Connect with us

Business

መቶ ቀናት የጠበቡት የመቶ ቀናት ዕቅድ!

Published

on

መቶ ቀናት የጠበቡት የመቶ ቀናት ዕቅድ ! | በሬሞንድ ኃይሉ

መቶ ቀናት የጠበቡት የመቶ ቀናት ዕቅድ ! | በሬሞንድ ኃይሉ

አንድ ሰሞን ወሬው ሁሉ ስለ መቶ ቀናት ዕቅድ ሁኖ ነበር፡፡ በጥቅምት ወር ለሚኒስትሮች ከተሰጠው ስልጠና በኋላ አጀንዳ የሆነው ይህ ዕቅድ ሀገሪቱን ከወራት በኋላ ወደ አንድ የስኬት ጫፍ እንደሚያደርስ ተደጋግሞ ተነግሮለታል፡፡ የመንግስትም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኃንም ስለጉዳዩ ደጋግመው ተርከዋል፡፡ ይሁን እንጅ የአንድ መቶ ቀናት ዕቅዱ የመነሻውን ያህል መድረሻው ትኩረት አልሳበም። ጠቅላይ ሚንስሩ በተገኙበት አፈጻጸሙ ቢገመገምም መነጋገሪያ የመሆን ኃይል ግን አለገኘም።

ይህ ለምን ሆነ ካልን በመላምት ደረጃ አንድ ሀሳብ እንድናነሳ ዕድል ይስጠናል። የመቶ ቀናት ዕቅዱ ከሞላ ጎደል አልተሳካም። እንዲህ ያለው መላ ምታችንን በማስረጃ ለማየት እንሞክር። ለዚህ እንዲረዳንም ተቋማት ለፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ያቀረቡትን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንመልከት።

የንግድ ሚኒስቴር በመቶ ቀናት ውስጥ ለማሳካት ያቀደው ዋናው ጉዳይ የተቀዛቀዘውን የውጭ ንግድ እንዲያንሰራራ ማድረግ ነበር። ነገር ግን ሚንስትሯ ወ/ሮ ፈትለወርቅ እንዳሉት አፈጻጸማቸው እንኳንስ ዕድገት ሊያስመዘግብ ካለፈው አመት አንጻር ሲታይ የ10.80 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። በዘርፉ 1.96 ቢልዮን ዶላር ለማግኘት ቢታቀድም የተሳካው 1.21 ቢልዮን ዶላሩ ብቻ ነው። ይህን ዕቅዱ ከ62 በመቶ በላይ መሳካት እንዳልቻል ያሳያል።

የሀገሪቱን የምንዛሬ ችግር በመፍታት በኩል የላቀ ሚና ይጫወታል የተባለው የውጭ ንግድ ጉዳይ በንግድ ሚኒስቴር ሪፖርት መሰረት ያለው ቁመና ይህን ሲመስል ብሄራዊ ባንክም ከዚህ የተሻለ አፈጻጽም ማስመዝገብ አልቻልም። ባንኩ ለውጭ ገብያ አቀርበዋለሁ ብሎ ካሰበው የ ወርቅ መጠን ያሳካው አምስት በመቶ ብቻ መሆንም ይህን ያሳያል።

ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ተስፋ ሰንቀዋል የተባሉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጉዳይም ወደ ቀቢጸ ተሰፋነት መቀየራቸውም ተስምቷል። ያለፉ አመታትን አፈጻጸም ሳይቀር ሪፖርት ያደረጉት የኢንዱስትሪ ፓርኮች የስራ ሀላፊዎች ተቋማቸው አጣብቂኝ ውስጥ መሆኑን ተናግረዋል። ለማሳያነትም ከሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 50 ቢልዮን ብር ለማግኘት ቢታቀድም የተሳካው 2 ቢልዮን እንኳን የሚሞላ አልሆነም።

ለኢትዮጵያ መንግስት የኢኮኖሚ ዋና መሰረት የሆነው ግብር አሰባሰብም ውጤቱ ስኬት የራቀው መሆኑ አያጠራጠርም። ባለፉት ስድስት ወራት 122.18 ቢልዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ የተገኘው 98.67 ብር ብቻ ነው። ከላይ የተመለከትናቸው አብነቶች መቶ ቀናትን በጉያቸው የያዙት ስድስት ወራት በኢኮኖሚው በኩል ግባቸውን እንዳልመቱ የሚያሳዩ ናቸው።

