Connect with us

Ethiopia

ዳዊት ዮሐንስ ማንነው?

Published

on

ዳዊት ዮሐንስ ማንነው? | በያሬድ ጥበቡ

ዳዊት ዮሐንስ ማንነው?
(በያሬድ ጥበቡ)

የወዳጄ ዳዊት ዮሐንስ የቀብር ሥነሥርአት በአዲስአበባ በመጪው ቅዳሜ እንደሚፈፀም ሰምቻለሁ። ከሁለት ቀናት በፊት የመሞቱን ዜና ለወዳጅ ዘመዱ በፌስቡክ ገፄ ላይ ሳጋራ ካልተጠበቁ ሃይሎችና አዲስ በተነሳው የአማራ ብሄርተኝነት የሰከሩ አንዳንድ ወጣቶች እንወክልዋለን የሚሉት ህዝብ ባህል የማይቀበለውን ተራ የዱርዬ ቃላት ሲያሰሙ በማየቴ አዝኛለሁ። ይህ የዱርዬዎች መረን የለቀቀ ተግባር በመንግስት ላይ ተፅእኖ አሳድሮ ዳዊት ዮሐንስ በቀድሞ የተወካዮች ምክርቤት አፈጉባኤነቱና በቀድሞ በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ አምባሳደርነቱ የሚገባውን የክብር አቀባበር ከማግኘት፣ መንግስትን ዓይንአፋር እንደማያደርገው ምኞቴ ነው ። ስለዳዊት የማውቀውንም በጥቂቱ ማጋራት እወዳለሁ።

ዳዊትን ከተፈሪ መኮንን ትምህርትቤት ተማሪነታችን ጀምሮ አውቀዋለሁ። እኔ 7ኛ ክፍል እያለሁ፣ ዳዊት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ነበር ። ትምህርትቤታችንን በመወከል ይደረጉ በነበሩ የተማሪዎች የክርክር መድረኮች ይካፈል ስለነበር ይመስለኛል፣ እሱ ባያውቀንም ዳዊትን እናውቀው ነበር ። ኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአንደኛ ዓመት ተማሪ ሳለን፣ ፕሮፌሰር አሊ ማዙሪ ከኡጋንዳ መጥቶ በመኮንን አዳራሽ ንግግር ባደረገ ምሽት የህግ ተማሪ የነበረው ዳዊት ባሰማው ዲስኩርና የተቃውሞ ድምፅ ይበልጥ መደነቅንና ስምን አተረፈ። በቀጣዩ አመት የተማሪውን ማህበር ለማስመለስ በተደረገው ትግል ከነመለስ ተክሌ ጋር ግንባርቀደም ተዋናይ ሰለነበር ዳዊት ይበልጥ በተማሪው ዓይን ገባ። ማህበሩም ተፈቅዶ የምርጫ ዘመቻ ሲጀመር፣ በህጉ መሠረት የአንደኛ አመት ተማሪዎች ሙሉ የመምረጥ ድምፅ ስላልነበራቸው ዳዊት ሙሉ ድምፅ እንዲያገኙ ያደረገው ተጋድሎ የፍሬሽሜኖቹን ፍቅር ያሰገኘለት ቢሆንም፣ “ህዝበኝነት” ወይም ፖፑሊስትነት ነው የሚል ውግዘት ከቀሩት የከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች ደረሰበት። በዚህም የተነሳ የማህበሩ ልሳን የሆነው የ”ታገል” መፅሄት ዋና አዘጋጅ ለመሆን ባደረገው የምረጡኝ ዘመቻ በጣት በሚቆጠሩ ድምፆች በመለስ ተክሌ ተሸነፈ።

