Connect with us

Ethiopia

የአቶ በረከት የመጨረሻ ቃል | ፀጋው መላኩ

Published

on

የአቶ በረከት የመጨረሻ ቃል | ፀጋው መላኩ

የአቶ በረከት የመጨረሻ ቃል | ፀጋው መላኩ በድሬቲዩብ

አንጋፋው ኢህአዴግ በእርጅና እንቅልፍ ሲያንጎላጀጅ በህዝባዊ ማዕበል ተገፈትሮ አይሆኑ ሊሆን የመጨረሻው መጨረሻ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ውስጥ ውስጡን ተበልቶ ቀፎ ምስለ ቁመናው ብቻ ቀርቶ የነበረው ኢህአዴግ የፖለቲካ የተፈጥሮ ሞትን ለመሞት ከላይ ከላይ እየተነፈሰ ባለበት ሁኔታ አንድ ወሳኝ የፈውስ መድሀኒትን አገኘ፡፡ ይህ የመጨረሻ የፈውስ መድሀኒት ሆኖ የተገኘው የራስን አካል በራስ በራስ እየበሉ ከሞት ማምለጥ ነው፡፡

በቃ ምንም አማራጭ የለም፡፡ አንተ በህይወት መኖር ካለብህንና፤ በህይወት መኖርህም የእጅህን አንዱን ጣት ቆርጥመህ በመብላት የሚወሰን ከሆነ፤ እንደሰው ምን ታደርጋለህ? ጣትህን ቆርጥመህ በልተህ ቀሪውን ህይወትህን ታስቀጥላለህ ወይንስ ስለአንዱ አካለህ በመላ ህይወትህ ላይ የሞት ፍርድ ታስተላለፋለህ፡፡

አዎ ኢህአዴግንም የገጠመው ፈተና ይህ ነው፡፡ ራስን በልቶ መዳን ወይንም በራስ ላይ ሞት ፈርዶ እስከደዲያኛው ማሸለብ፡፡

ኢህአዴግ በስብሶ ሲሸትና ጠረኑ እየሰነፈጠ የህዝብን አፍንጫ ሲያሲዝ የገማውን አካሉን ከማስወገድ ይልቅ በተሀድሶ ስም ቀዝቃዘ ሻወር እየወሰደ ልብሱን ቀይሮ ሀገር ለመምራት ብዙ ጥሯል፡፡ ይሁንና ችግሩ ከልብስ ሳይሆን ከውስጥ ሆነና ራስን ለማዳን ራስን መብላት ግድ ሆነ፡፡

በመሆኑም በህይወት ለመኖር ራስን መብላት ብቸኛው አማራጭ የሆነበት ኢህአዴግ ራሱን መብላት ከጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡

ግንባሩ ራሱን በበላ ቁጥርም እለት እለት በህይወት የመቀጠል መድህኑን ዋስትና እያገኘ ሄዷል፡፡ ራስን እየበሉ መዳን ከባድ የፖለቲካ ፍልስፍና ቢሆንም፤ግን ደግሞ እየሆነ ነው፡፡

እናም በለውጡ ሂደት ውስጥ እንደ ሾላ ፍሬ ተራግፈው የወደቁት አቶ በረከት ስምኦንም አንዱ የኢህአዴግ ራስን በልቶ የማዳን መርህ መድሀኒት ሆነው በመገኘታቸው ተበልተዋል፡፡ አቶ በረከት አዲስ አበባ ቦለሌ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እስከ አፍንጫቸው በታጠቁ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው በዚያው ዕለትም ወደ በሀርዳር አምርተዋል፡፡ “በሀብት ብክነት ወንጀል እጠረጥራቸዋለሁ” ያለው የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ በረከትን በቁጥጥር ሥር በማዋል “ጓደኛህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ” እንደሚባለው በመቀሌው የህወሓት ጡረተኞች ምሽግ ላይ ከባድ የስጋት ፈተና እንዲደቀን አድርጓል፡፡

