Connect with us

Ethiopia

እኛ ባመጣነው ለውጥ…..

Published

on

እኛ ባመጣነው ለውጥ…..

እኛ ባመጣነው ለውጥ…..
(አሳዬ ደርቤ)

ከመሥሪያ ቤቴ እስከ መኖሪያ ቤቴ ያለውን መንገድ በሐይገርና በባቡር አቆራርጬ ከቤቴ ስገባ እሜቴ ‹‹ዛሬም ደሞዝ አልወጣም?›› በማለት ጠየቀችኝ፡፡ እኔም ቀልጠፍ ብዬ ‹‹ኧረ ወጥቷል›› በማለት ደሞዜንና ጭንቀቴን ባንድ ላይ አስረከብኳት፡፡

ሚስት ማግባት እኮ ደስ የሚለው ለዚህ ነው፡፡ በወንደላጤነት ዘመንህ በሳምንት ውስጥ የምትጨርሰውን ደሞዝ ለሚስትህ ትሰጥና ከጭንቀት ትገላገላለህ፡፡ ‹‹እንዴት አድርጌ ነው በዚህ ብር ከወር ወር መድረስ የምችለው?›› የሚል ጥያቄ ሲቀርብልህም… ‹‹ሴትዮ እኔ ማድረግ የምችለው የተቀበልኩትን ገንዘብ ባግባቡ ማስረከብ ብቻ ነው›› ትልና ከሐሳቡ በተጨማሪ ሒሳቡንም ለእሷ ታስረክባለህ፡፡

ይሄን ባደረግህ በአስራ አምስተኛው ቀን የሰጠኸው ብር ማለቁ ሲነገርህም ‹‹እስካሁን ድረስ አንዴት አድርጋ አብቃቃችው›› በማለት ፈንታ ‹‹ከምኔው አመድ አደረግሽው?›› ብለህ መንግስት ላይ ያለህን ቁጣ ሚስትህ ላይ ትገልጻለህ፡፡ ታዲያ ከዚህ በላይ ጸጋ የት አለ?

እኔም ይሄኑኑ ከፈጸምኩ በኋላ በመገላገል አይነት ስሜት ሶፋ ላይ ጋደም ብዬ የቴሌቪዥኑን ቻናል ስቀይረው ‹‹ይሄን ለውጥ በዋናነት ያመጣው ማንም ሳይሆን እንትና ነው›› የሚል ፉከራ ጠበቀኝ፡፡ ቲቪውን ትቼ ፌስቡኬን ስከፍትም የለውጡ ባለቤቶች እየሸለሉ ናቸው፡፡

ከዚያም እንደ እስከዛሬው ‹‹ይሄን ለውጥ ያመጣነው እኮ….!›› የሚል ንግግር በሰማሁ ቁጥር ተሳቅቄ ዝም በማለት ፈንታ ‹‹የቱ ለውጥ?›› በማለት ራሴን ጠየኩትና እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ግለሰብ ያገኘኋቸውን የለውጥ ትሩፋቶች አስባቸው ጀመር፡፡

ቅኝቴን ከመሥሪያ ቤቴ ስጀምር ለውጡ አለቃዎቼን አቀያይሯቸው አገኘሁ፡፡ ይሄም ሁኔታ በአሮጌ አመራር ከመሰብሰብ አውጥቶ በአዲስ ባለሥልጣን የመሰብሰብ እድልን እንደፈጠረልኝ አረጋገጥኩ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ከሶስት ዓመት በፊት የተቀጠርኩበትን ደሞዝ ዛሬም እየተቀበልኩት እገኛለሁ፡፡

ከቢሮ ስወጣ ደግሞ በመንገድ ላይ የማየው ነገር የትራንስፖርት ሚኒስትሩ እንጂ የትራንስፖርት ችግሩ አለመቀረፉን የሚያሳይ ነው፡፡ ከለውጡ በፊት የተዘረጋው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር፣ ዛሬም በሺህ የሚቆጠሩ ተሳፋሪዎችን አጭቆ አንድ ጊዜ በሐይል እጥረት፣ ሌላ ጊዜ ከመጨናነቁ የተነሳ በሩን መዝጋት አቅቶት ሃድዱ ላይ እየተንገላወደ ነው፡፡

ባቡሩን ትቼ ወደ አስፓልቱ ስመለከትም የማየው ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ መንገድ መሥራትም ሆነ መኪና ከውጭ ማስገባት ለጊዜው ስለቆመ ከለውጡ በፊት በርካሽ ሲሸጡ የነበሩ ተሸከርካሪዎች ከለውጡ በኋላ ዋጋቸው በእጥፍ ጨምሮ ጎዳናው ላይ ይርመሰመሳሉ፡፡ (አየህልኝ አይደል ለውጡን?)