በቀጣዮቹ የየካቲት አብዮት ወራትና አመታት ኢህአፓ እየገነነ ሲመጣ ፣ ዳዊትና ጓደኞቹ (እነወርቅነህ ቸርነትና ገነነው አሰፋ) በኢህአፓ አካሄድ ላይ በግላቸው ያሰሙት በነበረው ሂስና ትችት የተነሳ “ቀባ” (ቀይ ባንዲራ) ተብለው በኢህአፓና የአዲስአበባ ወጣቶች ስማቸው “ጎደፈ” ። በኢህአፓ ደጋፊ ወጣቶች ዓይናችሁን ላፈር ተባሉ። በወቅቱ እኔ የኢህአፓ አባል የነበርኩ ቢሆንም፣ እነዳዊት ማታ ማታ የሰፈሬ ልጆች የሆኑት የወንድማማቾቹ የለማና ሰለሞን ቤት ሲመጡ እየተገናኘን መወያየትና መከራከር እናዘወትር ነበር። ሌሎች የህግ ተማሪዎች የነበሩም የደርግ ደጋፊዎች የነበሩ ተማሪዎች እነ ዘላለም በንቲ፣ ሰለሞን ገብሬ ወዘተም እየመጡ ስንከራከር እናመሽ ነበር ። እኔ ለማን ለኢህአፓ አባልነት በመመልመል ለይ ስለነበርኩ ቤተኛ ሆኜ ነበር። ይህንን ስብስብ ይታዘቡ የነበሩ የሰፈሬ ልጆች ከነዳዊት ጋር አዘውትሬ ከመገናኘቴም በላይ በወጣት ማህበሩ ስብሰባ ላይ ከፓርቲዬ ወጣ ያለ አስተሳሰብ በማራመዴ “ቀባ ወይም ቀይ ባንዲራ” የሚለው ታፔላ ወይም ታርጋ እኔም ለይ ተለጠፈብኝ ። ሰፈሬ ውስጥም መኖር አደገኛ እየሆነ ሲመጣ ሰፈሬን ለቅቄ ወደቦሌ አጎቴ ቤት ለመሰደድ ምክንያት ሆነ ።

በ1969 አጋማሽ ላይ እኔ ለትጥቅ ትግሉ ወደ አሲምባ ሳቀና ዳዊትና ጓደኞቹ ወደ ሱዳን ተሰደዱ ። ሆኖም ሱዳን ሲደርሱም ኢህአፓ ቢሮ ከፍቶ ምሬቱን ይዞ ጠበቃቸው። የሱዳን ቆይታቸውን መራር እንዳደረገባቸው አጫውተውኛል። በፊት በቀይ ባንዲራነት ስማቸው የጎደፈ ቢሆንም አንዳቸውም ቀይ ባንዲራ የሚባለውን በራሪ ወረቀት የሚያትመው የኢትዮጵያ ኮሙኒስት ፓርቲ (ኢኮፓ) አባል አልነበሩም ። ከአመታት በኋላ እአአ በ2006 ወደ ለንደን ስሄድ የኢኮፓ ሊቀመንበር የነበረውን ዶክተር አሰፋ እንደሻው “እነ ዳዊት የኢኮፓ (ቀባ) አባላት ነበሩ ወይ?” ብዬ ላቀረብኩለት ጥያቄ በፍፁም እንዳልነበሩ አጫውቶኛል። ዛሬ በኦሮሚያና አማራ ክልል ለነገሰው የወመኔ ፍርደገምድልነት (mob justice) ትምህርት ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ከዳዊት ጋር ከዓመታት በኋላ የተገናኘነው፣ የኢህዴን (የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ) አመራር አባል ሆኜ እ.አ.አ በግንቦት 1985 ወደ አሜሪካ ዲሲ በመጣሁ ወቅት ነበር ። ከስምንት ዓመታት በኋላም ሳገኘው ዳዊት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በመንፈሱ ሙሉ ለሙሉ የተነከረ ነበር። 17ኛውና ኪው መንገዶች መገናኛ ላይ በሚገኘው የትሪዮ ካፌ በረንዳ ላይ በየእለቱ እየተገናኘን መከራከርና ማምሸት ጀመርን ። ኢህአፓ በሺዎች ተሰዶ አሜሪካ ከገባ በኋላ “ጥቂት ቆራጦች ያልተንበረከክን አለን” የሚለው ኢህዴናዊ መልእክቴ ለዳዊትና ጓደኞቹ ብርቅ ነበር ። ዳዊት ድጋፉን ፍቅሩን ሊሰጠን አፍታም አልወሰደበትም። አግራሞቱን ለመግለፅ የገነነው ታላቅ ወንድም እስክንድር “ስታር ትሬክ” ብሎ ቅፅል አወጣልኝ ። የተለያዩ ከተሞች ጎብኝቼ ስመለስ የእነዳዊት ቡድንና ትሪዮ ካፌ መመለሻ ጎጆዬ ነበር ። ያንኑ ዓመት በሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ብላክበርን ሴንተር ላደረግኩት የስብሰባ ጥሪ በድል መጠናቀቅ የዳዊት ድጋፍና እርዳታ ጉልህ ነበር ።

ከስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ወደበረሃ ስመለስ እ.አ.አ በህዳር 1985 አንገረብ ወንዝ ዳር አርማጨሆ ውስጥ በሚገኘው የኢህዴን የስምሪት ማእከል (ቤዝ አምባ) የኢህዴን አመራር ስብሰባ ሲደረግ ስለውጪ ጉዞዬ ባቀረብኩት መዘርዝር (ሪፖርት) በአባልነት ሊመለመሉ ይችላሉ ብዬ ካቀረብኳቸው ስሞች መሃል የዳዊት ዮሐንስና አንዳርጋቸው ፅጌ ስሞች ቀዳሚዎቹ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ጠቅልዬ ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ኢህዴንን ወክዬ በአመታዊው የአፍሪካ ቀንድ ኮንፈረንስ ላይ የማቀርበውን ንግግር ከዳዊት ጋር ሆነን በጋራ አዘጋጀን ። እአአ በ1989 መለስ ዜናዊ ወደ ዲሲ ሲመጣ ከዳዊትና ብርሃኑ ነጋ ጋር ሆነን ስንከራከር ውለን ስንከራከርና ስንዝናና አመሸን ። እኔ ከድርጅቱ ከተገለልኩ በኋላ ዳዊት ወደሜዳ ለስብሰባ መሄዱን ሰማሁ። ኢህአዴግ አሸንፎ አዲስአበባ ሲገባና የመጀመሪያውን የተወካዮች ምክርቤት እ.አ.አ በ1995 ሲያቋቁም ዳዊትን የመጀመሪያው አፈጉባኤ አድርጎ አስመረጠው ። ዳዊት በሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ኢህአዴግ በአመራር አባላቱ ላይ በሚያደርገው ቁጥጥር የተነሳ ይሁን ወይም በግል ምርጫው ከዳዊት ጋር የነበረን ግንኙነት እየከሰመ ሄደ።

የመጀመሪያው ሃገራዊ ምርጫ እ.አ.አ በ1995 የተደረገ ሰሞን ዳዊትን ከገነነው አሰፋ ጋር ሆነን አንዲት ዘመዳቸው ቤት ለእራት አገኘነው ። ኢህአዴግ ያገኘውን መጠነሰፊ ድል (82•9%) የተብዛዛና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳልነበር ማሳያ አድርገን ስንከራከረው ዳዊት ይባስ ብሎ “እናንተ የድሉ ማርጂን በዛ ትላላችሁ እኛ ደግሞ እንደ ኢህአዴግ ተሰብስበን፣ ያጣናቸውን የምክርቤት መቀመጫዎች ለምን አጣን ብለን ነው ስንመራመር የነበረው” ብሎን ወሽመጣችንን ቆረጠው ። ሁላችንም ለመለ ወጥ ተስፋ አለው በሚል ሃሰባችን ላይ ተስፋ ቆረጥን። አንዳንዶች ሁለተኛ ላያገኙት አመረሩ።

ከዚህ ግንኙነት በኋላ ዳዊት በሥልጣን ላይ እያለ አንድ ሶስቴ ተገናኝተናል። አንዱ የማስታውሰው ከ1997 ምርጫ በኋላ የቅንጅት መሪዎች ታስረው በነበረበት ወቅት ያደረግነው ግንኙነት ነው ። ቀስተደመና አካባቢ የነበርን አባላትና ደጋፊዎች አቶ ብርሃነ መዋ ቤት እየተገናኘን ስለ ቅንጅት ዓለምአቀፍ አካሄድ እንወያይ ነበር ። በአንዱ ምሽት ውይይቱ አልቆረጥ ብሎ ሲንዛዛ “ቀጠሮ አለብኝ መሄዴ ነው” ብዬ ተነሳሁ ። እንድቆይ ቢያግባቡኝም እምቢተኛ ሆንኩ። ከማ ጋር ነው ቀጠሮህ ሲሉኝ የሰጠሁት መልስ የአንዳርጋቸውን የመረረና የፍቃደን ተቃውሞ አስነሳብኝ ። ዳዊት ዮሐንስን ሲልቨር ስፕሪንግ ስለቀጠርኩት መሆኑን ስነግራቸው ነው ያወገዙኝ ። በተለይ አንዳርጋቸው የነበረው ምሬት አይረሳኘም ። በመካረርና ኩርፊያ ስለማላምንና፣ የሰው ልጅ ህሊናና የዳኝነት ስሜት ስላለው ይሸነፋል ብዬ ስለማምን ከዳዊት ጋር ተገናኝቶ መከራከሩ ይጠቅማል በሚል የጓደኞቼን ውግዘት ንቄ ከዳዊት ጋር በላንጋኖ ሬስቶራንት ስንከራከር አመሸን ።

