Connect with us

Africa

የሻዕቢያው ጀኔራል እንደምን ከረሙ…?!

Published

on

የሻዕቢያው ጀኔራል እንደምን ከረሙ…?! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የሻዕቢያው ጀኔራል እንደምን ከረሙ…?! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

የኢሳይያስ አፈወርቂ ቀኝ-እጅ በመኖሪያቤታቸው በራፍ ላይ የደረሰባቸው ጥቃት ቀላል አልሆነም፡፡ዛሬም ከሚታከሙበት ሀገር ስለመመለሳቸው አልታወቀም፡፡ ሚስታቸው ‹በአንገቴ ገመድ ይገባል እንጂ ባሌ ወደ ኤርትራ አይመለስም› ብላለች፡፡ኤርትራዊው ጀኔራል፣ ስብሃት ኤፍሬም በስተርጅና ቆስለዋል፡፡

ጀኔራሉ ባሳለፍነው ዲሴምበር 19-2018 በጥይት ጥቃት ከደረሰባቸው በኋላ ወደቁ፡፡ በግቢያቸውም ኡኡታና ዋይታ እንደነበር የቀድሞው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት የአካባቢው ሰዎች ነገሩኝ ብሎ ጽፏል፡፡ወዲያው ወደ ኦሮታ ሆስፒታል የተወሰዱ ቢሆንም ቁስላቸውን በዘላቂነት ለማከም ግን ኤርትራ ውስጥ ያሉ ተቋማት ብቁ ሆነው አልተገኙም፡፡ባለቤታቸው ሩት ኃይሌ፣ የጀኔራሉ ቁስል እንዲያገግም ወደ አቡዳቢ እንዲሄዱ አደረጉ፡፡ከቀናት በኋላም ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ወደ አቡዳቢ ተሻግረው የክፉ ቀን ወዳጃቸውን ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬምን ጎብኝተዋቸዋል፡፡

ግድያ ሞካሪው ማነው?

የኤርትራ መንግሥት ስለጥቃት አድራሹ ያለው ነገር የለም፡፡ እንኳን ስለጥቃት አድራሹ፣ጥቃት ስለመድረሱም አልተናገረም፡፡ሆኖም፣በሻዕቢያ ባልሥልጣናት ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ፈጣን አስተያየት በመስጠት የሚታወቁት በጃፓን የኤርትራ አምባሳደር እስጢፋኖስ አፈወርቂ ‹‹ ስብሃት ከሕመሙ ይፈወስ ዘንድ እመኝለታለሁ፤ይህ አሳፋሪና የፈሪ ተግባር ግን መወገዝ አለበት›› ብለዋል፡፡በርግጥ ኤርትራን በምትመስል ሳር ቅጠሉ ሁሉ በአንድ እዝ ስር ባለባት ሀገር፣የፕሬዚዳንቱን የቅርብ አጋርና የቀድሞውን የመከላከያ ሚኒስትር ለመግደል መሞከር ነፍስን አስይዞ መደራደርን የሚጠይቅ ጀግንነት እንጂ፣አምባሳደሩ እንዳቀለሉት የፈሪ ተግባር አይመስልም፡፡

የሆነው ሆኖ ጀኔራል ስብሃት ፊታቸውንና ጭንቅላታቸውን ተመትተዋል፡፡እንደ ፕላውት ዘገባ ከሆነ፣የጥቃት አድራሹ ሽጉጥ አንድ ጊዜ ተኩሳ መክሸፏ በጀ እንጂ ሰውዬው ምናልባትም በሕይወት ላይገኙ ይችሉ ነበር፡፡ይህንን የግድያ ሙከራ የፈጸመው ግለሰብም ታስሯል፡፡

ይህ ሰው ወታደር እንደሆነ ተገልጹዋል፤በጀኔራሉት ላይ ቂም የቋጠረ መሥመራዊ መኮንን!!ጀኔራሉ፣ ‹‹ወዳጆቻችንን ያሳሰሩ፣የኤርትራን ለውጥ ያጨናገፉ፣ የኢሳይያስን የግፍ አገዛዝ ያራዘሙ ናቸው›› ብሎ ያመነ ኤርትራዊ ወታደር የፈጸመው ስለመሆኑ ታውቋል፡፡