አቶ በረከት አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር ከማዋላቸው ቀደም ብሎ በነበሩት ጊዜያት ከለውጡ ማግስት በመንግስት አይነ ቁራኛ ጥብቅ ክትትል ሲደረግባቸው የነበሩ ሰው ናቸው፡፡ ለዚህም መነሻ ምክንያት ተደርጎ በምክንያትነት ሲጠቀስ የቆየው የአማራ ክልል መንግስት ኢንደዎውመንት ድርጅት በሆነው ጥረት ኮርፖሬት ውስጥ ለረዥም ዓመታት በቦርድ ሊቀመንበርነት በነበራቸው ኃላፊነት “ድርጅቱ ለምዝበራ ተጋልጦ ክስረት እንዲደርስበት አድርገዋል” በሚል ነው፡፡

አንዳንዶች “ምንው የአቶ በረከትን የ27 ዓመታት ሁሉ በኩሉሄ የስልጣን ፈላጭ ቆራጭነት ወደ ጎን ብላችሁ ጉዳያቸውን ከአንድ ድርጅት ምዝበራ ጋር ብቻ በማያያዝ የክፋት ታሪካቸውን አሳነሳችሁት” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

እርግጥ ነው አቶ በረከት በቀድሞው ብአዴን በአሁኑ አዴፓ ውስጥ በነበራቸው የተለያየ የኃለፊነት ደረጃዎች ድርጅቱን በመወዘወር ሰፊ ሥራን የሰሩ ሰው ናቸው፡፡ አቶ በረከት ከብአዴን እስከ ኢህአዴግ ብሎም እስከ ተለያዩ የሚንስትርነት ወሳኝ የሥልጣን ቁልፍ ቦታዎች ድረስ የሥልጣን ወንበራቸውን በመቀያየር ብዙ የፖለቲካ ሚና የተጫወቱ አንጋፋ ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡

ግዙፉን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በቦርድ ሰብሳቢነት ሰዘውሩት ኖረዋል፡፡ የፓርቲው ታማኝ ካድሬን መፈልፈል ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚፈለፈልም ብዙ አስተምረዋል፡፡

ኢህአዴግ የያዘው አስተሳሰብ አርጅቶ መለዋወጫው እንኳን አልገኝ ባለባቸው ጊዜያት አቶ በረከት እንዳመሉ ጠጋግነው የግንባሩን ሞተር ከሚያስነሱት ወሳኝ ድርጅታዊ መካኒኮች ነበሩ፡፡ ይህችን ድርጅታዊ የመካኒክነት ሙያቸውን ቁጭ ብለው የቀሰሙት ደግሞ ከሟቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እግር ስር ቁጭ ብለው ነው፡፡

አቶ መለስ ሞተሩ አርጅቶ ጭስ የበዛበትን ኢህአዴግ እንዴት ፈተው ሲገጥሙት እንደነበር ማንም የሚየያውቀው እውነታነው፡፡ አቶ መለስ ኢህአዴግ ሲታመም ቤት ዘግተው በህመሙና በፈውሱ ዙሪያ ጥራዝ ሰነድ አዘጋጅተው ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ እናም በዚያ ስብሰባ የግንባሩን ሞተር አውርደው ብትንትኑን በማውጣት በአዲስ መልክ እንዲገጠም ካደረጉ በኋላ ግንባሩ ቢያንስ በካይ ጭሱና የሚረብሸው ድምፁ እንዲቀንስ ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡

በትጥቅ ትግሉ ወቅት አቶ መለስ በፓርቲው አስተዳደራዊ ሥራ ውስጥ ተጠምደው ጊዜ የሚያጠፉበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በግንባር ጦርነቱ ሂደት ውስጥም የነበራቸው ሚና እጅግ ውስን ነበር፡፡ የአቶ መለስ ዋነኛ ትኩረት የተለያዩ የውይይት አጀንዳዎችን በፅሁፍ መልክ በማዘጋጀት ህወሀትን እንደዚሁም ኢህአዴግን እሳቸው በሚፈልጉት አቅጣጫ መምራት ነበር፡፡

