Connect with us

Ethiopia

የአማራና የትግራይ ክልል ውጥረቶች

Published

on

የአማራና የትግራይ ክልል ውጥረቶች | ፀጋው መላኩ

የአማራና የትግራይ ክልል ውጥረቶች | ፀጋው መላኩ@DireTube

በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ውጥረት አደገኛ ውጤትን እንዳያስከትል ሥጋትን አጭሯል፡፡ የነገሩ አካሄድ ያላማራቸው የሀይማኖት አባቶች የሁለቱን ክልል መስተዳድሮች አዲስ አበባ ድረስ ጠርተው ነገር አብርዱ ብለዋል፡፡ ጉዳዩ አንደ ጓደኛ ፀብ፤ “አንተም ተው አንተም ተው” የሚያልቅ አይደለም፡፡ ባለፉት ዓመታት የተሄደበት የፖለቲካ መስመር በሁለቱ ክልሎች መካከል የፖለቲካ ክፍተትን ፈጥሯል፡፡ እናም በከፋኝ ስሜት የተወጠረው የፖለቲካ ፊኛ የመፈንዳት የውጥረት ጫፍ ላይ መድረሱ በርካቶችን አስግቷል፡፡ በፖለቲከኞች የተጀመረው ጨዋታ ከፖለቲከኞች እጅ እየወጣ መሆኑ ሲታይ ደግሞ የሁኔታውን አሳሳቢነት ይበልጥ አንሮታል፡፡

በአማራ ከልል በምሽት አዝማሪ ቤቶች የሚዜሙ ዘፈኖች፣ለአዝማሪ የሚሰጡ ግጥሞች ወደፊት አለ ነገር የሚያስብሉ ናቸው፡፡ የግጥም ምሽቶች በሽለላና በቀረርቶ የተሞሉ ናቸው፡፡ የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ከጋዜጣው እስከ ቴሌቭዥኑ ቀድሞ በህዝቡ ላይ ደረሰ የተባለውን የህወሓት በደል በሰፊው ማስነበብ፣ማስደመጥና ማሳየት ከጀመሩ ዋል አደር ብለዋል፡፡ ከሚዲያዎቹ የመረጃ ስርጭት ባሻገር ህብተረሰቡ መረጃዎቹን የግል ቤተሰባዊ ጉዳይ ያህል በሚገናኝባቸው ማህበራዊ ግንኙነቶች ሁሉ የዕለት ተዕለት መነጋገሪያ አጀንዳው አድርጎ ይወያይባቸዋል፡፡

በመሆኑም ሰዎች በየጀበና ቡናው ሲኮልኮሉ፣በየካፌውና ባሩ ሲዝናኑ፣በየትራንስፖርት ሲጓጓዙ ብሎም በየማህበራዊ ሚዲያው የመረጃ ልውውጥ ሲያደርጉ የጭውውት ጭብታቸው ማጠንጠኛ ሀሳብ አንድና አንድ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህም አንኳር ነጥብ የአማራ ህዝብ ባለፉት 27 ዓመታት ከባድ በደልና ግፍ የደረሰበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡

በመሆኑም “ ተበድያለሁ፣የዘር ማጥፋት ደርሶብኛል፣ማንነቴ በሌላ ማንነት ተውጧል፣ታሪካዊ ግዛቶቼ ሳይቀሩ በሌሎች ክልሎች ውስጥ እንዲካለሉ ተደርጓል” በማለት የሚነሱት የአማራ ማንነት ጥያቄዎች የሚዲያዎች የውይይት አጀንዳዎች ከመሆን ባለፈ በየሰልፉ በሚታዩ መፈክሮችም ከፍ ብለው ሲውለበለቡ ይታያል፡፡ እናም በክልሉ በሰው ሰሜት ውስጥ ተረግዞ ያልተወለደ፤ በውስጥ መብሰልሰል እየተናጠ ገፍትሬ ካልወጣሁ የሚል የመጠቃት ስሜት ከፍ እያለ ሄዷል፡፡