የሆነው ሆኖ የእኔ እቅድ በመኪና አደጋ አለመሞት እንጂ መኪና መግዛት ባለመሆኑ…. በአዲሱ የትራንስፖርት ታሪፍ በታክሲ ተሳፍሬ ወደ ሰፈሬ በመምጣት የቤቴ ሁኔታ ሲገመገም ለውጡ ከእኔ ይልቅ ለአከራዬ መልካም እድልን ፈጥሮለት ይገኛል፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን በቤቴም ላይ ሆነ በሚስቴ ላይ የለውጡ አሻራ አይታይም፡፡ እርግጥ 14 ፐርሰንት የደረሰው የኑሮ ውድነት ከሚስቴ ፊት ላይ አነስተኛ ማዲያት መፍጠሩን መካድ አልችልም፡፡ የእኔም ክብደት ቢሆን እንደ ብር የመግዛት አቅም በየቀኑ እየቀነሰ በመምጣቱ የኑሮዬን ቀዳዳ ትቼ የቀበቶዬን ቀዳዳ በማጥበብ እንደ ሕውሓት ካልወረድኩ እያለ የሚታገለኝን ቦላሌየን በስፍራው ለማቆየት ትግል ማድረጌን ቀጥያለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ለውጡን በመጠቀም የገዛሁት ልብስም ሆነ ቁሳቁስ የለም፡፡ ወደፊትም ቢሆን በኑሮ ደረጃዋ ከእኔ የተሻለች ሚስት ከሰማይ ካልተላከችልኝ በቀር የተሻለ መንግስት መጥቶ ሕይወቴን ያቃናዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡

ይሄን ብዬ ወደ ሌላ አጀንዳ ስሸጋገር ‹‹አዲሱ መንግስት ሥልጣን በያዘ ማግስት የቤት መሥሪያ ቦታ ባይሰጠኝ እንኳን በተለያዩ አናዳጅ ምክንያቶች ላገኘው ያልቻልኩትን የነዋሪነት መታወቂያ ይሰጠኛል›› በማለት ተስፋ አሳድሬ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በፊት በገንዘብ ሲሸጥ የነበረው መታወቂያ፣ ባሁኑ ሰዓት በሥራ-አጥነት እንጂ በነዋሪነት የማይሰጥ በመሆኑ ይህ ህልሜ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከዚህ ውጭ ግን እንደ ግለሰብ ማሰቤን ትቼ እንደ አገር ሳስብ… በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ቀያቸው ተመልሰው አንዳንዶቹ በፖለቲካው ላይ ሲሳተፉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባንክ ሲዘርፉ ለመታዘብ በቅተናል፡፡ ነገር ግን የችግሩ መንስኤዎች ፓርቲዎቹ እንጂ መንግስት ባለመሆኑ ለውጡን ልናስተባብለው አንችልም፡፡

ባይሆን ‹‹እኛ ባመጣነው ለውጥ›› የሚለውን ማሸማቀቂያ ከህዝቡ ላይ አንስታችሁ ፓርቲዎቹ ላይ ብትጠቀሙት ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፡፡

ብቻ በአጠቃላይ ስፈልገው አምሽቼ በሁሉም ቦታ ያጣሁትን ለውጥ የማገኘው ወደ አካውንቴ ስገባ ነው፡፡ ምክንያቱም ከለውጡ በፊት የማስባቸውን ነገሮች ፌስ-ቡክ ግድግዳዬ ላይ ከለጠፍኩ በኋላ የሚሰጠኝን ኮሜንት እያነበብኩ፣ የሚያስረኝን ኮማንድ ፖስት እጠብቅ ነበር፡፡ አሁን ግን መናገርን የሚከለክሉት ባለሥልጣኖች ተባርረው የተሻሉ መሪዎች ስለመጡ የተሰማኝን ነገር ስገልጽ መንጋቸውን እንጂ ኢህአዴግን መፍራቴን አቁሜያለሁ፡፡

ለነገሩ እኔም ብሆን ከለውጡ በኋላ የምለጥፋቸው ጽሑፎች ከድጋፍ አልፈው ተቃውሞዬን የማይገልጹ በመሆናቸው ለሹመት ካልሆነ በቀር ለእስራት የሚዳርጉ አይደሉም፡፡

ምንም እንኳን በዚያው ህገ-መንግስትና በዚያው ስርዓት ያንኑ ሕይወት እየኖርኩ ቢሆንም፣ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች የሚያወሯቸው ጣፋጭ ንግግሮች ከመሬት ላይ አንዲበቅሉ ከሚደግፉት ወገን ነኝ፡፡ ይሄም እውነታ ለውጡ ያለው በእኔ ጭንቅላት ውስጥ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ባለቤቱም ብሆን እኔ እንጂ አንተ አይደለህም፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ለባለፉት ዓመታት ያደረግነው ትግል ሲለካ የአንተ ፍልሚያ ከእኔ በልጦ ቢገኝ እንኳን ‹‹እኔ ባመጣሁት ለውጥ›› ብለህ መኮፈስ የምትችለው ካመጣኸው ለውጥ ተቋዳሽ ሆኜ ስገኝ ብቻ ነው፡፡ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መንግስታችን ስንቀይር፣ በወርድ እና በቁመታችን ልክ በመረጥናቸው ሰዎች ስንወከል፣ የአገራችን እድገትና አንድነት ሲያንሰራራ፣ ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል ተፈጥሮ ሕይወታችን ሲቀየር ፣ የእኔና የአንተ መብት እኩል ሲከበር…. ያኔ ተጠቃሚነቱ የጋራ ይሆንና የለውጡ ባለቤት አንተ ትሆናለህ፡፡

አሁን ግን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስናስበው ከመጭው ዘመን ይልቅ ያለፈው ሕይወት የተሻለ መስሎ እየታየን ባለበት ሁኔታ… ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ስለባለቤቱ ማውራት የሚቻል አይመስለ|ኝም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

 

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close