እሳቸው አዘጋጅተው ራሳቸው አወያይ በሚሆኑባቸው በእነዚህ የጥናት ሰነዶችና መድረኮች በርካቶች ሲሸማቀቁና ሲባረሩ፤ አቶ መለስ በአንፃሩ እንደኮከብ እያበሩ የድርጅቱ አድራጊ ፈጣሪ የሆኑባቸው አጋጣሚዎችን እየተፈጠሩ ሄዱ፡፡ እናም አቶ መለስ በእንደዚህ አይነት ስብሰባዎች በሚኖሩት የሀሳብ መንሸራሸሮች ማን ምን እንደሆነ በሚገባ ያጠናሉ፡፡ አቶ መለስ ይህ ተግባራቸው የመጨረሻው ፈተና የገጠመው በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት በተፈጠረው የሀሳብ ልዩነት ከህወሀት መሰንጠቅ ጋር በተያያዘ ብቻ ነበር፡፡ ያችን ፈተና ጓዶቻቸውን በማባረርና በማሰር በአሸናፊነት የተወጡት አቶ መለስ ፤ከዚያ በኋላ ይህ አይነቱን የመካኒክነት ሥራውን አሳልፈው የሰጡት ለአቶ በረከት ነበር፡፡

አቶ በረከት ከአቶ መለስ ተገቢውን የፖለቲካ መካኒክነት ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ ይሄንኑ አሰራር እንዳለ ለመተግበር ኢህአዴግ ወይንም የቀድሞው ብአዴን የፖለቲካ ትኩሳት ሲያተኩሰው ዳማ ከሲያቸውንና መፍቻቸውን ይዘው ብቅ ማለት ጀመሩ፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በተለይ በኢህአዴግ ፅህፈት ቤት በነበራቸው ኃላፊነት ድርጅቱ በምን መልኩ አገዛዙን እያጠበቀ መቀጠል እንዳለበት ሰፊ የውይይት ሰነዶችን በማዘጋጀት በርካታ በፓርቲው ውስጥ የለውጥ ችቦን ለመለኮስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አባላትን ማሸማቀቁን ተያያዙት፡፡ በዚህ ወቅት በበርካታ የንቅናቄውና የግንባሩ አመራሮች ጥርስ ውስጥ የገቡት አቶ በረከት፤ ቀስ ብለው ስልታዊ ማፈግፈግ በማድረግ የጥናት ሰነዳቸውን ፊት ለፊት ከማቅረብ ተቆጠቡ፡፡ ከዚያ ይልቅ ያዘጋጁትን የውይይት ሰነድ የፀሀፊውን ስም ሳይጠቅሱ በጀርባ ልከው በበር ገብተው መወያየቱን መረጡ፡፡

“ጠርጥር “ ያሉት አንዳንድ የብአዴን አመራሮች “በጥናቱ ሰነድ ጭብጥ ላይ መወያየቱ ብቻ ሳይሆን የጥናቱ አቅራቢ ባለቤትስ ማነው?” የሚል የባለቤት ይበጅለት ጥያቄን ማንሳት ጀመሩ፡፡

ሆኖም አቶ በረከት አንድም ቀን “ሰነዶቹ በእኔ ተዘጋጅተዋል” ብለው አያውቁም፡፡ ሁኔታዎች በዚህ መልኩ በቀጠሉበት ሂደት የአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት አቶ በረከትን ለፖለቲካ ብርድ አጋለጣቸው፡፡ እናም ያ በድብቅ ሰነድ እያዘጋጁ የለውጥ ፈላጊ ሀይሎችን በየስብሰባው ሲመቱ የነበሩት ዘ ጎስት ማን አቶ በረከት መሆናቸው ተረጋገጠ፡፡ የዚህም ሚስጥር መዘርገፍ በተለይ በቀድሞው ብአዴን ውስጥ የነበሩትን የድርጅቱን የፖለቲካ አመራሮች እርስ በእርስ አባላ፡፡