በርግጥም ወዲ ኤፍሬም በታችኛው የወታደሩ ክፍል ቂም ቢያዝባቸው አይደንቅም፡፡በ2013 (እ.ኤ.አ) በኤርትራ ተሞክሮ የነበረውን የመንግሥት ፍንቀላ እንቁልልጭ ብለው ያከሸፉት እኒህ ጀኔራል ናቸው፡፡
‹‹ኦፕሬሽን ፎርቶ ››

ሰኞ ማለዳ ፌብረዋሪ 21-2013፣ከደቀመሐሪ ተነስቶ ወደ አስመራ ያመራው የኤርትራ ሠራዊት 12 ታንኮችን ይዟል፡፡ሌሊት የተጀመረው ጉዞ ረፋድ አራት ሰዓት አስመራ ደረሰ፡፡ ሶስቱ ታንኮች ወደ አውሮፕላን ማረፊያ አቀኑ፡፡ቀሪዎቹ ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ሄዱ፡፡100 የሚሆኑ ወታደሮች የኤርትራ ቴሌቭዥን የሚገኝበትን የፎርቶ ሕንፃ ከበቡ፡፡የጣቢያውን ሠራተኞች በሙሉ በአንድ ክፍል ታጎሩ፡፡

ከዚያ የኤርትራ ቴሌቭዥን ሥራአስኪያጅ አስመላሽ አብርሃ በአማጽያኑ ወታደሮች የተዘጋጀውን መግለጫ እንዲያነብ ተገደደ፡፡የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣የተሰደዱ ኤርትራዊያን እንዲመለሱና የ1997ቱ ረቂቅ ሕገመንግሥት እንዲተገበር የሚጠይቁትን ዓረፍተነገሮች ካነበበ በኋላ የቴሌቭዥኑ ሥርጭት ተቋረጠ፡፡በሥርጭት መቆጣጠሪያው ላይ የነበሩት የአቶ ኢሳይያስ ታማኞች ሞገዱን ቆረጡት፡፡

አማጽያኑ ‹‹አቶ ኢሳይያስ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ከክልል አስተዳዳሪዎች ጋር ለስብሰባ ተቀምጠዋል›› የሚል መረጃ ደርሷቸው ነበር፡፡በርግጥም መረጃው ልክ ነበር፡፡ስብሰባው ሊካሄድ የነበረው በዚሁ ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ይሁን እንጂ አቶ ኢሳይያስ ሁሌም እንደሚያደርጉት መጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የስብሰባ ቦታውን ቀይረው በጽ/ቤታቸው አደረጉት፡፡

ፕሬዚዳንቱ ስብሰባውን አቋረጡትና በቢሮአቸው ውስጥ ሆነው በመከላከያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ እየተከናወነ ያለውን ነገር በተገጠመላቸው ካሜራ መከታተል ቀጠሉ፡፡የዚህ ኦፕሬሽን መሪ በቅጽል ስሙ ወዲ አሊ እያሉ የሚጠሩት፣ኮሎኔል ሰዒድ አሊ ነው፡፡ይህ መኮንን ከኢትዮጵያ ጋር በነበረው ውጊያ በአሰብ በኩል የነበረውን ጦርነት የመራና እነርሱ ጀግና አድርገው የሚጠሩት ወታደር ነው፡፡የኮሎኔል ሰዒድ ታዛዦች ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ቀውጢ አደረጉት፡፡

ፕሬዚዳንቱ ጉዳዩን በሽምግልና ለመፍታት ወሰኑ፡፡ የሜካናይዝድ ጦር አዛዡን ኮሎኔል ተስፋይ መኮንንንም እንዲደራደር ወደነ ኮሎኔል ሰዒድ ላኩት፡፡ሆኖም ገና ብቅ እንዳለ፣ኮሎኔል ተስፋይ ተመታና ወደቀ፡፡ፕሬዚዳንቱ ይሄኛው እድላቸው እንደከሸፈ ተገነዘቡ፡፡ሌላ አማራጭ እያሰቡ ባለበት ሰዓት፣ኮሎኔል ሰዒድ የፕሬዚዳንቱ ሕንፃ እንዲደበደብ አዘዘ፡፡