የአስፈጻሚው አካል ቁንጮ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አህመድ ከሞላ ጎደል እንዳረቀቁት የሚነገረው ይህ ዕቅድ ዕጅጉን ጉጉት የሚስተዋልበት ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ለመተግበር አይደልም ለመዘጋጀት ራሱ መቶ ቀናት የማይበቃቸው ጉዳዮች ሳይቀር ከሦስት ወራት በኋላ እንደሚሳኩ አድርጎ አቅርቧል፡፡ የመከላክያ ሚኒስቴርን የመቶ ቀናት ዕቅድ የተመለከተ ሰው ይህን ሀሳብ በአግባቡ የሚረዳው ይመስለኛል፡፡

የሚኒሲቴር መስሪያ ቤቱ በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ከግብ አደርሰዋለሁ ብሎ የተረከበው አንዱ ጉዳይ የባህር ኃይልን ማደራጀት ነበር፡፡ ይሁን እንጅ ከወራት በኋላም የባህር ኃይል ማደረጃት አይደለም የት እንደምንመሰርት እንኳን የታወቀ ነገር የለም፡፡ የመመስረቻ ረቂቁ ለፓርላማ ደርሶ የጸደቀውም ገና በቅርቡ ነው፡፡

የአንድ መቶ ቀናት ዕቅዱ እንደ ዕድገትና ትርንስፎርሜሽን ዕቅዱ መረገጫው ዕርቁ እንደሆነ የሚገባን ግን መከላክያ ሚኒስቴር አሳካዋለሁ ያለውን በመመልከት ብቻ አይደለም፡፡ የሰላም ሚኒስቴር በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ መራጋጋት አስፍናለሁ ብሎ ነበር፡፡ ይህ ዕቅድ ከመነሻው አሻሚነት ያለው ነው፡፡ ሀገራዊ ሰላም ሊሰፍን የሚችለው ለግጭት መነሻ የሆኑ ጉዳዮች በውሉ ሲለዩና በእነሱ ላይም መግባባት ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ዛሬ ኢትዮጵያ ሰላም እንደራቃት አንጅ ለምን እንደራቃት ከመግባባት ላይ ለመድረስ አዳጋች ሁኗል፡፡ ከፊሉ ወገን ፌደራሊዝሙን ለመጠው መዓት ሁሉ ሲኮንን የቀረው ፌደራሊዝሙን መተቸት አይደለም ስለሱ ክፉ ማውራት ሀገር ያፈርሳል የሚል ዛቻ ማሰማት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

ከሁሉም በላቀ መልኩ ደግሞ የስራ አጥነት መጠኑ በጊዜ ሂደት ከመቀነስ ይልቅ እየጨመረ መሄድ ወጣቶችን ለጎዳና ላይ ተቃውሞ ቅርበ አድርጓቸዋል የሚለው ሀሳብ ጠንክሮ እየተደመጠ ነው፡፡ የሰላም ሚኒስቴር ግን ከወራት በፊት ከአንድ መቶ ቀናት በኋላ በኢትዮጵያ ሰላም አሰፍናለሁ ብሎ ተነሳ፡፡ የሰላም ዕጦቱን መነሻ በውሉ ሳይውቅ ወደ ህክመና መግበቱም ዕቅዱን የማጨበጥ አደረገው፡፡ የሀገሪቱ ሁኔታም ከመረጋጋት ይልቅ ይበልጥኑ መልኩን እየቀያረ እየሰፋ ሄደ፡፡

ሚኒሲትር መስሪያ ቤቱ ሰላም አመጣለሁ ብሎ ጉዞ በጀመረ ማግሰት ዩኒቪርስቲዎች በብሄር ትርመስ የተማሪዎችን አሰክሬን ለመሸኘት ተገደዱ፡፡ በምዕራብ ወለጋና ቢንሻጉል ጉምዝ ክልል በተፈጠረ አለመረጋጋት በመቶ ሺዎች ተፈናቀሉ፡፡ ስላማዊ የሚባለው የአፋር ክልልም የተቃውሞው አውድማ ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡

ከላይ የጠቀስናቸው ማሳያዎች ለአብነት ያህል ተብራሩ አንጅ የሌሎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ዕውነትም ከዚህ አይርቅም፡፡ እንዲህ ከሆነ ተቆጥሮ የተሰጠውን ስራ በጊዜው ያላደረሰ ሚኒስትር በኃላፊነቱ አይቀጥልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ምን ሊወስኑ ይችላሉ? ዕቅዱን መከለስ ወይንስ አብዛኘኞቹን ሚኒስትሮች ከኃላፊነት ማንሳት?

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close