Connect with us

Art and Culture

ሌላኛው አስተምህሮ!

Published

on

ሌላኛው አስተምህሮ! | በቀለ ዘርይሁን

ሌላኛው አስተምህሮ! | በቀለ ዘርይሁን

በዘመናዊ የሀገራችን ንግድ ሥርዓት የዘመነ አስተዳደር ለመመስረት በተደረገው ሙከራ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ተጠቃሽ ከሆኑት ጥቂት ባለድርሻዎች ውስጥ አንደኛው ነው ፡፡ በአሁኑ ወቅት 26 ኩባንያዎች በአንድ ቺፍ ኤግዚኪዮቲቭ ኦፊሰር አመራር ሥራ ያዋቀረው የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የማምረቻና የአገልግሎት ተቋማትን ያቀፈ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ሲሆን ራስን በመቻልና ተደጋግፎ በማደግ የሥራ ክንዋኔም በተምሳሌነት ሲጠቀስ 19 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በማዕድን፣ በእርሻ፣ በሪል እስቴትና ኢንጂነሪንግ ፣በብረታ ብረትና የሕንፃ መሳሪያዎች ምርት በኢምፖርት ጅምላና ችርቻሮ ንግድ፣ በፕላስቲክና ጋዝ ምርት ውጤቶች ፣ በአየርና በየብስ ትራንስፖርት ፣ በትምህርት፣ በሰው ኃይል ስልጠናና ጥበቃ እንዲሁም በሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ ኩባንያዎችን ያሰባሰበ ግሩፕ እንደመሆኑ መጠን በየሙያ ዘርፉ የሰለጠኑና የዓመታት ልምድ የካበቱ ባለሙያዎች የሚገኙበት ግሩፕ ነው፡፡ በሰው ኃይል ፖሊሲ፣ በገበያ ጥናትና ውድድር፣ በጥራትና ብቃት አደረጃጀት ፣ በጥናትና ምርምር ፣ በቴክኖሎጂያዊ ዕውቀትና ስምሪት የዘመናዊ ማነጅመንት ሥርዓት ትግበራ እያከናወነ በሁሉም ዘርፎች ሊወደሱና ሊደነቁ የሚገባቸው አስተምህሮዎችን በማበርከት ለአርአያነት ብቃት ያላቸው ስኬቶች መታወቂያዎቹና መለኪያ አሴቶቹ ያደረገ ግሩፕ ነው፡፡

የእነዚህ እውነታዎች ድምር ባለቤቶች መላው ሠራተኛና ጥቂት የአመራር አባላት ሲሆኑ በየእርከኑ ያላቸው ተቀባይነትም ሆነ ታዋቂነት የዚያኑ ያህል የተራራቀ ከመሆኑ ጋር ተዛምዶ በግሩፑ መሪዎች የሚከናወኑት አንዳንድ ድርጊቶች በትከክለኛ ሚዛንም ሆነ አግባብነት በሌለው መስፈርት በተለያዩ ሚዲያዎች ብሔራዊ ገጽታ እንዲኖራቸው የተደረጉባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡

በግለሰብ የግል ሕይወት ውስጥ የሚመደቡ ውሳኔዎችና ግላዊ ቤተ-ሰባዊ ድርጊቶች ከግሩፕ የንግድ ሥርዓትና ማናጀመንት ጋር ተቆራኝተው ሲተቹባቸውና የማህበራዊ ሚዲያ ቅብብሎሽ ሲደርግባቸውም በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡ ሐሰቱን ከእውነት፣ አሉባልታን ከተጨባጭ ድርጊት የሚያደበላልቁ ሶሺያል ሜዲያዎች እንደየአቅራረባቸውና እንደ ደራሲዎቻቸውም የገበያ ፍላጎት አየሩን ሲሞሉት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ የዓመታት ተሞክሮዎች በማስተማሪያነታቸው መወሰዳቸው ቀርቶ ከማስተማሪያነታቸው በመለስ ተድበስብስው ይቀሩና ጠቃሚ ገጽታቸው ለጊዜውም ቢሆን የሚደበቅበት አጋጣሚም ይፈጠራል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና መስሪያ ቤት በሚገኝበት በመቻሬ ሜዳ ግቢ ውስጥ በቅርቡ የተከናወነ አንድ ከፍተኛ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ዜና የብዙዎችን ጆሮና የማህበራዊ ሚዲያ ድረ ገጾች ለመሳብ በቅቷል፡፡ በጉዳዩ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የትኩረት ርዕስ ለመሆን የቻለው ይህ የሠርግ ሥነ ሥርዓት በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሆኖ፣ ወይም በተወሰኑ ዓመታት የተራራቀ እድሜ ያላቸው ሰዎች ትዳር ሲመሰርቱ ማየት አዲስ ነገር ሆኖ፣ ወይም በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ የሚገኙ ሁለት ሰዎች መጋባታቸው ልዩ ዜና ሆኖ አይደለም፡፡ አሊያም የመጀመሪያና ሁለተኛ ጋብቻዎች በተለያዩ ምክንያቶች ዘላቂነት አጥተው ሶስተኛ ጋብቻ መመስረት ተሰምቶ የማይታወቅ ሆኖ ሳይሆን፣ ጋብቻውን የፈፀሙት እነማን ናቸው? ከሚል መነሻ ብቻ ወሬ ማጣፈጫዎች ተርከፍክፈውበት ለአንባቢና ለተመልካች የሠርጉ ሥርዓት የቀረበበትን ገጠመኝ በትዝብት ጭምር ማስተዋል ችለናል፡፡

ትዳር መመስረት የቻሉ ሰዎች ልምድ እንደሚያረጋግጠው ለሁለቱ ሰዎች መገናኘት አጋጣሚውን የሚፈጥሩት በቆየ ልማድ ባህላዊ ስርዓት ከሆነ ወላጆች ራሳቸው ናቸው፡፡ በዘመናዊው ዓለም ደግሞ ጥንዶቹ የሚገናኙባቸው መንገዶች በቤተሰብ አባል ወይም በጓደኛ ጥቆማ ወይም በሁለቱ የወደፊት ባለትዳሮች የትምህርት ወይም የሥራ ቦታ ትውውቅ ገጠመኞች ናቸው፡፡ ለማንኛውም በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዚኪዮቲቭ ኦፊሰር በሆኑት በዶ/ር አረጋ ይርዳውና በአዳጎ ትሬዲንግ ኩባንያ የማቴሪያልስ ማነጅመንትና ማርኬቴንግ ኦፕሬሽንስ ዳይሬክተር በሆኑት በወ/ሮ ሶፋኒት መንግሥት መካከል የተፈጠረው ትውውቅና ለጋብቻ ብቁ የሆነ ግንኙነት መመስረት አጋጣሚውን የፈጠረው የሥራ ቦታ ትውውቅ መሆኑ እውነት ነው ፡፡ የተፈፀመው የጋብቻ ሥነ ሥርዓት ሂደት እጅጉን ከማማሩም በላይ በመቻሬ ግቢ በተከናወነው ዋናው ሠርግም ሆነ በደብረ ማርቆስ ከተማ በነበረው የመልስ ክብረ በዓል ላይ የታዩት ዝግጅቶች ለየት ያሉ ሆነው በአስተማሪነታቸውና በባህላዊ አክብሮት ተምሳሌትነታቸው ሳይዘከሩ ሊዘለሉ የማይገቡ ለመሆን በቅተዋል፡፡

ታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ዕለቱ ማክሰኞ ነበር፡፡ የዕለቱ አመራረጥ የሠርግ ሥነ ሥርዓቶች በአብዛኛው የሚከናወኑት በሳምንት መጨረሻ ቀናት ወይም በበዓላት ቀናት ስለነበር “ደስታን ለማብሰሪያነት የተመረጠው ይኸኛው ቀን ብቻ ነው” የሚል ልማድ ለማስወገድ ከመቻሉም በላይ የፕሮግራሞች መጣበብና የታዳሚዎች መጨናነቅን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እንደሚቻል በግልጽ የታየበት የሠርግ ዕለት ምርጫ ነበር፡፡ ይህ የሰርጉ የመጀመሪያው አስተምህሮት ነው፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆነው ሁዳ ሪል እስቴት ኩባንያ ከወልድያው ስታድየም ምርቃት ማግሥት ባገኘው ትምህርት ያዘጋጃቸው የልዩ ክንዋኔዎች (በዓላት ) አገልግሎት መስጫ ድንኳኖች በራሳቸው ከማሊኒየም አዳራሽ የተቀራረበ የስብሰባና የልዩ በዓላት ማክበርያ ሥፍራ ለመሸፈን በመቻላቸው ለዚህ ሰርግ ውበትና ድምቀት ልዩ ግብአት ሆነው ነበር ፡፡ የሁዳ ሪል እስቴት ንብረት የሆኑት እነዚህ ድንኳኖች ለየትኛውም ታላላቅ ክንዋኔና የሠርግ ሥርዓቶች መጠናቸው በተፈለገው ሁኔታ ተቀናንሶና ሙሉ ለሙሉ በሆነ ቁመት፣ ወርድና ስፋት እንደ አስፈላጊነታቸው የሚከራዩ ድንኳኖች ሆነው በመዘጋጀታቸው ለኩባንያው ሌላ የገቢ ምንጭ ማስገኚያ የአገልግሎት መስጫ ንብረት መሆን መቻላቸውን ማረጋገጫ ያስመዘገቡበት ልዩ አጋጣሚ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ እጅግ የተዋበው የድንኳኖቹ የውስጥ እይታና የመድረክ ዝግጅቶች ዲኮር ሥራ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሠራተኞች የቀለምና ዲዛይን ምርጫና አስተባባሪነት መከናወኑ የኢንቨስትመንት ቡድኑን የሰው ኃይል ስብጥር ከህሎት፣ ዓይነትና ብዛት ያመላከተ ስለነበር አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡

የዚህ ሠርግ ሥነ ሥርዓት ከጥሪ ካርዶቹ ልዩ ዲዛይንና ስእሎች ይልቁንም ለመታሰቢያነት የሚቀመጡበት ሁኔታ ተመቻችቶ መታተማቸው በራሱ የታሰበበት መሆኑ የሠርጉን ትዝታ ሕያው በማድረግ ልዩ አስተምህሮት ነበረው ፡፡ የታዳሚዎች የመስተንግዶ ሥርዓት ደግሞ በተለይ የሚወደስ ባህላዊ ውበትን የተላበሰ በመሆኑ የሚረሳ አየደለም፡፡ ዘመነኛ ናቸው በተባሉ የሠርግ ሥርዓቶች ሁሉ የመስተንግዶው አገልግሎት በረዥም ጠረጴዛ ላይ በተደረደሩ ሳህኖችና ሸክላ ጣባዎች ወይም ድስቶች የምግብ ዓይነቶች ሲቀርቡበትና ፊት ለፊት ተንዠርግጎ በሚታይና ሉካንዳ ቤቶች በሚያስመስል የጥሬ ሥጋ አቅርቦት መስተንግዶ የተደራጁ መሆናዠው የለመደ ነው ፡፡ የመቻሬ ሜዳው ሠርግና የደብረ ማርቆስ ከተማ የመልስ ዝግጅት ታዳሚዎች የተስተናገዱበት ባህላዊ የምግብ አቀራረብ ሥርዓት ገጽታ ግን በሀገራችን ዳግም መለመድ ያለበትን ታላቅ ባህላዊ ሥርዓትን ያሳዩ ነበሩ፡፡ አራት ሰዎች በአንድ መሶብ (ገበታ) ዙርያ በአንድነት የተስተናገዱበት የምግብና መጠጥ (ማዕድ) አቅርቦት መስተንግዶ በአንድ በኩል ታዳሚዎች ተከብረው በተቀመጡበት ስፍራ ሳይንገላቱና ለዘመናዊ “ቢፌ” ሰልፍ ሳይዳረጉ በተቀመጡበት እንደተከበሩ በጋራ ማህበራዊ ግብዣ እንደ ባህላችን የተቋደሱበት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ምግብ በአክብሮት ወደ ተጠራው እንግዳ ታዲሚ ሰው በአስተናጋጆች የሚቀርብበትን ባህላዊ ሥርዓትን በማዘመን ሰው ዝቅ ብሎ ለምግብ ተሰልፎ የሚስተናገድበትን አቀራረብ የለወጠ መስተንግዶ ስለነበር ለአንግዶች ልዩ የባህላዊ ሥርዓት አክብሮት የታየበት ሆኖ አልፏል፡፡