ወዲያው ለኢሳይያስ ባላቸው ታማኝነት የሚታወቁ ሁለት ጀኔራሎች ወደ አማጽያኑ ተልከው መጡ፡፡ጀኔራል ስብሃትና ኢዮብ!! ስብሃት ተናገሩ፡፡‹‹ዓላማችሁንና እቅዳችሁን ሙሉበሙሉ እደግፋለሁ፡፡እኔም እንደናንተ ብዙ ቅሬታ አለኝ፡፡በሰማዕታቱ አጽም እምልላችሁዋለሁ ይህንን ጉዳይ ያለምንም ደም መፋሰስ እንፈታዋለን፡፡አንድም ወታደር ሳይታሰርና ሳይገደል ያሰባችሁት ነገር እንዲፈጸም ከጎናችሁ እቆማለሁ›› አለ፡፡አማጽያኑ አመኑት፡፡

ጀኔራሉ ከአሁን በፊትም ለዘብተኛ አቋም እንዳላቸውና በኢሳይያስ አገዛዝ እንደማይደሰቱ ተደጋግሞ ይነገር ስለነበር የሚሏቸውን አለማመን አይችሉም ነበር፡፡ ሆኖም የፎርቶ ኦፕሬሽን መሪ ኮሎኔል ሰዒድ የስብሃትን ልመና አልተቀበለም፡፡ጭፍራዎቹ ለጀኔራሉ ልመና እጅ ሲሰጡ እርሱ እራሱን ገደለ፡፡

መንግሥትን ለመፈንቀል ከሌሊት ጀምረው የተጓዙት ወታደሮች ተበታተኑ፡፡ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬምም ከያሉበት እየለቀሙ አሰሯቸው፡፡፡ወታደሮቹም እነሆ ላለፉት አምስት ዓመታት የት እንዳሉ አይታወቅም፡፡

‹‹ጀኔራል ስብሃት በነዚህ ጓዶቻቸው ላይ በፈጸሙትን ነገር መስመራዊ መኮንኖች አቂመዋል፤ የግድያ ሙከራውን የፈጸመው ሰው ከዚህ ክፍል የወጣ ሊሆን ይችላል››የተባለውም ከዚህ የተነሳ ነው፡፡
‹‹ወዲ ሹቕ ጀኔራል ››

ኤርትራዊው ደራሲና ሰላይ ተስፋዬ ገብረአብ፣‹‹ተግባቢና የማይኮፈሱ፣ እንደ ጓደኛ የሚያወጉ ትሁት ሰው ናቸው፤ሐሳባቸውንም አደራጅተው መግለጽ ያውቁበታል›› ሲል ይገልፃቸዋል፤ጀኔራል ስብሃትን!በርግጥም ጀኔራሉ በዚህ እንደማይታሙ ይነገራል፡፡በሳህል ዘመናቸው ብዙዎችን ማሳመን የቻለ፣ዲያስፖራን ለሻዕቢያ ያሰለፈ አንደበት ነበራቸው፡፡ ኤርትራዊው ፕሮፌሰር በረከት ሀብተስላሴ፣‹‹Wounded Nation›› በሚለው መጽሀፉ እንዳስነበበን፣እርሱ ከሚኖርበት ቦሎኛ (ጣሊያን) ወደ ኤርትራ በረሃ ያመጣው የስብሃት ኤፍሬም ‹‹የማግባባት ችሎታና፣የማሳመን ቴክኒክ›› ነው፡፡

ይህንን የስብሃትን ተሰጥኦ አብዛኞቹ ታጋዮች የከተማ ልጅ በመሆኑ ያገኘው እንደሆነ አድርገው ያዩታል፡፡ በርግጥ ጀኔራሉ የተወለዱት አስመራ ውስጥ ባርዳ በተባለው መንደር ውስጥ ነው፡፡ በ1964 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርቱን ትቶ፣ሳኅል ሲወርድ 21 ዓመቱ ነበር፡፡ቀጫጫና ሕፃን ልጅ ይመስል የነበረው ስብሃት፣ትግሉን እንዲቀላቀል አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ሆኖም አቶ ኢሳይያስ ከጀብሃ ገንጥለው ያቋቋሙት ‹‹ሰልፊ ናጽናት›› የተባለው አንጃቸው ሰው ይፈልግ ስለነበር፣ወዲ ኤፍሬም በቀላሉ ተቀላቀለ፡፡በኋላም ሻዕቢያን ነፍስ ከዘሩበት ታጋዮች መሀል አንዱ ሆነ፡፡የኢሳይያስን ‹ጠላቶች› በማደንም የተዋጣለት ታማኝ ሆነ፡፡ በተለይ መንካዕ በሚል የተመነጠሩትን የኢሳይያስን ተቃዋሚዎች በማፈን ዋነኛ ተባባሪ እንደነበር ይነገራል፡፡

