Connect with us

Ethiopia

ቤተልሄም ታፈሰ ከExodus እስከ LTV

Published

on

ከExodus እስከ LTV | ከአሳዬ ደርቤ

ከExodus እስከ LTV | ከአሳዬ ደርቤ

ቤተልሄም ታፈሰን የማውቃት EBS ቴሌቪዥን ላይ Exodus የሚል ፕሮግራም ጀምራ እነ ፓስተር ሐይሉ ዮሐንስን ስትሳደብ ነው፡፡ እናም ያኔ በጣም በሚያሳቅቅ ሁኔታ ስተገለማምጣቸው ችግሩ ያለው ከእሷ ሳይሆን ከእነሱ ይመስለኝ ነበር፡፡

ከዚያ ለረዥም ጊዜ ጠፍታ ከቆየች በኋላ በLTV ተከሰተች፡፡ ፕሮግራሟን እንደጀመረች አካባቢም እንግዶቿን ስታፋጥጥ የተመለከቱ ሰዎች ከBBC hardtalk አዘጋጅ ከSteven Sacker ጋር ሲያዛምዷት ነበር፡፡ እየቆየች ስትመጣ ግን ለጋነቷ እና ብሔርተኝነቷ ጎልቶ ይታይ ጀመር፡፡ የጠራቻቸውን እንግዶች በክብር ተቀብላ ያሏትን ጥያቄዎች ከመጠየቅ ይልቅ አንዱን በአድናቆት ሌላውን በንቀት መቀበሉ የዘወትር ተግባሯ ሆነ፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የምታቀርባቸው እንግዶች የሰዎችን ቀልብ የሚስቡ በመሆናቸው ብዙ ተመልካቾች አሏት፡፡ ጥያቄ ማቅረብ ባታውቅበትም እንደ’ነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያም፣ ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ፣ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ፣ ጌታቸው ረዳ፣ ሐጫሉ ሁንደሳ፣ በቀለ ገርባ፣ዳውድ ኢብሳ፣ ጃዋር መሃመድ፣ ኤርሚያስ ለገሰ፣ ኢንጂነር ይልቃል….. የመሳሰሉ አነጋጋሪ ሰዎችን ስለምትጋብዝ ፕሮግራሟን የሚመለከተው ሰው በርካታ ነው፡፡

ታዲያ የቤቲ ተጋባዥ እንግዶች በእሷ ዐይና ሲመዘኑ ‹‹ወዳጅ›› እና ‹‹ጠላት›› ተብለው የተፈረጁ ናቸው፡፡ እናም ወዳጆቼ የምትላቸውን ሰዎች ስትጋብዝ የሚወቀሱበትን ትታ የሚመሰገኑበትን ብቻ ትጠይቃለች፡፡ የምትጠላቸውን እንግዶች ስታቀርብ ደግሞ በስድብና በንትርክ ስታጥረገርጋቸው ቆይታ ታሰናብታቸዋለች፡፡ ወዳጆቿን ቃለ-መጠይቅ ስታደርግ በጥላሸት የተቀባ ሥማቸውን ለማጥራት ትንደፋደፋለች፤ ባላንጣዎቿን ስትጋብዝ ደግሞ አመድ ልትነሰንስባቸው ትሞክራለች፡፡

ከዚህ ውጭ ደግሞ ቤቲ ተገቢ ያልሆኑ የፌስቡክ አሉባልታዎችን ሰብስባ በመቅረብ የዓየር ሰዓቷን ማባከኗ የተለመደ መገለጫዋ ነው፡፡

ሐጫሉ ሁንዴሳን አቅርባ… ይሄ ‹‹የዚህ ዘፈንህ ግጥም እናና ዜማ የማን ነው?›› በማለት ፈንታ ‹‹አዲስ አበባ የማን ናት?›› እያለች ለማንም የማይጠቅም ጥያቄ ስትጠይቀው ነበር፡፡

የአብኑን ሊቀ-መንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔን ጋብዛ…. ክርስቲያን ታደለ በተናገረው ነገር ‹‹ሕዝቡን ይቅርታ ካልጠየቅህ›› ስትለው ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማሪያምን ወንበሯ ላይ አስቀምጣ ‹‹ደርግ በገደላቸው ባለሥልጣናት እጄ አለበተት ብለው ማመን ይኖርበዎታል›› እያለች ስታደርቃቸው ነበር፡፡

ሰራዊት ፍቅሬን ከማስታወቂያ ባለሙያነት ወደ ስኳር ኮርፖሬሽን አመራርነት አምጥታ ለአባይ ጸሐዬ መቅረብ ያለባቸውን ጥያቄዎች እየነሳች ስትመናቸክበት ነበር፡፡ ቴዎድሮስ ተሾመን ደግሞ ‹‹ጥበብን ገድለሃልና አድናቂዎችህን ይቅርታ ጠይቅ›› ስትለው ነበር፡፡

ትናንት ደግሞ ኢንጂነር ይልቃልን አቅርባ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስቴሩን የምትተቻቸው ስለምትቀናባቸው ይሆን? አምስት ፓርቲዎችን ማፈራረስህና የፓርቲ ገንዘብ መመዝበርህ የሚታወቅ ሆኖ ሳለ እሳቸውን ስትተች ትንሽ አይከብድህም?›› እያለች ስትሰድበውና ስትመክረው ነበር፡፡

ታዲያ የሚገርመው ነገር ቤቲ ካቀረበቻቸው እንግዶች መሃከል የሰደበችው እንጂ ያሸነፈችው አለመኖሩ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኦነግ አመራሮች እንኳን ጢባ ጢቤ ተጫውተውባት ወጥተዋል፡፡ (ወይም ደግሞ እንዲያሸንፏት ፈቅዳላቸውም ሊሆን ይችላል፡፡)

የሆነው ሆኖ ሃሳቤን ጠቅለል ሳደርገው በክብር የጠሩትን እንግዳ በስድብ አጥረግርጎ መሸኘት የጋጠ-ወጥነት እንጂ የጋዜጠኝነት መገለጫ ሊሆን አይችልም፡፡ ቤቴ ልሄም ግን ከኤክሲዶስ ጀምራ ስታካብተው የኖረችውን ‹‹ሰዎችን የማዋረድ ጥበብ›› እንደ ዋነኛ ብቃቷ በመቁጠር እያደር በመግዘፍ ፈንታ ስትከስምበት እያየናት ነው፡፡

እነ መዓዛ ብሩን ባዳመጥንበት ጆሯችን በዘረኝነትና በጥላቻ የተለከፈች ጋዜጠኛ ስሜቷን መደበቅ አቅቷት እንግዶቿን ስትወርፍ ማየት በጣም አድርጎ ያሳቅቃል፡፡ LTVም ቢሆን ይሄን የጋዜጠኛዋን ምግባር ማስተካከል ያልቻለበት ወይንም ደግሞ ያልፈለገበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡

በተረፈ ግን ከጋዜጠኛዋ በላይ ፂማቸውን ተከርክመው እና ሱፋቸውን ገጥግጠው የሚቀርቡላት እንግዶቿ ይገርሙኛል፡፡ እንዴት አንድ ጤነኛ የሆነ ሰው ሃሳቧን እንጂ ሃሳብህን እንዲትናገር ለማትፈቅድ ጋዜጠኛ ቃለ-መጠይቅ ሊደረግ ስቲድዮዋ ድረስ ይሄዳል? አይገርምም??

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪል አቋም አያንጸባርቅም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close