በተለይ በአቶ ደመቀና በአቶ በረከት መሀልም ግልፅ የሆነ የጎራ አሰላለፍ የታየው በዚህ ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተለይም ከወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የተለኮሰው የአማራ ብሄርተኝነት ለአቶ በረከት መልካም ዜና አልነበረም፡፡ ይህ የአማራ ብሄርተኝነት ችቦ መለኮስ ጉዳይ አማራው ቀድሞ እንደነበረው ብአዴንን ከማጥላላት ይልቅ በንቅናቄው ውስጥ የለውጥ ሀይሎችን በመደገፍ ንቅናቄውን ወደ ህዝብ እቅፍ ውስጥ የማስገባት ሥራን ሰርቷል፡፡ ይህ አይነቱ ብኤዴንን የትግሉ አጋር የማድረግ ሥራ ሲሰራ የመጨረሻው ማጠቃለያ ምዕራፍ የነበረው አቶ በረከትንና አጋሮቻቸውን ከፓርቲው ጠራረጎ ማስወገድ ነበር፡፡ እናም አቶ በረከት በተነሳው የፓርቲው የፖለቲካ ማዕበል ተጠርገው መወገድ ግድ ሆነባቸው፡፡

አቶ በረከት የብአዴን አመራርነት መነሳታቸው ወይንም መባረራቸው የቀድሞው ብአዴን ወይንም አዴፓ ከስምና ከአርማ ለወጥ ባለፈ ንቅናቄው በለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን አንዱ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ተግባር ሆነ፡፡ እናም እነ አቶ ደመቀ መኮንን ከቀድሞው የፖለቲካ አካሄዳቸው ንስሀ ገብተው የፖለቲካውን የፅድቅ መንገድን ሲከተሉ አቶ በረከትንን እና ጓዶቻቸውን በይሁዳ የፍርድ ወንበር ላይ በማስቀመጥ ነበር፡፡

በዚሁ አጋጣሚ አቶ በረከት በዚህ ወቅት በቁጥጥር ስር ሲውሉ አንድ የታሪክ ግጥምጥሞሽም ተፈጥሯል፡፡ በምርጫ 97 የኢህአዴግ ኮከብ ተጫዋች የነበሩት አቶ በረከት፤ ከምርጫው ውዝግብ ማግስት ወይዘሪት ብርቱክን ሚደቅሳን ጨምሮ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ዘብጥያ እንዲወርዱ በማድረጉ ረገድ ወሳኝ የፖለቲካ ውሳኔን ከሰጡ አንኳር የኢህአዴግ ሰዎች መካከል አቶ በረከት አንዱ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከቀድሞው የገቢዎችና ጉምሩክ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ፋንታ የዓመታት እስር ጀርባ የአቶ በረከት እጅ እንደነነበረበት ብዙ ሲባል ቆይቷል፡፡

ዛሬ ነገሮች ተገለባብጠው ወይዘሪት ብርቱካን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ደግሞ ከ97 ምርጫ ማግስት በስደት ከነበሩበት ሀገር ተመልሰው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሀዲድ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አቶ መላኩ ፋንታም ከዓመታት እስር መማቅ በኋላ በነፃ ከመሰናበት አልፈው በጎንደር ህዝብ በተደረገላቸው የጀግና አቀባበል የሚሊዮን ብሮች መኪና ተበርክቶላቸዋል፡፡
በአንፃሩ ጊዜን ጊዜ እየወለደው ነገሮች ተገለባበጡና፡-