ቀጫጫ ተክለ ሰውነት፣አጭር ቁመና፣ምጥጥ ያለ ፊት፣የነበረው ታጋዩ ስብሃት ቀልድ አዋቂና ነገርን አዋዝቶ ማቅረብ የሚችል እንደነበር ይወራለታል፡፡ይህንን ሁኔታውን ያዩት የትግል ጓዶቹም፣‹‹ወዲ ሹቕ ጀኔራል ›› ሲሉ ይጠሩታል፤ከተሜው ጀኔራል እንደማለት!!

መንካዕና ስብሃት

መንካዕ የሌሊት ወፍ የሚል ትግርኛዊ አቻ አለው፡፡ ቃሉ በሻዕቢያ የትግል ዘመን ዝነኛ ነበር፡፡ ያኔ ሻዕቢያ ከአባቱ ጀብሐ አምልጦ ሲወጣ ከወላጁ የባሰ አምባገነን መሆኑ ያሳሰባቸው፣ የትግል ሒደቱ ኢዲሞክራሲዊ መሆን ያስጨነቃቸው ምሁራን እዛው ሳዋ ሌሊት ሌሊት እየተሰባሰቡ መላ መምታት ጀመሩ፡፡ ወቅቱ 1973 (እ.ኤ.አ)ነበር፡፡

ይህንን ታሪክ በሚገባ ያስነበበው ግዛቸው አበበ፣‹‹ቅርምት በዘመነ ግንባር›› በሚለው መጽሐፉ እንዳስቀመጠው፣የመንካዕ አባላት ጭንቀት፣የድርጅቱና የኢሳይያስ አምባገነናዊነት ትግሉን ያራዝመዋል የሚል ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ሻዕቢያን በቀዳሚነት ከተቀላቀሉ ሴቶች መካከል ደሀብ ተስፋጽዬ እና አበራሽ መልኬ፣በጥሩ ሐኪምነቱና በድንቅ አዋጊነቱ የሚታወቀው ዶክተር ኢዮብ ምጽዑ፣በማደራጀት አቅሙና በጠንካራ አቋሞቹ የሚወደሰው አብርሃም ተወልደ፣ከአሜሪካ ወደ ሳህል ለኤርትራ ነፃነት ብሎ የመጣው ጴጥሮስ ዮሃንስ፣ ኢሳይያስ አፈወርቂን፣‹አንተ ለስልጣን ስግብግብ ነህ፤ስስታም ነህ› ብሎ በድፍረት የተናገረው መብርሀቱ ወልዱ፣የናዚ ወታደራዊ ምስጢሮችን /enigma codes/ ሳይቀር አብጠርጥሮ ይበታትን የነበረው ዓረፋይኔ ተስፋጋብርና ሌሎች ተመሳሳይ አቋም የነበራቸው ታጋዮቸ፣ሌሊት ሌሊት ውይይት ማድረግ ቀጠሉ፡፡በመጨረሻም የሌሊቱ ‹አድማ› ተደረሰበት፡፡እነኢሳይያስ እነዚህን ምሁራን መንካዕ ሲሉ ጠሯቸው፡፡ እናም ረሸኗቸው፡፡

በዚህ የመረሸን ተግባር ላይ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩት ድሮም ዘንድሮም ለአቶ ኢሳይያስ ባላቸው ታማኝነት የሚታወቁት ስብሃት ኤፍሬም ናቸው፡፡‹መንካዕ› በሚል ፍረጃ ስለገደሏቸው ታጋዮች በ1989 (እ.ኤ.አ) በሎሳንጀለስ ከዳያስፖራዎች የተጠየቁት አቶ ኢሳይያስ፣‹‹እርሱን በፍርድቤት ስንከሰስ እንናገራለን›› ማለታቸውን የቀድሞው የሻዕቢያ ታጋይና በአሁኑ ወቅት በጸረ-ሻዕቢያ አቋሙ የሚታወቀው ፕሮፌሰር በረከት ከላይ በጠቀስሁት መጽሐፉ ውስጥ ተርኮታል፡፡

