Connect with us

Business

ወላይታ ሶዶ-ሳንባ የዳሞታን አየር፤ ወላይታ ሶዶን ረግጦ ማን ያልፋል?

Published

on

ወላይታ ሶዶ-ሳንባ የዳሞታን አየር፤ ወላይታ ሶዶን ረግጦ ማን ያልፋል?

ወላይታ ሶዶ-ሳንባ የዳሞታን አየር፤ ሆድ ደግሞ የማይጠገበውን የበሬ ቁርጥ የሚመገብባት ከተማ፤ (ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ኦሞ ሸለቆ እየተጓዘ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ አርባ ምንጭ የሚያቀኑ መንገደኞች አረፉ የሚሉባት፤ ስጋ ቆርጠው የሚደሰቱባት ወላይታ ሶዶ ለምሳ አርፎ የዳሞታን አየር እየሳበ ያሳለፈውን ጊዜ እንዲህ ያካፍለናል፡፡) ሄኖክ ስዩም በድሬቲዮብ

ዳሞታ ስር ነኝ፡፡ ዳሞታ ተራራ ብቻ አይደለም፡፡ አሁን የምስበው አየር ከዚያ ታሪካዊ ተራራ ቁልቁል የሚለቀቅ በረከት ነው፡፡ ሶዶ የምትስበው አየር ዳሞታ የሚተነፍሰውን ነው፡፡ የኦሞ ሸለቆ በራፍ ናት፡፡ የካዎ ጦና ሀገር፡፡ የንጉሥ ከተማ ስለመሆኗ ዛሬም የሚጠራጠር ሰው የምታሳምን ከተማ ናት፡፡ ወላይታ ሶዶን ረግጦ ማን ያልፋል? እዚህ አረፍ ማለት ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ የተፈጥሮ ሰንጋ በተፈጥሮ እህል የሚቀርብበት ምሳ የት ይገኛል?

የወላይታ ቁርጥ የጊፋታ ብቻ የሚቀርብ ጌጥ አይደለም፡፡ አመቱን ሙሉ አለ፤ ሁሌም የሚጣፍጥ ጥሬ ስጋ የሚበሉባት ከተማ ናት፡፡ የወላይታዎች መዲና አሁን እየሰፋች ነው፡፡ ገዝፋለች፡፡ ጎዳናዎቿ ሰው ይርመሰመስባቸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዋ ከመላ ኢትዮጵያ የሚመጡ ተማሪዎችን ከወላይታ ምድርና ከወላይታዎች ባህል ጋር ያቆራኛቸዋል፡፡ የዲቻን ማሊያ ለብሰው የሚወዱትን ክለብ ደረታቸው ላይ ለጥፈው የሚሄዱ መንገደኞች ብዙ ናቸው፡፡

ከቦሎሶ ሶሬ እስከ ዳሞት ጋሌ፣ ከዳሞት ሶሬ እስከ ዱጉና ፉንጎ፣ ከቦዲቲ እስከ ሁምቦ፣ ከአረካ እስከ ኦፋ፣ ከኪንዶ ኮይሻ እስከ ዳሞት ወይዴ፣ ከቦሎሶ ቦምቤ እስከ ዳሞት ፉላሳ፣ ከኪንዶ ዲዳዬ እስከ ሶዶ ዙሪያ ሁሉም መዲናዬ የሚላት የወላይታዎች የባህልና የታሪክ ከተማ ነኝ፡፡ የታታሪ ገበሬዎች መዲና የሆነችው ሶዶ ከደጋማው ምድር እስከ ሸለቆው ቆላ ድረስ ምድሩ የሚሰጠውን በረከት አንድ ስፍራ ማግኘት የፈለገ ከሶዶ የተሻለ ምርጫ የለውም፡፡

ወላይታ የምታድሩ ሰዎች ሞቼ ቦራጎ ዋሻ ብላችሁ ጠይቁ፤ ከ50 ሺህ ዓመት በፊት የሰው ዘር ኖሮበታል የተባለ የአርኪዎሎጂ ዋሻ ትጎበኛላችሁ፡፡ ሊጋባ በየነ ሶዶ ከተማ የሚገኝ ቀደምት ትምህርት ቤት ነው፡፡ ሙዚቃ ላይ የሰማነው ትምህርት ቤት በስማቸው የተጠራው ሰው የግቢ አዛዥ፣ የቤተ መንግሥቱ ሊጋባ የወላይታ አስተዳዳሪ የነበሩ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

በንጉሡ የአልጋ ወራሽነት ዘመን አድማ መቱ ተብለው ተገረፉ፡፡ በግርፋት የቀጧቸው ንጉሥ የጦርነት ክተት ሲያውጁ ሊጋባ በየነ ማይጨው ዘምነተው ለእናት ሀገራቸው ፍቅር ሞቱ፡፡ የደጃዝማች ወልደሰማያት ገብረወልድ ቱሩፋቶች ዛሬም አሉ፡፡ ወላይታ ሶዶን አልፈን እስከ ኦሞ እንጓዛለን፡፡

አርባ ምንጭ አድረን፣ ጉማይዴ አሳ በልተን ኮንሶ እረፍት አድርገን ዱካቱ ጠጅ ተጎንጭተን እስከ ጅንካ የማይሰለቸውን ቸር ምድር እንጓዝበታለን፡፡ ማጎና ኦሞ ሰላም መክረማቸውን እንጠይቃለን፡፡ ከላይኛው ኦሞ እስከ ታችኛው ኦሞ ሸለቆ ጉዞው ይቀጥላል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close