቶብስ አልሄድም›› በማለቷ የተነሳ በኮንትራት ታክሲ አሳፍሬ ይዣት የመጣኋት ሰራተኛ በቀድሞ ሰራተኛችን ላይ የተላለፈው ውሳኔ ስህተት መሆኑን የገለጸና ኦዲተሯን በጸጸት ያንገበገበ ነበረ፡፡

እናም ውዷ ባለቤቴ እኔንም ሆነ ሰራተኛዋን ጠምዳ ስትይዘን ሳሎን ውስጥ ገብተን አረፍ እስክንል ድረስ ጊዜ አልሰጠችንም፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በሰራተኛ ፍለጋ አሳሩን የሚያየው አባወራ ወደ ትዳር ከገባበት ጊዜ አንስቶ በቀላልም ሆነ ከባድ የውስልትና ጠባይ ታምቶ የማያውቅ ቢሆንም ይህችን ሰራተኛ ካመጣ ወዲህ ግን ሚስቱ በርበሬና ሽሮዋን ትታ አባዋራዋን ትከታተል ያዘች፡፡

ሰራተኛዋ ደግሞ ከብላቴናው በተጨማሪ ውበቷን የምትጠብቅ ሆና መገኘቷ የቆይታ ጊዜዋን ያሳጠረው ሆነ፡፡ ‹‹እቃ እጠቢ›› ስትባል ‹‹የእጅ ጓንት ያለበትን ቦታ አሳዩኝ›› ፤ ‹‹ቤት ጥረጊ›› የሚል ትዕዛዝ ሲሰጣት ‹‹የፊት ማስክ ግዙልኝ›› ፤ ‹‹ሽንኩርት ከትፈሽ ጠብቂኝ›› ስትላት ‹‹ቃና ያለበትን ቁጥር ንገሪኝ›› ፤ ‹‹የልጁን ወተት አፈላሽው እንዴ?›› ተብላ ስትጠየቅ ‹‹ለእኔ ግማሽ ሊትር ወተት ያልተከራያችሁልኝ ፆመኛ መስያችሁ ነው እንዴ?›› የሚል መልስ መስጠቷ እሷን ከሰራተኝነት፣ አባወራውን ደግሞ ከተጠርጣሪነት የሚገላግል ሆነ፡፡

ብቻ በአጠቃላይ የችግሩ ምንጭ ሰራተኞቹም ይሁኑ ቀጣሪዎቹ በግልጽ ባይታወቅም ባሁኑ ሰዓት አምስተኛ ሰራተኛችንን አስገብተን እንገኛለን፡፡ አሁን ይሄን በምጽፍበት ሰዓት ራሱ እሜቴ በንዴት ሆና ‹‹እንዴት ያንን ሁሉ ስኳር ቃምኩት ትይኛለሽ?›› ስትላት፣ ሰራተኛዋ ‹‹ጫት እንጂ ስኳር መቃም ለጤና መጥፎ መሆኑን ስላላወኩ ነው!›› እያለቻት ትገኛለች፡፡ እኔ ደግሞ ‹‹ስንትና ስንት የስኳር ፋብሪካ በሚሰረቅበት አገር ላይ የጥቂት ማንኪያ ስኳር መጥፋት የግጭት መንስዔ መሆን የለበትም›› በማለት ሃሳቤን የገለጽኩ ሲሆን የእሜቴ አቋም ግን ‹‹ከሰራተኛ ፍጆታ ለማያልፍ ደሞዝ ስንከራተት ከምውል ሥራዬን ለቅቄ ልጄን አሳድጋለሁ›› የሚል ሁኗል፡፡ (ይሄም ውሳኔዋ በእኔም ሆነ በልጄ ድጋፍ ተችሮት በሙሉ ድምጽ የሚጸድቅበት ቀን ሩቅ አይሆንም፡፡)

የሆነው ሆኖ ወሬዬን እንደ ሰራተኞቻችን እድሜ አጠር ሳደርገው…. አዲስ አበባ ላይ ልጅ ማሳደግ የፈለገ ሰው የሚስቱን ባህሪ የምትቋቋም ሰራተኛ ከማፈላለግ ይልቅ የሰራተኛን ባህሪ የምትቋቋም ሚስት ብትኖረው ይመከራል፡፡ ወይም ደግሞ ‹‹ስራ አለሽ ወይ?›› ብለህ የጠበስካትን ሴት ከእርግዝና በኋላ ሥራ-ፈት ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እናትነት እና የቢሮ ሰራተኝነት አብሮ አይሄድም፡፡

የታደሰው መንግስታችን ደግሞ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ከአገሪቱ ችግር በላይ የሴቶችን ችግር በመረዳት ‹‹በሁሉም መስሪያ ቤት የህጻናት ማቆያ እንዲኖር አደርጋለሁ›› በማለት ቃል የገባ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ የወሊድ መከላከያ ከማሰራጨት አልፎ የህጻናት ማቆያ መገንባት አልተሳካለትም፡፡

እናም ‹‹አንድም እናት በወሊድ ምክንያት መሞት የለባትም›› የሚለው መፎክር ላይ ‹‹ሥራዋን ማጣት እንጂ!›› የሚል ሐገር እንዲጨመርበት በማሳሰብ፣ በእናታቸው እቅፍ ማደግ ላልቻሉ ህጻናት ‹‹በእድላቸው ማደግን›› ተመኝተን ብንሰነባበት ምን ይለናል!!

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close