ፈንቅል ፈንቃዩ ስብሃት
ሻዕቢያ በበረሃ ዘመኑ ምፅዋን ለመያዝ ያደረገውን ግብግብ ያህል ውጊያ እንዳላካሄደ ይገለፃል፡፡አንዳንድ ፀሀፊዎች እንደሚሉት ሻዕቢያ ተዋግቶ ያስለቀቃት ብቸኛ ከተማ ምጽዋ ነች፡፡በምጽዋ ጦርነት ከመክፈቱ በፊት ለ18 ወራት ያለምንም ውጊያ ሙሉ ዝግጅት አደረገ፡፡ውይይት፣ ጥናትና ወታደራዊ ንድፍ ተደርጎ የካቲት 1 ሌሊት ለየካቲት 2 አጥቢያ በ1982 ዓ.ም፣ ምጽዋ እንድትወረር ተደረገ፡፡ ዘመቻው ‹ፈንቅል› የሚል ስያሜ ተሠጠው፡፡

በምፅዋ ከአብዮታዊ ሠራዊት ጋር ለሚደረገው ውጊያ ሻዕቢያ ያለ የሌለ ኃይሉን አዘመተ፡፡ ሰባ ያህል T-55 ታንኮች፣ አራት የአየር መቃወሚያ ሻለቆች፣ ሦሥት መድፈኛ ሻለቆች፣ አምስት እግረኛ ብርጌድ፣ አንድ ኮማንዶ ብርጌድ፣ ሁለት ሜካናይዝድ ብርጌድ፣ በሦስት አቅጣጫ ግዳጃቸውን እንዲወጡ ተደረገ፡፡

በሰለሙና፣ በውቅሮና በሸኢብ ግንባሮች ጥቃት ከፈቱ፡፡ ውጊያው እስከ የካቲት 9 ቆየ፡፡ ከአፍአቤት የተነሳው የሻዕቢያ ሃይል የምጽዋን ወደብ ተቆጣጥሮ ወደ አስመራ የሚወስደውን መንገድ ቆረጠ፡፡ 17ሺህ የመንግሥት ወታደሮችን ገደለ፣ማረከ፣ አፈነ፡፡ ይህ ድል ሻዕቢያ የመንግስትን ሠራዊት አቅም ያሸመደመደበትና የደርግን ውድቀትም የአደባባይ ምስጢር ያደረገበት ሆነ ፡፡ይህንን የፈንቅል ዘመቻ የመራው ፣ የያኔው ወታደራዊ ክንፍ ሃላፊ የአሁኑ ቁስለኛ ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬም ነው፡፡አስመራ ከገቡ በኋላም፣‹‹ስለበረሃ ዘመኑ ሲያወራ ቀድሞ ወሬውን የሚያሟሸው በምጽዋ የጦርሜዳ ውሎው ነው›› ይላሉ ጀኔራሉን የሚያውቁ ሰዎች፡፡

‹‹አማራ ውጊያ አይችልም››
ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬም፣‹‹ደርግን እንዴት አሸነፋችሁት›› ተብለው ሲጠየቁ፣‹‹አማራ ውጊያ ስለማይችል›› የሚል ምላሽ እንደሰጡ፣‹‹The Ethiopian Revolution›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ አስነብበውናል፡፡ በርግጥ ለሻዕቢያ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያ ማለት አማራ ነች፤ሲዋጉ የኖሩትም ከአማራ ቅኝ ገዥዎች ጋር እንደሆነ አቶ ኢሳይያስም ሆኑ ሌሎቹ ባለሥልጣናት ደጋግመው ተናግረውታል፡፡