ያን ጊዜ በዚች ሀገር እጣ ፈንታ ላይ ፊርማቸውን ሲያኖሩ የነበሩት አቶ በረከት፣
ያን ጊዜ ቃላቸው ህግ የነበረላቸው አቶ በረከት
ያን ጊዜ የጥናት ሰነዶችን በእጅ አዙር ጣል በማድረግ በኢህአዴግ ውስጥ “አፋጀሽኝ” ቴአትርን የተወኑት አቶ በረከት
ዛሬ እጃቸውን ለካቴና ሰጥተዋል፡፡ ከፖለቲካው ገለል ብለው የእስር የፅሞና ጊዜን በማረፊያ ቤት ለማሳለፍ፤ ወደ ጣናዋ ዳር በሀርዳር ተወስደዋል፡፡ ጠቢቡ ሰለሞን ለሁሉም ጊዜ አለው እንዳለው ለአቶ በረከትም የዘመን ከፍታው ጊዜያቸው የቁልቁለት ዘመን መጀመሪያቸውን አንድ ብለው ተያይዘውታል፡፡

አሁን ሁሉም ነገር ተጠናቋል፡፡ ተውኔቱም አልቋል፡፡ መጋረጃውም ተዘግቷል፡፡ ቴአትሩም ከመድረክ ወርዷል፡፡ አዲስ ምዕራፍ የማይከፈትበት አሮጌው ምዕራፍ ተዘግቷል፡፡

ሰዎች አንድን የህይወት ምዕራፍ አጠናቀው ወደሌላኛው ምዕራፍ ሲሸጋገሩ በዚያ የህይወት አንጓ አንድ ቃል ይተነፍሳሉ፡፡ ይህች የመጨረሻዋ እስትንፋስ የእነሱን እውነተኛ ስሜት የምትገልፅ “የመጨረሻ ቃል ትባላለች” ፈረንጆቹ ላስት ወርድ ይሏታል፡፡

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አይሁዶችን በግፍ ከጨፈጨፉት ጀርመናዊያን መካከል አንደኛው ጀርመናዊ በደቡብ አሜሪካ አርጀቲና ለዓመታት ተደብቆ ሲኖር በስተመጨረሻ በሞሳድ በተደረገ ክትትል አንድ ቀን ሌሊት በአርጀንቲና ፖሊሶች ቤቱ ተከቦ እጁን እንዲሰጥ በሜጋፎን የድምፅ ማጉያ ተጠየቀ፡፡ ሥራውን የሚያወቀው ይህ ጀርመናዊ የናዚ ፓርቲ አባል፤ የመጨረሻው ለሚስቱ የተናገረው የስንበት ቃል “ልጄን አደራ” የሚል ነበር፡፡

በእርግጥም አቶ በረከት በዚያች የመጨረሻዋ መጀመሪያ ሰዓት እጃቸውን ለካቴና ሲሰጡ ምን ብለው ይሆን?
ታላቁ መፅሀፍ እንደሚነግረን ኢየሱስ መስቀል ላይ ሆኖ ሲያጣጥር ከመሞቱ በፊት እንደተናገራት አንዲት የመጨረሻ ቃል “ተፈፀመ” የሚል ይሆን? ወይንስ እንደ ድምፃዊት ብፅኣት ስዩምና እንደዚያ ጀርመናዊው የናዚ ፓርቲ አባል “ልጄን አደራ” የሚል

የመጨረሻ የጭንቅ የስንበት ቃል ይሆን?
ለማንኛውም ብፅዓት ስዩም ፡-
ወልደህ እየው ብሎ ወላጅ የመረቀው
ለልጅ ሲንሰፈሰፍ ያኔ ነው የሚያውቀው
እርብትብት ከንፈሩ ያንገቱ ስር ሽታ
ከሞትም ያድናል እንኳን ከበሽታ…. ብላ ባዜመችው ልብ የሚበላ ዜማ እንስነባበት፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close