የዳዊትን የእረፍት ዜና ስለጥፍ ከብዙ የአማራ ብሄርተኛ ነን ባዮች ወጣቶች ከባህላቸው የራቀና አጉራዘለል ስድብ ያዘሉ መልእክቶችን አስተናግጃለሁ። የተቃውሟቸው መሠረት ወያኔን አገለገለ የሚል ነው ። እነዚህ ወጣቶች የማያውቁት ጉዳይ ግን መለስ ስታሊንን ሳያነብ ዳዊት ዪሐንስ ማርክሲስት የነበረ መሆኑን ነው። መለስ የእኔ እድሜና ክፍል እኩያ ነው። ዳዊት ደግሞ የሁለት ወይም ሶስት ዓመትና ክፍል ታላቃችን ነው ። የዋለልኝን የብሄሮች ጉዳይ ከኔና መለስ ቀድሞ ነው ያነበበው ። ዳዊት በወያኔ ተላላኪነት ሊወነጀል አይችልም። ወያኔም ሆነ ኦነግ የተመሩበትን አጠቃላይ የብሄረሰቦች አርነትና በፈቅዶ መዋሃድ ፌዴራሊዝም የሚያምን የጭቁን ብሄረሰቦች ጠበቃ ነበር ዳዊት ። በኤርትራ የሪፍረንደም ወይም ህዝበ ውሳኔ መብትም ቁርጠኛ የሆነ አቋም የነበረው ነው ዳዊት ። ከተማሪው ንቅናቄ ቀናት ጀምሮ ከዚህ እምነቱ ውልፊት ሲል አይቼውም ሰምቼውም አላውቅም። የኢትዮጵያን ዜጎች በእኩልነት በማሳተፍ ወደ ኢኮኖሚያዊ እድገት ያስወነጭፈናል ብሎ የሚያምን ታጋይ ነበር ዳዊት ።

የአማራ ብሄርተኛ ነን የሚሉ ወጣቶች ወያኔ በአማራ ላይ ላደረሰው በደል መሳሪያ ነበር ብለው ሊያወግዙት ቢሞክሩም፣ ዳዊት የአማራ ብሄርተኝነትን ንድፈሃሳባዊ መሰረት የጣለ ቀዳሚው የፖለቲካ አሰናሳይ ነበር። ቃለአብ በሚል የብእር ስም እአአ በ1992 ዓም በእምቢልታ መፅሄት ላይ በእንግሊዘኛ ባወጣው ፅሁፍ፣ አማራው ገዢ መደቦቹ በሰጡት የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ባዶውን ከሚኮፈስ፣ ከተሰቀለበት ደመና ወርዶና እኩልነቱን ተቀብሎ በአማራነቱ መደራጀት አለበት ብሎ ተከራክሯል ። በዚህም ክርክሩ በጊዜው ገናና በነበረው የኢትዪጵያ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ምሁር ተወግዟል። በቃለአብ የብእር ስም የፃፈውን ክርክር ለማንበብና ለመረዳት ትምህርቱም ሆነ ብስለቱ ሲኖራቸው፣ ዛሬ የሰደቡት ወጣት የአማራ ብሄርተኞች ይቅርታ እንደሚጠይቁት እምነቴ ነው። ክርክር ወዳዱ ዳዊት ዮሐንስ በመጨረሻ ሲሰናበተንም በክርክር መሆኑ፣ የሚደንቅ ነው። ያማረ ፣ የሰመረ አሟሟት ማለት እንዲህ ነው። ጠበቃው፣ እርሱ ዝም ብሎ እኛን ያናግረናል!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close