Connect with us

Business

ግልጽ ደብዳቤ ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ

Published

on

ግልጽ ደብዳቤ ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ

ግልጽ ደብዳቤ

ለክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል አሙዲ
ሳዑዲ ዓረቢያ

አባቴ ሼህ ሙሐመድ ሆይ!…ለጤናዎ እንደምን ሰነበቱልኝ?

አውቃለሁ፤ እርስዎ የዋህ፣ ደግ አሳቢ፣ የድሆች አባት ኖዎት፣ ከ40 ሺ በላይ ሠራተኞችዎና ቤተሰቦቻቸው አባት ኖዎት፡፡

እንኳንም ከ14 ወራት የግዞት እስር በኃላ፤ ነጻ የመለቀቅዎን፣ በመልካም ጤንነት ላይ የመሆንዎን ዜና ሰማን፡፡ በዚህ ጊዜ ይህን ማስታወሻ ጽፌ ባልረብሽዎ ምርጫዬ ነበር፡፡ ግን የምታዘበው፣ የማየው ነገር ዕረፍት ቢነሳኝ በአቅሜ ምክር ቢጤ ለመጣል ተነሳሁ፡፡ የድፍረት ምክሬ በአጭሩ ወደሚወዱዋት አገርዎ የመምጣት ፍላጎትዎን ያዘግዩት የሚል ነው፡፡

አውቃለሁ፤ አገርዎን ይወዳሉ፣ ወገንዎን ይወዳሉ። ከእስር መልስ ምኞትዎ ሁሉ ወደአገርዎ መመለስ እንደሚሆን ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም። ግን በእኔ ይሁንብዎ!… ውሳኔዎን ያዘግዩት፤ የደፈረሰው እስኪጠራ ባሉበት ይቆዩ።
ይህን ለምን አልክ ይበሉኝ፤ ይጠይቁኝ።

ይህን ያልኩት ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ የሚወዷት አገርዎ ከገባችበት ምስቅልቅሎሽ ገና ያላገገመች በመሆንዋ ነው። ከስሜት፣ ከፍረጃ፣ ከሰዶ ማሳደድ የተላቀቀ መንግስታዊ አስተሳሰብና መዋቅር ገና ባለመዘርጋቱ ነው።

አባቴ ሆይ!.. እርስዎ የሚያውቁት ኢህአዴግ ዛሬ “የለውጥ ኃይል” እና “ፀረ ለውጥ” በሚባሉ ሁለት ኃይላት ከመበለቱ በስተቀር አሁንም በሕይወት አለ። በሰው አምሳል ይበላል፣ ይጠጣል፣ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሳምባ ይተነፍሳል፣ ይሠራል፣ ይወስናል…። ግንባሩ ዶ/ር ዐብይ አሕመድ የሚባል ሊቀመንበርም ሰይሟል።

አባቴ ሆይ.. የኢህአዴግ አዲሱ ሊቀመንበር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ የለውጥ ኃይል የሚባለውን ይመራል። በእውነቱ ይህ ስብስብ ለውጥ ለማድረግ፣ የሕዝብ ጥያቄን ለመመለስ አብዝቶ የሚውተረተር ነው። ይሄ ኃይል የፖለቲካ እስረኞችን ለቋል። አገራቸው ለመግባት በህልማቸው እንኳን ሊያልሙ የማይችሉ የሩቅ የፖለቲካ ኃይሎችን አቅፍ አበባ ይዞ ተቀብሏል፡፡ ይህ ጉሮ ወሸባዬ የበዛበት ደማቅ አቀባበል አንዳንድ ሞኝ ፖለቲከኞችን አሸንፈው የገቡ ያህል እንዲሰማቸው አድርጓል፡፡ ልጨምርልዎ!..የምስራች፡፡ ይኸውልዎ! እርስዎ ማረፊያ ቤት እያሉ ኩርፈኞቹ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሠላም አውርደዋል፡፡

ይህ የለውጥ ኃይል ኢትዮዽያን ያደኸየውን የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ አለም እንኳን መቀየር ባለመቻሉ ግን ክፉኛ ይተቻል፡፡ ይህ መሆኑ በድሮ በሬ እያረሰ፣ አብዝቶ ተስፋ በመስጠት እንዲጠመድ ሆኗል፡፡