አቶ ግዛቸው አበበ ከላይ በገለጽሁት መጽሐፋቸው ሻዕቢያዎች አማራን ማዕከል በማድረግ ኢትዮጵያን ማፈራረስ የሚል አጀንዳ እንዳላቸው ሲያስነብቡ‹‹ኢትዮጵያዊ በሙሉ አማራ ብቻ እንደነበር ተደርጎ ይቀርባል፡፡በደልን ለመግለጽ አማራ ገደለው፤አማራ አሰረው፤አማራ ለስደት ዳረገው፣አማራ ደፈራት፣አማራ ገዛን ወዘተሲባል ይሰማል፤ድልን ለመግለጽ አማራ ማረክሁ፣አማራ ገደልሁ፣አማራ አባረርኩ፣ እየተባለ ወሬው ይቀጥላል›› ብለዋል፡፡እናም ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬም አማራንና ኢትዮጵያን አብዝተው ከሚጸየፉ የሻዕቢያ መሪዎች መካከል መሆናቸው አይገርምም፡፡

በ1990 ዓ.ም ኢትዮጵያ ላይ ወረራ ሲፈጸምና እልፍ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ሲያልቁ፣እኒህ ጀኔራል የኤርትራ መከላከያሚኒስትር ነበሩ፡፡ጦርነቱ ከመካሄዱ በፊት ይደረጉ የነበሩ የሁለቱ ሀገራት ኮሚቴ ስብሰባዎችንም፣ከኤርትራ በኩል የነበረውን የመሩት እርሳቸው ነበሩ፡፡አዲስ አበባ ላይ ለሰላማዊ ውይይት የኢትዮጵያን የጦር አዛዦች በጊዮን ሆቴል አስቀምጠው፣በሽራሮና ባድመ በኩል ኢትዮጵያን እየወረሩ እንደነበር ብዙ ሰዎች ጽፈዋል፡፡

ከድል በኋላ የተሸነፈው ስብሃት፤

ጀኔራሉ በበረሃ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ደማቅ ታሪክና ገድል ቢኖራቸውም ከግንቦት16- 1983 ወዲህ ግን ተሸንፈዋል፡፡የደርግ ታንክና መድፍ ያልማረካቸው ስብሃት ኤፍሬም፣ለአቶ ኢሳይያስ ባሕርይ እጅ ሰጥተዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ በሹመትና በሽረት ባለፉት 27 ዓመታት ያንገላቱትና ያንከራተቱት ሰው ከስብሃት ውጭ ያለ አይመስለኝም፡፡

በ1983 ዓ.ም የከተማ ልጅ ነህ ብለው የአስመራ ከንቲባ አደረጓቸው፤ ወዲያው የፋርማሲ ትምህርት አለህ ብለው የጤና ሚኒስትር አደረጓቸው፡፡(ጀኔራል ስብሃት የፋርማሲ ትምህርታቸውን አቋርጠው በረሃ የወረዱት ገና ሁለተኛ ዓመት ላይ እያሉ ነው፡፡21 ዓመት በሳኅል ቆይተው ሥልጣን ሲገኝ ግን ይቺ የሁለት ሴሚስተር ሥልጠና ስብሃት ኤፍሬምን የጤና ሚኒስትር አድርጋቸዋለች)፡፡እንደገና በ1985 ዓ.ም ከንቲባነትንም ጤና ሚኒስትርነትንም ደርበው እንዲይዙ አደረጓቸው፡፡ዓለም ላይ የዋና ከተማው ከንቲባ የጤናሚኒስትር ሆነው ያገለገሉት እዚህ አፍሪቃ ቀንድ ኤርትራ በተሰኘች አገር ላይ ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ቀጥለውም የመከላከያ ሚኒስትር ሆኑ፡፡አሁን ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር ናቸው፡፡

እናም ሺህዎችን አንቀሳቅሰው፣ጦር መርተው አስመራ የገቡት ጀኔራል ስብሃት ኤፍሬም ከ1983 ግንቦት ወዲህ ሥራቸው ለአለቃቸው መላላክ ሆነ፡፡በልብ ወዳጆቻቸው ላይ ጨክነውም የአቶ ኢሳይያስን ተልዕኮ በመፈጸም፣የትግል ጓዶቻቸውን አሰሩ/ለእስሩም ተባባሪ ሆኑ፡፡ለዚህም ከላይ የጠቀስሁት የ2013ቱ የመንግሥት ፍንቀላ ሙከራና G-15 የተሰኘው የለውጥ ንቅናቄ ይጠቀሳል፡፡