ይህ ሁሉ የመረጃ ማዕበልና ናዳ መሬት ወርዶ ፍሬ እያፈራ ለመሆኑ አንድ ሁለት ብሎ መረጃዎችን ማጣቀስ ይቻላል፡፡ ሀገሬው ከከተማ እስከ ገጠር ጥቂት ሀብትና ጥሪት አሟጦ የጦር መሳሪየያ ሸመታ ውስጥ ገብቷል፡፡ ቀደሞውኑ ነፍጥ የመታጠቅ ባህልና ልምድ ያለው የአማራ ህዝብ ከአንድ መቶ ሺህ ብር በላይ ዋጋን የሚያወጣ ክላሽ የጦር መሳሪያን ሸምቶ በነፍስ ወከፍ መታጠቅ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል ፡፡

ጥራኝ ደኑ….ጥራኝ ጫካው የሚለው እንጉርጉሮም ጎልቶ ይሰማል፡፡ እናም የተጣደው የስሜት ድስት ፈልቶ መክደኛውን ወደላይ እያጎነው ይገኛል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ድስቱ መገንፈል በመጀመሩ እያቃጠለም ይገኛል፡፡

በህግ አስተምህሮ መሰረት “ከአንድ ሁነት በፊት ሁለት ነገሮች ይከናወናሉ” ይባላል፡፡ እነዚህም ሀሳብና ሀሳቡን ለመፈፀም የሚደረጉ መሰናዶዎች ናቸው፡፡ ሁለቱ ከተፈፀሙ ሶስተኛው የሁለቱ ቅንጅት የሆነው ድርጊት ወይንም አክሽን ነው፡፡ በትግራይም ሆነ በአማራ ክልል የሃሳብ መሻከሮችና መውጠንጠኖች ይታያሉ፡፡ አንዱ ሌላውን ለማጥቃትም ሆነ ለመከላከል ከሰፊ የጦር መሳሪያ ሸመታ ጀምሮ የሚታዩ ዝግጅቶች አሉ፡፡ ጉዳዩ፣የህዝብ ነው?፣የክልሎች ነው?፣የየክልሎቹ ገዢ ፓርቲዎች ፍትጊያ ነው? ወይንስ የሁሉም ድብልቅ ውጤት ነው? የሚሉት ነጥቦች የየራሳቸውን ሰፊ ፍተሻ የሚጠይቁ ናቸው፡፡

ለማንኛውም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያው ግብይቱ በሰፊው ደርቶ ይታያል፡፡ በሁለቱም ክልሎች በስፋት የሚታየው የጦር መሳሪያ ታጣቂነት ፍሎጎት መጨመር፤ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችንና አቅራቢዎችን ቀልብ በከፍተኛ ደረጃ ስቧል፡፡

እናም በዝውውር ላይ እንዳሉ በጅምላ የሚያዙት ህገወጥ ጦር መሳሪያዎቹ ተገቢው ክትትል ሲደረግባቸው ጫፋቸው ኢትዮጵያ ይሁን፤ እንጂ ጅራታቸው ከቱርክ እንደሚመዘዝ መሬት ላይ እየታዩ ያሉት እውነታዎች በሚገባ ያመላክታሉ፡፡ በተለይ በሱዳን በኩል ወደ አማራና ትግራይ ክልሎች የሚገቡት የተለያዩ ዘመናዊ ሽጉጦችና ሌሎች የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች መነሻቸው አውሮፓዊቷ ቱርክ መሆኗችው ሲታሰብ የጦር መሳሪያ ሸመታው የንግድ ሰንሰለት ምን ያህል ረዥምና በሚገባ የተደራጀ መሆኑን በግልፅ የሚያሳይ ነው፡፡

