Connect with us

Entertainment

የምን ጊዜም ምርጥ እንስት ኢትዮጵያውያን የምላቸው…

Published

on

የምን ጊዜም ምርጥ እንስት ኢትዮጵያውያን የምላቸ | በአሳዬ ደርቤ

የምን ጊዜም ምርጥ እንስት ኢትዮጵያውያን የምላቸው… | አሳዬ ደርቤ@DireTube

-እጅጋየሁ ሽባባው፡- ኪነ-ጥበብ ከሴቶች ይልቅ ለወንዶች ነፍስ የቀረበች ናት ብዬ አምናለሁ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ወንዶች በተፈጥሯቸው በጥያቄዎችና በውዝግብ የተሞሉ ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የበእውቀቱ ስዩምን ግጥም፣ በሞገስ ተካ ዜማ እና በቅዱስ ያሬድ ቅኝት ሴቷ ስታንጎራጉረው የሚወጣው ድምጽ እስከ ሰባተኛው ሰማይ የሚሰማ ይሆናል፡፡

ጂጂ ግን በዚህ ገለጻ ውስጥ የምትካተት አይደለችም፡፡ እንደ ዋሽንት ከሚስረቀረቅ ጉሮሮ ጋር ባለመክሊት አዕምሮ ይዛ የተፈጠረች ናት፡፡ ለማሳያም ያህል አድዋንና ኢትዮጵያን ብንወስድ በእሷ ልክ መግለጽ የቻለ የኪነ-ጥበብ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡

በሚያስደምም ድምጿ ‹‹እኔን የራበኝ ፍቅር ነው›› ብላ ስትዘፍን አፍ ማስከፈት ብቻ ሳይሆን በፍቅርም ታስይዛለች፡፡

እሱ አምላክ አይደለ እኔ አልሰግድለትም
ብቻ እግሩን ልሳመው አይሂድብኝ የትም
ዝንጥፍ ዝንጥፍ ያለ የበቆሎ ዛላ

ሰውነቱ እሸት ነው ተጠብሶ የሚበላ፣ ብላ ያንጎራጎረችለትን ሸበላ… ሴቶች ሲያፈቅሩት፣ ወንዶች ይቀኑበታል፡፡
ስለ አድዋ ስትሸልል ደግሞ በስሜት ውስጥ ሆኖ ሙዚቃውን ከማስማት ባለፈም መዋጋት ያምርሃል፡፡
እናም እጅጋየሁ ሽባባው ከዘፋኞች ራስጌ የማስቀምጣት ድንቅ አርቲስት ናት፡፡

-ደራርቱ ቱሉ፡- በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ወደ አፍሪካ ያመጣች፣ የዲባባ ልጆችን ጨምራ ለበርካታ ሴት አትሌቶች ስንቅ በመሆን ያገለገለች፣ የማይስማሙ ሕዝቦችን በድሏ ያስተቃቀፈች፣ ከማንነቷ ይልቅ ኢትዮጵያዊነቷን የምታስቀድም እና አሁንም ድረስ የአገሯን ሥም ለማስጠራት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ውስጥ በኃላፊነት ቦታ እያገለገለች የምትገኝ ዘመን አይሽሬ ኢትዮጵያዊት ንግስት ናት፡፡

-ወ/ሮ አበበች ጎበና፡- በ1972 ዓም ለንግስ በዓል ወደ ግሸን በሄዱበት ወቅት በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ድርቅ የተነሳ በርሃብ የሞተች እናቱን ሲጠባ ባዩት ህጻን የበጎ አድራጎት ሥራን የጀመሩት ወ/ሮ አበበች በዚያው ዓመት ከ20 የሚበልጡ ወላጅ አልባ ህጻናት በመኖሪያ ቤታቸው ሰብስበው ማሳደግ ይጀምራሉ፡፡ ይሄም ሁኔታ ለትዳራቸው መፍረስ እና ‹‹ብሩህ ተስፋ›› የሚባል የበጎ አድራጎት ድርጅት መመስረት ምክንያት ሆነ፡፡