“የለውጡ መሐንዲስ እኛ ነን፣ የመደመር ካልኩሌተሩን የሰራን እኛ ነን፣ ሁለተኛ መንግሥት እኛ ነን…” የሚሉ ኃይሎች ደግሞ አሉ። አንዳንዶቹ በቦሌ ወደ አገር እንዲገቡ የፈቀደላቸው ኢህአዴግ መሆኑን ጨርሶ የዘነጉ ናቸው። አንዳንዶቹ ከውጪ ገብተው ኢህአዴግ የሚሰፍርላቸውን ቀለብ አጎንብሰው እየተቀበሉ መሆኑን እየዘነጉ እርስዎን በአንድ ወቅት “ኢህአዴግን ደግፈው ነበር” በሚል ለትችት አፋቸውን የሚያላቅቁ ሞኞች ናቸው። በሞኞች ጭንቅላት ውስጥ ኢህአዴግ የሚባል ገዥ ፓርቲ የለም። በሞኞች ጭንቅላት ውስጥ ዶክተር ዐብይ አህመድ የሚባል የኢህአዴግ ሊቀመንበር የለም። በሞኞች ጭንቅላት ውስጥ አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ልማታዊ መንግስት የሚባሉ ርዕዮተ አለም ሞቶ ተቀብሯል። እናም ሞኞቹ ኢህአዴግን ሲረግሙ እየዋሉ መሪዎቹን እነዶ/ር ዐብይን እንኮኮ እንበላችሁ የሚል ስካር ውስጥ ናቸው።

እርስዎ ማረፊያ ቤት እያሉ እዚህ አገር ያልተፈጠረ ነገር የለም፡፡ ለውጡን ተከትሎ ጊዜው የእኛ ነው ባይ ኃይሎችም ተፈጥረው እየፈነጩ ነው። እነዚህ ኃይሎች ኦሮሞ ሥልጣን ላይ ስለወጣ አጀንዳው ሁሉ የኦሮሞና የኦሮሚያ እንዲሆን ክፉኛ የሚቋምጡ፣ የትላንቱን ስህተት፤ በስህተት ማረም የሚሹ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች በዘረኝነት ጭምር ታውረው በኦሮምያ የሚገኙ የሌላ ብሄር ተወላጆች እና ባለሀብቶችን የጥቃት ኢላማ አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። በጠባብ ብሔርተኝነት ታውረው ኢንቨስትመንት ጭምር እያወደሙ አገር እና ወገን የሚጎዱ ናቸው፡፡ በዚህ ክፉ እርምጃቸው ሰርቶ የሚበላ የገዛ ወገናቸውን ጭምር በአንድ ጀምበር የተፈናቃይ ለማኝ አድርገዋል፡፡

አባቴ ሆይ!… ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ አበባ እያሉ ህወሓት የሚባል አድራጊ ፈጣሪ ፓርቲ እንደነበር አይዘነጉም፡፡ አሁን ጊዜው ፈቅዶ ህወሓት ራሱን ወደመንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲነት አውርዶ አብዛኛው አባላቱ መቐለ መሽገው የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚ ሆነዋል፡፡ “እኛ ከሌለን አገሪቷ ትበታተናለች” የሚል ነጠላ ዜማ እያሰሙ የለውጥ ኃይሉን እየተገዳደሩ ነው፡፡

አባቴ ሆይ!…በዚህ ምስቅልቅሉ በወጣበት የፖለቲካ ምህዳር በአንዳች የፈጣሪ ፍቃድ ገለል ብለው መቆየትዎ ለበጎ ነበር፡፡ አሁንም በአገር ናፍቆት ናውዘው ወደአገርዎ ለመምጣት የያዙትን ሃሳብ በእኔ ይሁንብዎ ይሰርዙት?!…አሁን ያለው የፖለቲካ ትኩሳት፣ ትርምስ ስለአገር፣ ስለወገን ለሚያስቡ የእርስዎ ዓይነት የዋህ ሰው የሚበጅ አይደለም፡፡ እናም አባቴ ሼህ ሙሐመድ ሆይ!… እነኚህ የሰከሩ ኃይሎች ሰከን እስኪሉ፣ የደፈረሰው እስኪጠራ የአገር ናፍቆቱን ቻል ያድርጉት፡፡ የመምጣት ዕቅድዎን ያዘግዩት፡፡

አሳቢ ልጅዎ!
ጫሊ በላይነህ

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮ ጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close