ከጦር መሳሪያ መታጠቁና ማከማቸቱ ጎን ለጎን በሌላ አቅጣጫ በትግራይ በኩልም ሌላ የስሜት ግለት ይታያል፡፡ በአማራ ክልል እየሆኑ ያሉት ነገሮች ሁሉ በትግራይ ክልልም እየሆኑ ነው፡፡ ልዩነቱ ለድርጊቶቹ መነሻ የሆኑት ምንጮች ብቻ ናቸው፡፡

የአማራ ክልል በተጠቂነት ስሜት፣በግዛት ይገባኛልና ከማንነት ጋር በተያያዘ የሚንተከተክ የብሄርተኛ ስሜት ሲሆን በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በትግራይ አካባቢ በጥቃት ስጋት ውስጥ የመሆንና የመከበብ ስሜት ይታያል፡፡ የኤርትራ መንግስት ከክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ጋር የገባበት የቂም ቁርሾ በኢትዮ-ኤርትራ አዲሱ ግንኙነት ሊሽር አለመቻሉ ለበርካታ የትግራይ ተወላጆች ሥጋትን ፈጥሯል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለዓመታት በደንበር ላይ ተከማችቶ የነበረው መከላከያ ሰራዊት ወደ መሀል አገር መነቃነቁ ደግሞ ሌላው ሥጋቱን ያናረው ፈተና ሆኗል፡፡ እናም በሰሜን ከኤርትራ በኩል ከደቡብ ከአማራ ክልል ጋር በስጋት የተወጠረው የትግራይ ክልል፤ ነገሮች መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ ካልተደረገ ሁኔታዎች አስቸጋሪ መሆናቸው አይቀሬ ሆኖ ይታያል፡፡ ተፅዕኖው ፖለቲካዊ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊም ጭምር መሆኑም ሊዘነጋ አይገባም፡፡

በአማራና ትግራይ አዋሰኝ ደንበር፤ መንገዶች በተደጋጋሚ መዘጋታቸው ትግራይ ከመሀል አገር ጋር ባላት ግንኙነት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን አሳድሯል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴን ያነቃቃል ተብሎ የታሰበው የዛለንበሳው የኢትዮ-ኤርትራ ደንበር ተመልሶ መዘጋቱም የኢኮኖሚ አየሩን ከዜሮ በታች ወደ በረዶነት እንዲቀየር እያደረገው ይገኛል፡፡

ከዚህ ባለፈም በስጋት ውስጥ ያለውን የአማራ ትግራይ ደንበሮች ለጊዜው ተወት በማድረግ በአፋር ክልል ትግራይን ከመሀል አገር ጋር ለማገናኘት የተጀመሩት ሙከራዎች ደግሞ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ገጥመውታል፡፡ አንደኛው የአካባቢው ርቀትና በረሃማነት ሲሆን በሌላ ፈተና ደግሞ አሁን በአፋር ክልል እየታየ ያለው አለመረጋጋት ነው፡፡

እነዚህ ሁኔታዎች ሲታዩ ትግራይ እንደ ክልል አስቸጋሪ ፈተና እየገጠማት መሆኑ እያፈጠጠ የመጣ እውነታ ሆኖ ይታያል፡፡ እናም ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልሉ መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት መከሰት ጀምሯል፡፡ የዋጋ ንረት ክስተቱ ከተፈጠረው ውጥረት ጋር በተያያዘ አንድም የተሳለጠ የንግድ ግንኙነትን መፍጠር ባለመቻሉ ሲሆን፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ በርካታ ኤርትራዊያን ሀገራቸውን ጥለው መኖሪያቸውን በትግራይ ከተሞች ማድረጋቸው እንደሆነም ይነገራል፡፡

