Connect with us

Ethiopia

እነበረከት ሲመሩት የነበረው ጥረት ኮርፖሬት

Published

on

በረከት

እነበረከት ሲመሩት የነበረው ጥረት ኮርፖሬት

• በየዓመቱ 100 ሚሊዮን ብር ሲከስር ነበር፤
• የባንክ ዕዳውም 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ደርሷል፣

ጥረት እንዴት ተመሠረተ?
ከደርግ ውድቀት በኋላ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) በተለያዬ መንገድ ያካበተውን ጥሬ ሀብት በመሰብሰብ ለአማራ ክልል ሕዝብ በበጐ አድራጐት (ኢንዶውመንት) ስም ተቋቋመ:: ጥረት ሲቋቋም መነሻ ካፒታሉም ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ:: ዋና ዓላማው ደግሞ በአማራ ክልል ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ነበር:: ጥረት በኢህዴን (አዴፓ) ቢመሠረትም ባለቤትነቱ ግን የአማራ ክልል ሕዝብ እንደሆነ የአሁኑ የጥረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አምላኩ አስረስ ተናግረዋል::

ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መነሻ ካፒታል ለአማራ ክልል ሕዝብ ዘላቂ የበጐ አድራጐት (ኢንዶውመንት) ሆኖ የተዋቀረው ጥረት በአሁኑ ወቅት የ20 ኩባንያዎች ባለቤት ነው:: በነዚህ ኩባንያዎች ለ11 ሺህ ዜጐች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ከ200 ሚሊዮን ብር በላይም ለማኅበራዊ ልማት ዘርፍ እና ለስፖርት እያዋለ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዶክተር አምላኩ አስረድተዋል::

የጥረት ኩባንያዎች የትኞቹ ናቸው?
የጥረትን ግዙፍ እና ‹‹ስትራቴጂክ›› የሚባሉት ኩባንያዎቹ በሦስት ዘርፎች ከፍሎ ማየት ይቻላል:: ዳሽን ቢራ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን ከፋብሪካው ጋር ትስስር ያላቸው የብቅል፣ ቆርኪ እና ፕላስቲክ ፋብሪካዎች በሥሩ አካትቶ ይዟል::

የትራንስፖርት ኩባንያዎች ደግሞ ጥቁር ዓባይ እና በከልቻ ናቸው:: በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ጥረት ‹‹ግዙፍ ኩባንያዎቼ ናቸው›› የሚላቸው የባሕር ዳር እና ኮምቦልቻ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካን ሲሆን፣ ለእነዚህ ፋብሪካዎች አጋዥ የሆኑ ደግሞ ገንዳ ውሃ ጥጥ ማዳመጫ እና በአጠቃላይ ደግሞ የአምባሰል ንግድ ሥራዎች ድርጅትም ባለቤት ነው:: ከነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ አዚላና ጣና ሞባይልን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች እንዲሁም ሌሎች ጥቃቅን ኩባንያዎችን የሚያስተዳድረው ጥረት በድምሩ 20 ኩባንያዎችን ያቀፈ ነው::

ጥረት እና ከእውነት የራቀ ሪፖርቱ
በቀድሞው የቦርድ ሊቀመንበር በአቶ በረከት ስምኦን እና በወቅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ በነበሩት አቶ ታደሰ ካሳ የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው ጥረት ከ11 ቢሉዮን ብር በላይ ካፒታል እና 500 ተሽከርካሪዎች አሉት:: ይሁን እንጂ ይህ ከእውነታው የራቀ የውሸት መረጃ እንደሆነ ዶክተር አምላኩ ያስገነዝባሉ::

ዶክተር አምላኩ እንደሚሉት ጥረት ሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን የባንክ ዕዳ ያለበት መሆኑን ይፋ አድርገዋል:: ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ደግሞ የግል ባለሀብቱ ድርሻ ነው:: ከ11 ቢሊዮኑ ውስጥ አራት ነጥብ ስምንት ቢሊዮኑ የጥረት ጥሬ ሀብት አይደለም፤ የጥረት ጥሬ ሀብት አምስት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ብቻ መሆኑን ዶ/ር አምላኩ ገልጸዋል::
በትራንስፖርት ዘርፍ በቀድሞ አመራሮች ይፋ ይደረግ የነበረው መረጃም መሬት ላይ የሌለ ነጭ ውሸት መሆኑን እና አምስት መቶ (500) ተሽከርካሪዎች በጥቁር ዓባይ እና በበከልቻ የትራንስፖርት ድርጅቶቹ በኩል አለው የተባለው መረጃም ስህተት እንደሆነ ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው የተናገሩት::
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ ጥረት በትክክል ያለው የተሽከርካሪ ብዛት 348 ብቻ ሲሆን፣ ከነዚህ ውስጥ 48ቱ ብቻ ዓመቱን ሙሉ ይሠራሉ:: 300ዎቹ ያረጁ እና በጥገና ከፍተኛ ወጭ የሚያስወጡ ናቸው፤ ሥራ ላይም አይደሉም:: ለዚህም ጥረት 70 በመቶ የጭነት አገልግሎት የሚሰጠው በኪራይ (በኮንትራት) ሆኗል:: ጥረት በትራንስፖርት ዘርፉ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል::

ጥረትን ለምን ትርፍ ራቀው?
ዶክተር አምላኩ እንደሚሉት ለጥረት ኪሳራ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የአመራር ብልሹነት ነው:: ጥረት በትርፋማ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ ገቢውን ለማሳደግ አልሠራም:: ከባለሀብቱ ጋር ሽርክና የሚፈጥርበት አግባብም ልክ አልነበረም:: የጥረት ኮርፖሬት አሠራር ዝርክርክነት የሚታይበት ነበር:: በዚህም ጥረት ካሉት 20 ኩባንያዎች መካከል ሰባቱ በየዓመቱ ይከስራሉ:: ዶ/ር ባምላኩ እንዳረጋገጡልን ከነዚህ ሰባት ኩባንያዎች በየዓመቱ በአማካይ የ100 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ይደርስበታል:: ሥራ አስፈፃሚው ጥረትን ለኪሳራ የዳረጉ አመራሮች መረጃው ተጣርቶ እና ተሰንዶ ወደ ሕግ ተልኳል፤ በሕግ አግባብ የሚወሰደውን እርምጃ በተመለከተም በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋል ብለዋል::

(ምንጭ፡- በኩር (የሺሐሳብ አበራ)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close