Connect with us

Ethiopia

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የጡት አባት ወህኒ ወረዱ! | በጫሊ በላይነህ

Published

on

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የጡት አባት ወህኒ ወረዱ! | በጫሊ በላይነህ

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ የጡት አባት ወህኒ ወረዱ! | በጫሊ በላይነህ)

ኢህአዴግ ከአናቱ መበስበሱ የተነገረውን ገና በጠዋቱ ነበር፡፡ የሕወሓት ክፍፍል ተከትሎ አንጃ የተባለውን ቡድን ለማጥቃት የተመዘዘው ካርድ ሙስና ነበር፡፡ ያኔ ከመለስ ዜናዊ ጀርባ ካሉ ጠንካራ ክንዶች አንዱ የአቶ በረከት ስምኦን ነበር፡፡እነስዬ አብርሃን ጠልፎ ለመጣልና ለመክሰስ የአንበሳውን የታማኝነት ድርሻ በብቃት የተወጡት አቶ በረከት ነበሩ፡፡

አቶ በረከት የኢህዴን/ብአዴን ነባር ታጋይ ናቸው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥም ቁልፍ ሚና ነበራቸው፡፡ ኢህአዴግ አዲስአበባን ከተቆጣጠረ ቀጥሎ ባሉት ጥቂት ዓመታት አቶ በረከት በኢህአዴግ ጽ/ቤት ውስጥ የፕሮፖጋንዳ ዘርፉን በመምራት ድምጻቸውን አጥፍተው ሲመሩ ኖረዋል፡፡ያኔ ከጀርባ ሆነው የድርጅቱን ልሳናትና ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ያሽከረክሩ ነበር፡፡ ራሳቸውን ያበቁ ከመሰላቸው በኃላ ደግሞ በመንግሥታዊ ስልጣን ከች አሉ፡፡ የማስታወቂያ ሚኒስቴርን በኃላም የመንግስት ኮምኒኬሽን ጽ/ቤት፣ የፖሊሲ ጥናትና ምርምርን በሚኒስትርነት ያገልግሉ እንጂ ለረዥም ዓመታት የአቶ መለስ ዜናዊ የቅርብ አማካሪና ረዳት ነበሩ፡፡

ለአባላት በየደረጃው የሚወያዩባቸው እንደ “አዲስ ራዕይ” ያሉ የድርጅቱ ልሳናት ላይ አቅጣጫ ሰጪ ጽሑፎችና የወቅቱን የትኩረት ጉዳዮች ትንታኔ የሚሰጡት ከአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥሎ አቶ በረከት ስምኦን ብቻ ነበሩ፡፡ አቶ በረከት በኢህአዴግ ውስጥ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ዋና አጥማቂ ነበሩ፡፡ የአሁኖቹን መሪዎች ጨምሮ በእሳቸው ያልተማረ ካድሬ ድርጅቱ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ስለአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ስለኪራይ ሰብሳቢነት፣ ስለጥገኛ ኃይሎች፣ በጠላትነት ስለተፈረጀው ፕረስ፣ ስለተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች…ምኑ ቅጡ ያልተነተኑት፣ ያላስተማሩት የለም፡፡

እኚህ ሰው ዛሬ የኦዲተር እጅ ለዓመታት ርቆት በቆየው ጥረት ኮርፖሬት ሙስናና ብልሹ አሠራር ተጠርጥረው ዘብጥያ ወርደዋል፡፡ በጥረት ኮርፖሬት የሙስና ቅሌት መጠርጠር የብአዴን/አዴፓ የማዕከላዊ ኮምቴ አባልነት ሥልጣን አሳጥቷቸዋል፡፡ ከምንም በላይ ከልጅነት አስከዕውቀት ያገለገሉት ድርጅት ፊት አንገታቸውን አስደፍቷቸዋል፡፡ ሕዝብ ክብርና አመኔታውን ነፍጎአቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ወደአማራ ክልል በነጻነት ለመንቀሳቀስ እንኳን የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ለመግባት ተገደዋል፡፡

