Connect with us

Ethiopia

ምሁራንና የኢትዮጵያ ፖለቲካ

Published

on

ምሁራንና የኢትዮጵያ ፖለቲካ | ከማዕረግ ጌታቸው

ምሁራንና የኢትዮጵያ ፖለቲካ | ከማዕረግ ጌታቸው

አንዳንዶቹ የኢትዮጵያ ምሁራን ሰለፈኛ ይመስሉኛል፡፡ ተራ ደርሷቸው ከሚመጣው ስርዓት ጋር ለመጠቀም የሚጠብቁ፡፡ በደረግ ጊዜ አንድ ትውልድ ሲጠፋፋ ዋናዎቹ ተዋናዮች ምሁር የሚባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሂሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ቤተ መንግሰት የገባው መኢሶን የሚሉት የየዶክተሮች ስብስብ በኢህአፓ ላይ ጥይት እንዲረከፈከፍ ለማዘዝ ወደ ኋላ የሚል አልነበረም፡፡ ሶሻሊዝም ልቦናቸውን የሰለበው የያኔዎቹ ልሂቃን ግደለው ዕሰረው ከሚል የተሸለ ሀሳብን ለሀገራቸው ለማዋጣት አልታደሉም፡፡ በዚህ ምክንያትም በሰፈሩት ቁና ሆነና ነገሩ እነሱም በጊዜ ሂደት በራሳቸው ሀሳብ ተለብልበው ሞቱ፡፡

ወታደራዊ መንግሰቱ ግን ከመኢሶንም በኋላ በድግሪ ላይ ድግሪ የተከናነበ ሰው ለማግኘት አልተቸገረም፡፡ ኢሰፓ ሲመሰረት ተራው የደረሳቸው አንዳንድ ምሁራን ከወታደራዊ መንግስቱ ጋር ወደፊት እያሉ ከመድረኩ ተሰየሙ፡፡ በመቶ ሽዎች የሚቆጠርን ወጣት በነጠቀን የቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ህመም ማግስት ዳንኪራ እያሰሙ ኢትዮጵያ ትቅደም አሉ፡፡ የኢህዴሪ ህገ-መንግስት ሲጸደቅም የኢሰፓን ያህል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ከወዴት ይገኛል እያሉ በቴሌቪዥን ጣቢያ ምስክርነት መስተጠት ጀመሩ፡፡ ይሁን እንጅ የወታደራዊ መንግስቱ ፀሐይ በመጥለቋ ከዚያ በላይ የተሳፈሩበት የጥቅም ባቡር ወደፊት መጓዝ የቻለ አልነበረም፡፡

እናም 1983 ዓ.ም በሚሉት የፖለቲካ ፌርማታ ላይ ግራ ተጋብተው ቆሙ፡፡ በበፊቱ ስርዓት ተገፍተናል ያሉ ጥቂት ምሁራንም ይህን ዕድል ለመጠቀም ወደፊት ተንደረደሩ፡፡ ከፊሎቹም ጓድ የሚለውን የደርግ ጭንብላቸውን አውለቀው ዶከተርና ፕሮፌሰር ነን እያሉ ስለመጣው የፖለቲካ ድል መመሰከር ወደዱ፡፡ የኢህዴሪን ህገ-መንግስት አርቀቅው እንዲህ ያለ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት ታይቶም አይታወቅ ያሉን ሰዎች 1987 ዓ.ም የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ሲጸድቅ ሽበት እንጅ ቃላት ለመጨመር አልታደሉም፡፡ በዚህ የተነሳም ኢህአዴግ ሀገር ሊያድን የመጣ መሲህ ነው ለማለት አላንገራገሩም፡፡

ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ ምሁራን ሰልፈኛ ናቸው፡፡ ከሚመጣው ስርዓት ጋር ተራ ደርሷቸው ለመጠቀም የሚቁነጠነጡ፡፡          ” ምሁሩ ” የተሰኘ መጽሐፍን ባለፈው አመት ለህትመት ያበቁት አለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) በግልጽ እናዳሰፈሩት የሀገራችን ምሁራን ፖለቲካችንን ከማዳበር ይልቅ ሲያቀጭጩት ኑረዋል፡፡ መንግስታትን ከማረም ይልቅ በርቱ እያሉ ኢትዮጵያን ከመከራ ወደ መከራ አሸጋግረዋል፡፡ እንዲህ ያለው እውነተ የትናንት ብቻ ሳይሆን የዛሬም ሀቅ ነቅ ነው፡፡ በድግሪ ላይ ድግሪ ጨምረናል የሚሉ አንዳንድ ሰዎች እንደ ምሁርነታቸው አሁን ያለውን ስርዓት ህጸጾች ለማረም ከመምከር ይልቅ ከፊት ታይቶ የመጠቀም ፋላጎታቸው ጸንቷል ፡፡

ከዚህ ቀደም ሌሎች አደረጉት ብለው የተጸየፉትን በዕውቀት መማገጥ እነሱ እንደ ስራ ቆጥረውታል፡፡ ይህ ደግሞ ሀገሪቱ አሁንም ከምሁራን ከመጠቀም ይልቅ የምሁራን መጠቀሚያ እንዳትሆን ያሰጋል፡፡ እንዲህ ያለ ሀሳብ ሳነሳ ሀገርን ማገለገል ከመንግስት ጋር መለጠፈ ነው ወይ የሚል ተሟጋች እንደማይጠፋ እገምታለሁ፡፡ በርግጥ ፖለቲካና ሀገርን መለየያት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ድንበር ግን በእኛ ሀገር ደብዛው ከጠፋ ቆይቷል፡፡ በደረግ ጊዜ የነበሩ ምሁራን ደርግን የደገፉት ኢትዮጵያን ለማዳን አልነበረም፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የነበሩ አደህሪ ኢህአዴግ ምሁርን ህወሓት መራሹን ኃይል በየመድረኩ ያሞገሱት ሀገራቸውን ሰለሚወዱ አይደለም፡፡ ዛሬ ላይ ተራው የደረሳቸው ምሁራንም ፖለቲካችንን የሚንቆለጳጵሱት ከራሳቸው ጥቅም አንጻር መሆኑ አያከራክርም፡፡

ይህ አይነት አካሄድ መንግስትን ያሰንፋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚመኙትን ገለልተኘ የሆነ ለመንግስት ምክር ሃሳብ የሚሰጥ ቡድን እንዳይፈጠር እንቅፋት ይሆናል። ኢትዮጵያም የሀሳብ መሃን እንደሆነች እንድትቀጥል ይፈቅዳል፡፡

ምሁርነት ሳይንሳዊ ትርጉም የአንድ ማኅበረሰብ የሀሳብ ቋት መሆን ማለት ነው፡፡ የእኛ ሀገር ምሁራን ግን ሃሳብ አፋላቂ ሳይሆኑ ሀሳብ ጠባቂ ናቸው፡፡ በየመገናኛ ብዙሃኑ አቶ እገሌ የተባሉ ምሁር የሚል ዘገባ ስሰማ ምን አይነት ሀሳብ አፍልቆ ለዚህ ማዕርግ መብቃቱ ግልጽ የማይሆንልኝም ለዚህ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ፖለቲካዋ እንዲዘምን ከተፈለገ አንዱና መሰረታዊው ጉዳይ አንዳንድ ምሁራንን ምሁር አንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

ትናንት የመጣንበት መንገድ ከዚህ ተቃራኒ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምሁራን ከፊሎቹ ለፖለቲከኞች ሲያጎበድዱ የቀሩት ተራ አልደረስ ብሏቸው ሲያምጹ ዘመነት አልፈዋል፡፡ ነገም በዚህ መንገድ ነው ማቅናት ያለብን? አይደለም፡፡ ስለዚህ የፈቃደ አዘዘን(ዶ/ር) ቋንቋ ልዋስና ፊደላዊያንን ወደ ምሁርነት ከፍ እንዲሉ ማደረግ ለሀገራችን ፖለቲካ የሚበጅ ተግባር ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close