እንግዶች ከመቀመጫቸው ሳይነሱ በአገር ባህል ወግ እጅ የማስታጠብ ሥነ ሥርዓት ተካሂዶ፣ ወግና ባህሉን በጠበቀ የመሶብ ገበታ ምግባቸውን እንዲቋደሱ መደረጉ ብዙዎችን አስደስቷል፡፡ ያም ሆኖ በባህላችን ሙሽሪትን ማክበር የተለመደ በመሆኑም ሙሽራው እጅ ማስታጠብያ አስቀርበው ራሳቸው ሙሽሪትን ያስታጠቡበት ይህ የሠርግና የመልስ ሥርዓት በልዩ ባህላዊ አስተምህሮነት ሊወሰድ የሚገባው ነው ፡፡

ታዋቂ ሰዎች አልፎ አልፎ ለእይታ ሲባል የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች አሉ፡፡ ምንም እንኳን ሰርጉ ለአንድ ዓመት ያህል በሚታወቅና በተነገረ ምክንያት የዘገየ ቢሆንም ከዚህ በላይ ለእይታ በሚያመችበት ቦታና ሁኔታ ሠርጉን አዘጋጅቶ ለመደገስ ሙሽሮቹ ችሎታው የነበራቸው መሆኑን ማንም ሊጠራጠር አይችልም፡፡ ከሁለቱም ተጋቢዎች የኑሮ ደረጃና የቤተሰብ ሁኔታ የተደገሰው ሰርግ ቢያንስ እንጂ መጠኑን ያለፈ የሠርግ ድግስ አልነበረም፡፡ ሠርጉ ቢያንስ ቢያንስ ለሴቷ ሙሽሪት ቤተሰቦች አክብሮትና ባህል ሲባል ከዚህ በላይ መዘግየት እንደሌለበት ለታዛቢዎች ግልጽ ሲሆን የሰርግ ቦታና የቀለበት ማከናወኛ ቤተ ክርስትያን ምርጫቸውም ቢሆን “ልታይ ልታይ”፣”እዩኝ እዩኝ” ማለትን ያስወገደ ትሁት ምርጫና ክንዋኔ መሆኑን ታዳሚዎች በአድናቆት አስተውለዋል፡፡ እንደ ሙሸሮቹ እምነት የትም ሆነ የት በኦርቶዶክስ ካህናት ጸሎትና ቡራኬ መሆኑ እንጂ ትልቅ ካቴድራል ውስጥ በድምቀትና በሸብሸባ ገዝፎ መታየት ላይ ያተኮረ አልነበረም፡፡ በጣም አነስተኛ በሆነች የጥንት ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ በቃልና በእምነት በጸኑ አንድ ካህን ጽሎትና ቡራኬን በመቀበል ብቻ ከሠርጉ ዕለት ሁለት ቀናት ቀደም ብሎ የተከናወነው የቀለበት ሥነ ሥርዓት በራሱ አስተማሪ ነበር ፡፡