እነአቶ በረከት በሙስናና ብልሹ አሠራር የተጠረጠሩበት ጥረት ኮርፖሬት ግዙፍ እና ‹‹ስትራቴጂክ›› የሚባሉት ኩባንያዎቹ በሦስት ዘርፎች ከፍሎ ማየት ይቻላል:: ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን ከፋብሪካው ጋር ትስስር ያላቸው የብቅል፣ ቆርኪ እና ፕላስቲክ ፋብሪካዎች በሥሩ አካትቶ ይዟል::

የትራንስፖርት ኩባንያዎች ደግሞ ጥቁር ዓባይ እና በከልቻ ናቸው:: በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ጥረት ‹‹ግዙፍ ኩባንያዎቼ ናቸው›› የሚላቸው የባሕር ዳር እና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ሲሆን፣ ለእነዚህ ፋብሪካዎች አጋዥ የሆኑ ደግሞ ገንዳ ውሃ ጥጥ ማዳመጫ እና በአጠቃላይ ደግሞ የአምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጅትም ባለቤት ነው:: ከነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ አዚላና ጣና ሞባይልን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው ጥረት በድምሩ 20 ኩባንያዎችን ያቀፈ ነው::

የሚገርመው እነዚህ የትርፍና የስኬታማነት ምሳሌ እንደሆኑ በእነአቶ በረከት ስምኦን ሲነገሩ የነበሩ ኩባንያዎች ገመናቸው ሲፈተሸ በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ብር ከሳሪ እንደነበሩና የባንክ ዕዳቸውም 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር መድረሱ ይፋ የሆነው በቅርቡ በበኩር ጋዜጣ አማካኝነት ነበር፡፡

በቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበር በአቶ በረከት ስምኦን እና በወቅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በነበሩት አቶ ታደሰ ካሳ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ጥረት ከ11 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል እና 500 ተሽከርካሪዎች አሉት ቢባልም መረጃው ከእውነታው የራቀ መሆኑን ዶክተር አምላኩ ያስረዳሉ፡፡

የጥረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ እንደሚሉት ጥረት ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የባንክ ዕዳ ያለበት መሆኑን ይፋ አድርገዋል:: ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ የግል ባለሀብቱ ድርሻ ነው:: ከ11 ቢሊዮኑ ውስጥ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮኑ የጥረት ጥሬ ሀብት አይደለም፤ የጥረት ጥሬ ሀብት አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ዶ/ር አምላኩ ገልጸዋል::

በትራንስፖርት ዘርፍ በቀድሞ አመራሮች ይፋ ይደረግ የነበረው መረጃም መሬት ላይ የሌለ ነጭ ውሸት መሆኑን እና አምስት መቶ (500) ተሽከርካሪዎች በጥቁር ዓባይ እና በበከልቻ የትራንስፖርት ድርጅቶቹ በኩል አለው የተባለው መረጃም ስህተት እንደሆነ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት::

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ጥረት በትክክል ያለው የተሽከርካሪ ብዛት 348 ብቻ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 48ቱ ብቻ ዓመቱን ሙሉ ይሠራሉ:: 300ዎቹ ያረጁ እና በጥገና ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጡ ናቸው፤ ሥራ ላይም አይደሉም:: ለዚህም ጥረት 70 በመቶ የጭነት አገልግሎት የሚሰጠው በኪራይ (በኮንትራት) ሆኗል:: ጥረት በትራንስፖርት ዘርፉ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል::

እናም የኢህአዴግ አከርካሪና የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም አጥማቂ የሆኑት ቁልፍ ሰው አቶ በረከት ስምኦን እና የአዴፓ ነባር ታጋይ አቶ ታደሰ ጥንቅሹ በጥረት ውስጥ በፈጸሙት ሙስናና ብልሹ አሠራር ጋር ተያይዞ ጉዳያቸውን ሲጣራ ቆይቶ እነሆ ማረፊያቸው ወህኒ ሆኗል፡፡

በአንዳንድ ምንጮች መረጃ መሠረት ተጠርጣሪዎቹ ወደአማራ ክልል በባህርዳር ተወስደው ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close