ከዚያን ጊዜ አንስቶም ወላጅ አልባ ለሆኑ ህጻናት አሳዳጊ ብቻ ሳይሆን እናትም በመሆን የብዙዎች ህጻናት ልጅነት እንደ እሳቸው አስተዳደግ የከፋ እንዳይሆን ማድረግ ችለዋል፡፡ ሙሉ እድሜያቸውን ለበጎ አድራጎት ሥራ ከማዋል ባለፈም የግል ንብረታቸውንም ለማዕከሉ አውርሰዋል፡፡ ምንም እንኳን በሕይወት ዘመናቸው የፈጸሙት መልካም ሥራ ተዘርዝሮ የማያልቅ ቢሆንም አሳድገው ለፍሬ ያበቋቸው ልጆቻቸው ‹‹እማማ›› በማለት ሲጠሯቸው አንዳንዶች ደግሞ ‹‹የአፍሪካዋ ማዘር ቴሬዛ›› የሚል ሥያሜ ሰትጠዋቸዋል፡፡ እናም የብዙዎች እናት ለሆኑት ለወይዘሮ አበበች ጎበና ከታላቅ አድናቆት ጋር ረዥም እድሜን እመኛለሁ፡፡

-የትነበርሽ ንጉሴ ፡- በአምስት ዓመቷ የዓይን ብርሐኗን ማጣቷ ከፈጠረባት ችግሮች ይልቅ ያመጣላትን ጸጋዎች እያሰበች ‹‹እድለኛ ነኝ›› የምትል፣ የአካል ጉድለት ለመንገድ ዳር ልመና ተጋላጭ በሚያደርግ አገር ላይ በትምህርቷ በመግፋት በህግ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተመረቀች፣ ለእኛ ለዐይናማዎቹ የተጋረደውን የስኬትና የታላቅነት መንገድ የሚመለከት ብሩህ ልብ እና አዕምሮ ተሰምቶ ከማይጠገብ አንደበት ጋር የታደለች፣ ለበርካታ አካል ጉዳተኞች ሮል ሞደል የሆነች፣ ሎሬት ከሚል ማዕረግ ጋር በሽልማት ያገኘችውን 374000$ ለበጎ አድራጎት ሥራ ለማዋል እየተንቀሳቀሰች የምትገኝ አስደናቂ ልበ-ብርሐን ሴት ናት፡፡

-እሟሐይ ጽጌ ማሪያም፡- ኢየሩሳሌም በሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት ውስጥ የሚኖሩ መነኩሴ ሲሆን ፒያኖን ይጫወቱታል ከማለት ይልቅ ‹‹ያጫውቱታል›› ብንል ይገልጻቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ የክላሲካል ሙዚቃ ታሪክ ውስጥም የጎላ ሥም ካላቸው የሙዚቃ ፈጣዎች ግንባር ቀደም መሆናቸውን የጃዝ ንጉሱ አቶ ሙላቱ አስታጥቄም መስክሮላቸዋል፡፡ እናም የ94 ዓመት የእድሜ ባለጸጋ የሆኑት እሟሃይ ጽጌ ማሪያም ፒያኖ መጫወት የጀመሩት ገና በልጅነታው ሲሆን ፒያኖውን በጣቶቻቸው ሲነካኩት መሳሪያው የእሳቸውን ስሜት ይጋራል፡፡ ሲያለቅሱ አብሯቸው ያለቅሳል፡፡ ሲስቁ አብሯቸው ይፈነጥዛል፡፡ ሲመንኑ አብሯቸው ይመንናል፡፡ ለመንፈሳዊያኑም ሆነ ለዓለማዊያኑ የሚጣፍጥ ኖታ ያፈልቃል፡፡