የሙሽሪት አባትና እናት የተማሩና ሁለቱም በጡረታ ላይ የሚገኙ የቀድሞ መምህራን ሲሆኑ የመጀመሪያ ልጃቸውን ለወግ ለማዕረግ ሲያበቁ በዚህ ባህላዊና ትምህርት ሰጪ በሆነ የጋብቻ ሥርዓት አፈጻጸምና ጥር 5 ቀን 2011 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ውስጥ በተከናወነው ደማቅ የመልስ ሥነ ሥርዓት በሙሉ ፍላጎትና አስተዋይነት አዘጋጅና ተሳታፊ መሆናቸው የሚያሰከብራቸው ተምሳሌትነት ነው፡፡ ብዙዎቹን በትምህርት ቤት ኮትኩተው በጥሩ ባህል አሳድገው መልካም ዜጎችን ያፈሩት እነዚህ የቀድሞ መምህራን ለቤተሰቦቻቸውና ለአካባቢያቸው አስተምህሮነቱ ሊጠቀስ የሚችል በመልካም ሥነ ሥርዓት የተገነባ ደመቅ ያለ የመልስ ሥነ ሥርዓት እንዲከናወንና እንደ አዲስ አበባው ሠርግ ሙሉ በሙሉ በማህበራዊ ባህላዊ አክብሮት የታጀበ መስተንግዶ አንዲከናወን ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ፡፡ የጎጃም ሕዝብ በአጠቃላይ ፣ የደብረ ማርቆስ ነዋሪ በተለይ፣ በሰለጠነ ፀጥታ የታጀበ ለባህል ያለውን አክብሮትና ደመቅ ያለ ተሳትፎውን የሳየበት አጋጣሚም ስለነበር ታዳሚው በራሱ የባህላዊ ይዘቱ ጉላት እንዲጨምር አድርጓል፡፡

የሚድሮክ ቴክኖጂ ግሩፕ ሠራተኞችና ማነጀመንት አባላት የሠርጉንና የመልሱን ሥርዓቶች አስተምህሮ በሚያመዛዝኑበት ወቅት በሁሉም ዘርፎች ራሳቸውን የቻሉ ኩባንያዎችና ሠራተኞች የተሰባሰቡበት ግሩፕ መሆኑን የበለጠ አስተውለውበታል፡፡ የቤተሰብና ሠራተኞች ዓመታዊ በዓላትን፣ የደንበኞች ቀናት አከባበርም ሆነ ዓመታዊ የስፖርት ዝግጅቶች ደማቅ በዓላት ተሞክሮዎቻቸው ላይ በሁዳ ሪል እስቴት ድንኳኖች፣ በሬይንቦ ኩባንያ ተሽከርካሪዎች፣ በኢትዮ ድሪም ምርት የተከሸኑ ታይተው የማይጠገቡ ውብና ደማቅ አበባዎች ፣የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ሠራተኞች በሆኑ የግሩፑ ታዋቂ የመድረክ መሪዎችና የሙዚቃ ባለሙያዎች ፣ በአጠቃላይም በሁሉም ኩባንያዎች በሚገኙ የበርካታ ልምድና ዕውቀት ባለቤት በሆኑት ምርጥ ሠራተኞች ተሳትፎ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኩባንያዎች ለምንም ዓይነት ዝግጅት ብቁ ሆነው ወጨውን ሳያንሩ ራሳቸውን ችለው ማናቸውንም ዓይነት ዝግጅት ማሰናዳት እንደሚችሉ በአደባባይ የግሩፕ ሕብረት ሥራና ክህሎታቸውን አስመስክረዋል፡፡ የኩባንያዎቻችንን ግብዓቶች ትስስር (ሲነርጂ) ይዘው ምንም ነገር ለመሥራት መቻላቸውን በተግባር ያረጋገጡበት የሠርግ ሥነ ሥርዓት በመሆኑ ልዩ ኩራት ሊሰማቸው ይገባል፡፡

በዚህ አጋጣሚ የአዲሱ ትዳር መሥራቾች መጪው ጊዜ በፍቅርና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተ የተቃና እና ስኬታማ የሆነ የቤተሰብ ግንባታ ሕይወት የሚታይበት መልካም ጊዜ እንዲሆንላቸው ከልብ እንመኛለን ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close