Connect with us

Ethiopia

የጃዋር የባከኑ ካርዶች! | በጫሊ በላይነህ

Published

on

የጃዋር የባከኑ ካርዶች! | በጫሊ በላይነህ

የጃዋር የባከኑ ካርዶች! | በጫሊ በላይነህ

የክብር ዶ/ር ሼህ ሙሐመድ ሁሴን ዓሊ አልአሙዲ ከአንድ ዓመት ከአራት ወር እስር በኃላ ትላንት መፈታታቸው ሲሰማ ወዳጆቻቸው ብቻ ሳይሆኑ ጠላቶቻቸውም ደስ ተሰኙ፡፡ ለምን ቢባል የታሰረ መፈታቱና ከቤተሰቦቹ ጋር በሠላም መገናኘቱ በራሱ ሰው ለሆነ ፍጡር ሁሉ የሚያስደስት ነውና፡፡

ልብ በል!… ሼህ ሙሐመድ ማንም ወደኢትዮጵያ ፊቱን ባላዞረበት የ1980ዎቹ አስቸጋሪ ወቅት ደፍረው ገንዘባቸውን ይዘው ወደሚወዷት የትውልድ አገራቸው የገቡና ሥራ የፈጠሩ ፈርቀዳጅ ባለሃብት ናቸው፡፡ ከመንግሥት ቀጥሎ ከፍተኛ ሥራ የፈጠሩ፣ የአገር ኢኮኖሚ ሠርተው የደገፉ፣ በሥራቸው አንቱታን ያተረፉ ዓለም አቀፍ ባለሃብት ናቸው፡፡

ብሉምበርግ በቅርብ እንደዘገበው የሼህ ሙሐመድ ትልቅ ሐብት የሚገኘው በሲውዲን እና በሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ ነው፡፡ ሼሁ ዓለም አቀፍ ባለሃብት እንደመሆናቸው ዓመታዊ ትርፋቸውን በውጭ ምንዛሪ አስልተው ይዘው እብስ ማለት ከልካይ አልነበራቸውም፡፡ ግን ባለፉት 20 ዓመታት ሼሁ ዶላር ከማስገባት በስተቀር ዜሮ አምስት ሳንቲም ትርፍ ከኢትዮጵያ ወደውጭ ወስደው እንደማያውቁ በአንድ ወቅት በኩራት የገለጹት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በውጭ ምንዛሪ እጦት ለምትማቀቅ አገሬ፣ አገርህ ትልቅ ውለታ መሆኑን መቼም ለአንተ አልነግርህም፡፡

እናም እኚህ ብርቅዬ ባለሃብት ተፈቱ ሲባል እነጃዋር መሐመድ ጨርቃቸውን ጣሉ፡፡ በጣት በሚቆጠሩ ሰዓታት ከ12 በላይ ጸረ- አልአሙዲ ውግዘትና የይታሰር ማመልከቻ ለቀለቁ፡፡ አንድ ጊዜ የወርቅ ማዕድኑ ሰዎችን ጎድቷል፣ ሌላ ጊዜ የመለስና የበረከት፤ ቀኝ እና ግራ እጅ ነበሩ… የሚሉ ጥላቻ አዘል ክስና ፍርዶችን ማዥጎድጎድ ቀጠሉ፡፡

የጃዋር ሙሐመድ ህልም የታወቀ ነው፤ አሸማቅቆ ማስገበር!.. ከዚህ ቀደም ህወሓትን በመፍራት በአሜሪካ በድብቅ ቤት ውስጥ ተወሽቆ ፌስቡክ ላይ ተጥዶ ከሚውልበት አላቅቀው፣ በታላቅ ወግና ማዕረግ የነጻነት አየር እንዲተነፍስ የረዱትን እነአቶ ለማ መገርሳ እና ዶ/ር ዐብይ አህመድ ውለታ ረስቶ “የለውጡ መሐንዲስ እኔ ነኝ፣ የመደመር ካሌኩሌሽን የእኔ ነው” ከሚል መቀደዶች ጀምሮ እነዐብይ ገና መንፈቅ እንኳን ሳይደፍኑ “አገር መምራት አልቻሉም!” እያለ መዘባረቅ ጀምሮ ነበር፡፡ በኃላም አብረውት እፍ ይሉ የነበሩ ተከታዮቹ ሳይቀር በአንዴ ተገልብጠው መናደፍ ሲጀምሩ ፈጥኖ ወደሰገባው ለመግባት ተገደደ፡፡ ያው መሸብለል ልማዱ ነውና እነሆ በዚያው አንደበቱ እንደገና “ለውጡ መጨናገፍ የለበትም፣ ከለውጥ ኃይሎች ጎን ልንቆም ይገባል” እያለ ያወገዛቸውን መካሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