እማሆይ ጽጌ ለአድማጭ ጆሮ ያልደረሱ በርካታ ሥራዎች ያሏቸው ሲሆን እስካሁን ድረስ ከስድስት በላይ አልበሞችን በማውጣት የሙዚቃ ሊቅ መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ከሥራዎቻቸውም መሃከል ‹‹Song of the sea & Homeless wonderer›› የሚል ሥያሜ የሰጧቸውን አልበሞች መጥቀስ የሚቻል ሲሆን እንደ አጠቃላይ ግን እሟሃይ ፅጌማሪያም ከመንፈሳዊ ህይወታቸው በተጨማሪ በፒያኖ ችሎታቸው የሚደነቁ አስገራሚ እናት ናቸው፡፡

-መዓዛ ብሩ፡- በተፈጥሮ ያገኘችውን አዕምሮ በንባብ አዳብራ የመረጃ ቋት መሆን የቻለች፣ ጋዜጠኛ ሲባል ቀድሞ የሚታወስ ሥም የገነባች፣ የጨዋታ እንግዳ በሚል ፕሮግራሟ ላይ የምታቀርባቸውን እንግዶቿን ሥሜት በመመርመር እንዴት እና ምን ማውራት እንዳለባት ጠንቅቃ የምታውቅ፣ ድንቅ ጋዜጠኛ ናት፡፡

-ብርቱካን ሚዴክሳ፡- አሳሪውም፣ ከሳሹም፣ ምስክሩም፣ ፈራጁም ኢህአዴግ በነበረበት ሰዓት የሙያ ግደታዋን የተወጣች፣ ‹‹በህግ እንጂ በሰው አልመራም›› በማለት ሥራዋን የለቀቀች፣ ፖለቲካ ክስረት በነበረበት ሰዓት በፓርቲ ታቅፋ አምባገነኑን ስርዓት የታገለች፣ ይቅርታ አልጠይቅም በማለቷ የተነሳ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደባት፣ በወህኒ ቤት ውስጥ የሚፈጸመውን ግፍና ጥቃት ተቋቁማ አልሸነፍ ባይነቷን ያሳየች፣ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከከፈለች በኋላም የሰላም አየር እየተነፈሱ ከመኖር ይልቅ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ ተመድባ በሙያዋ ህዝቧን ለማገልገል ወደ ሃገሯ የተመለሰች…

-ሕይወት ተፈራ፡- የሴቶች እጣ-ፈንታ በወንዶች ጭንቅላት በሚወሰንበት ዘመን ላይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት ከዚያ ትውልድ ጋር ተሰልፋ የእነ ማርክስን እና ሌኒንን ፍልስፍና ያጠናች፣ ዲሞክራሲያ ጋዜጣንን በልብሷ ውስጥ ሸጉጣ ያከፋፈለች፣ ለሕዝቧ ነጻነት የታገለችና የተንገላታች፣ ከጥቂት አመታት በፊት ደግሞ የኢህአፓን እና የፍቅር ሕይወቷን ቀላቅሎ የያዘ‹‹Tower in the sky›› የሚል መጽሐፍ ጽፋ ከፍተኛ አድናቆትን ያገኘች ብርቱ ሴት ናት፡፡

-ከዚህ ባለፈ ደግሞ የኢትዮጵያ ምርት ገባያን በመመስረት የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊ ለማድረግ የድርሻዋን ያበረከተችውን ዶክተር ኢሌኒ ገብረ-መድህንን፣ የሜሪጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር በመሆን የ1.5 ሚሊዮን ህዝብ እናት ለመሆን የበቃችውን ሲስተር ዘቢደርን- በሴትነታቸው ሳይሆን በብቃታቸው ተመርጠው የአገራችን ፕሬዝዳንት የሆኑትን ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴን፣ በብእሯ አምባገኑን መንግስት ሞግታ በርካታ ዋጋ የከፈለችውን ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙን፣ የሶልሬብልስ ጫማ ባለቤት የሆነችውን ቤተልሄም ጥላሁንን አለማድነቅ አይቻልም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close