G-15 እና ስብሃት ኤፍሬም፤

ከ199ዎቹ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት በሻዕቢያ ውስጥ አለመግባባት ተከሰተ፡፡ ‹‹ያካሄድነው ጦርነት ተገቢ አልነበረም፤ቃል በገባነው ልክ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማንበር አለብን…››የሚል ቡድን በአንድ በኩል ቆመ፡፡ ቡድኑ ከአስመራ ወጣ ባሉ ቦታዎች መኪና ውስጥ፣እና በተለያዩ ምስጢራዊ ቦታዎች ውይይቶችን ያደርግ ነበር፡፡በነዚህ ውይይቶች ላይም ገና ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ ስብሃት ኤፍሬም እንደነበሩ፣ፕሮፌር በረከት ጽፏል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ የሻዕቢያ አመራሮች የያዙትን አቋም ከተማው ላይ በሚታተሙ ጋዜጦች ላይ ማውጣት ቀጠሉ፡፡ይሁን እንጂ እንቅስቃሴውን ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ደረሱበት፡፡ እነዚህን ባለሥልጣናት እና ሐሳባቸውን ያሰራጩ የነበሩ ጋዜጠኞችን ሰብስበውም አሰሩ፡፡ይህ ታሳሪ የሻዕቢያ ክንፍ፣ ‹ቡድን-15› ተብሎ ይጠራል፡፡ 15 የባለሥልጣናቱና የጋዜጠኞቹ ቁጥር ነው፡፡

ፕሮፌሰር በረከት፣በዚህ ወቅት የነበረውን የጀኔራሉን አቋም፣‹‹ስብሃት ለምን ኋላ ላይ እንዳፈገፈገ ለታሪክ አጥኚዎች የሚተው ይሆናል›› ብሎ አልፎታል፡፡ understanding Eritrea በሚለው መጽሐፉ የሻዕቢያን ጓዳጎድጓዳ የፃፈው ማርቲን ፕላውት ግን፣‹‹ስብሃት ኤፍሬም የኢሳያስ ታማኝ ሆኖ ቀጠለ›› ብሎ ገልፆታል፡፡ያኔ ከታሰሩ ባለሥልጣናት መካከል የወቅቱ የውጭ ጉዳይሚኒስትር ጴጥሮስ ሶሎሞን ይጠቀሳሉ፡፡አቶ ጴጥሮስ ደግሞ፣የስብሃት የምሥጢር ጓደኛ ናቸው፡፡

ሁለቱ ሰዎች ወደበረሃ የወረዱት አብረው ነው፡፡ ወደሳኅል ከማቅናታቸው በፊትም በአዲስ አበባ፣የጥናት ክብቦችን መሥርተው ፖለቲካ የጀመሩት፣ ስፖርታዊ ሥራዎችንና ለበረሃ የሚሆን አመጋገብ ስልቶችን የተለማመዱት፣አብረው ነው፡፡በበረሃ ዘመናቸውም የልብ ጓደኛሞች ነበሩ፡፡በመጨረሻ ግን ስብሃት ኤፍሬም፣ ጓደኛቸውን ከሚያስረው የኢሳይያስ ቡድን ጋር ወገኑ፡፡አቶ ጴጥሮስን ጨምሮም ሌሎች የትግል አጋሮቻቸው በኮንቴይነር ውስጥ ታስረው ለሞት ሲዳረጉ (ከአንድ ዓመት በፊት የወጣ ጥናት በሕይወት የሚገኙት ሁለት ባለሥልጣናት ብቻ ናቸው ብሏል)፣ ስብሃት ኤፍሬም ግን በተደላደለ ኑሮ የእድሜ ዘመናቸውን እየገፉ ነበር፡፡

ልጆቻቸውንም በሲዊዲን በቅምጥል ሕይወት አስቀምጠው፣ውድ ትምህርት ቤት አስተምረዋል፡፡ በመጨረሻም ጀኔራሉ የንጹሃን ደም ከመቃብር ጮኸና፣የግፉአንም ድምጽ ተጣራና በጥይት ተመቱ፤ ከፍተኛ ቁስለትም አስተናገዱ፡፡ የፕሮቴስታንት አማኝ እንደሆኑ የሚገመቱት ጀኔራሉ አሁን እጃቸው ላይ ያለው ሥራ፣‹‹ጌታሆይ ነፍሴን አደራ›› የሚል ጸሎት ብቻ ይመስለኛል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close