ጀዋር እንዲህ ነው፡፡ ሲፈልገው የቄሮን፣ ሲያሻው ኦሮሞን ሕዝብ ካርድ እየመዘዘ ማስፈራራት፣ ማዘዝ፣ ይቃጣዋል፡፡ ለዚህም ነው፤ እነዶ/ር ዐብይ በስንት ደጅ ጥናት ያስፈቷቸውን ሼህ ሙሐመድ የመፈታት መልካም ዜና ሰዓታት እንኳን ሳይሞላው እንደገና ይታሰሩ ለማለት ያላንገራገረው፡፡

ትላንት በቦሌ በክብር ገብተው የኦሮሞን ንጹሃን የጨፈጨፉ፣ ከ17 በላይ ባንኮችን የዘረፉ ወንጀለኞችን ጃዋር በሰዓታት ውስጥ የእርግማን መዓት ሊያወርድባቸው ቀርቶ “ኸረ በሕግ አምላክ!” የማለት ሞራል እንደሰማይ ርቆት ታዝበናል፡፡ ዛሬ አልአሙዲ ለምን ተፈቱ በሚል የአዞ እምባውን የሚያወርደው ለኦሮሞ ሕዝብ አስቦ አለመሆኑን ይኸው ቅሌቱ ሕያው ምስክር ነው፡፡

እርግጥ ነው፣ለ OMN ገንዘብ ሲለምን “የሼሁ ድርጅቶች አልረዱንም” በሚል ትልቅ ቀየሜታ እንደነበረው ይታወቃል፡፡ ይህን ሒሳብ ለማወራረድ ግን የሺዎች አባት የሆኑትን ሼህ ሙሐመድ ካልታሰሩ ሞቼ እገኛለሁ ማለትና መልካም ስማቸውን ማጥፋት ለእኔ ጨቅላነት ነው፡፡ አርቆ ማሰብ መሳን ነው፡፡

ጃዋር ሙሐመድ ሆይ፡- የለገደንቢ ሚድሮክ ወርቅን በተመለከተ በአንተና በመሰሎችህ ቅስቀሳ በመንግሥት ለጊዜው ተዘግቶ በአካባቢ ላይ ጉዳት ስለማድረስ፣ አለማድረሱ በባለሙያዎች እየተጠና ነው፡፡ በቦታው ግን አሁንም በባህላዊ መንገድ፤ ያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከለከለው “ሜሪኩሪ” በተሰኘ ኬሚካል ፍጹም ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ ወርቅ እየተመረተ ነው፡፡ ሚድሮክ ወርቅ ከተዘጋ በኃላም ዛሬ ወገኖቻችን በኬሚካል መጎዳታቸውና አካላቸውን ማጣታቸው ቀጥሏል፡፡ ግን በእናንተ እኩይ ዘመቻ ምክንያት የሚድሮክ ወርቅ በመዘጋቱ አገሪቱ በትንሹ በዓመት ታገኝ የነበረውን ከ 400 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማጣት ተገዳለች፡፡ ምንም እንኳን በባለቤቶቹና በበላይ አመራሮቹ መልካም ፈቃድ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ደመወዝ ባይቋረጥም በርካታ የሚድሮክ ወርቅ ሠራተኞች በሥራ ዋስትና ስጋት ውስጥ የወደቁት በእናንተ እኩይ ተግባር የተነሳ ነው፡፡ በዚህ ከባድ ዋጋ የሚከፍለው ደግሞ ቆመንለታል እያላችሁ በየደቂቃው የምትምሉለት የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡

እናም ጃዋር መሐመድ ሆይ፡- ነገር ሁሉ በር ዘግቶ ፌስቡክ ላይ እንደመለቅለቅ ቀላል አይደለም፡፡ ውሸት ደጋግመው ስለጻፉትም እውነት አይሆንም፡፡ በኦሮሞ ሕዝብ እየማሉ በመዛትም ማስገበር፣ ማንበርከክ የሚቻልበት የአፈና ጊዜ አልፏልና ወደቀልብህ ብትመለስ?

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያንጸባርቅም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close