በብዙ የኑሮ ውድነት ውስጥ ያለፉት ኤርትራዊያን በትግራይ ምንም ያህል የኑሮ ወድነት ቢከሰት እነሱ ካሳለፉት ኑሮ የከፋ ስለማይሆን፤ አሁን በትግራይ እየታየ ያለውን ሁኔታ እንደ ችግርም አይቆጥሩቱም፡፡ እናም ከውጪ በሚላክ ገንዘብ ገበያ የሚወጣው ኤርትራዊና ሰርቶ በወር በሚያገኘው ገቢ ገበያ የሚወጣ አንድ የትግራይ ክልል ነዋሪ፤ እኩል የመግዛት አቅምና የሸማችነት ተወዳዳሪነት ላይ ሊቀመጡ አይችሉም፡፡ ስለሆነም ቀሰም ባለው የሰው ፍልሰት፤ የመብረቅ ብልጭታ ያህል ተከፍታ የተዘጋችው የዛላንበሳዋ ኢትዮ-ኤርትራ ደንበር ለትግራይ ክልል ተጨማሪ የኢኮኖሚ ፈተናን ደቅና ትታያለች፡፡

እንግዲህ አቶ ገዱና ዶክተር ደብረፅዮን በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተገናኝተው ለህዝባቸው የሰላም ጥሪ እንዲያስተላልፉ የተደረገው፤ በእንደዚህ አይነት ፖለቲካዊ ውጥረትና ኢኮኖሚዊ ፈተና ውስጥ ነው፤

ድርጊቱ መልካምና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ሆኖም ጅማሮው የችግሩን ምንጭ ለይቶ መፍትሄ መስጠቱ ላይ ትኩረቱን ቢያደርግ በእርግጥም ዘላቂ ውጤት ይገኛል፡፡ በትግራይም ሆነ በአማራ ህዝብ መካከል ጎራዴ የሚያማዝዝና ነፍጥ የሚያስነሳ ታሪካዊ ጠላትነት የለም፡፡ የተፈጠሩት ሁኔታዎች ከአንድ ፓርቲ እድሜ የዘለሉ አይደሉም፡፡

ጉዳዩን የበለጠ ያከረረው የፌደራሊዝም ሥርዓቱና አከላለሉ ከማንነት ጋር የተቆራኘ መሆኑ ነው፡፡ በዓፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜም ሆነ በደርግ ዘመን ጠቅላይ ግዛቶችና ክፍለሀገሮች ለአስተዳደር አመቺ በሆነ መልኩ በተፈለገው መጠን የአከላለል ለውጥ ሲደረግባቸው አንዳች አይነት የተቃውሞ ድምፅ ተሰምቶ አይታወቅም፡፡ በዚህ ዙሪያ ታሪክ የዘገበው የህዝብ ውጥረትና ግጭትም የለም፡፡

እናም ዛሬ ከማንነት፣ከግዛት ይገባኛልና ከመሳሰሉት ጋር ህዝቡ በየአቅጣጫው ከባድ ውጥረትና መፋጠጥ ውስጥ ሲገባ ሲታይ ችግሩ የህዝቡ ሳይሆን ያን ጊዜ “ይህ አይነቱ ፌደራሊዝም ይበጀችኋል” ብለው በማንነት ጎጥ ከልለው ካስቀመጡን ፖለቲከኞች የመነጨ ነው፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን በይይቱ ማጠቃለያ ከአቶ ገዱ ጋር በሰጡት የጋራ መግለጫም “የህዝቦች ችግር የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ ጉዳዩ የፖለቲከኞች ነው፡፡” ነበር ያሉት፡፡ ዘግይቶም ቢሆን ከገባን እውነታው ይህ ነው፡፡

እናም በዚህ በከፋው ዘወግ ተኮር የፌደራሊዝም ሽንሸና ትግራይና የአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአፋርና የሶማሌ ህዝብም ሌላ ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡ ሶማሌና ኦሮሞም ተከባብሮ በኖረበት ሀገር ደም መቃባት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ እንዲህ እየተባለ አንድ በአንድ ቢዘረዘር በዚህ ዘር ተኮር ፌደራሊዝም ዋጋ ያልከፈለ ኢትዮጵያዊና ብሄረሰብ የለም፡፡ ይህ ሁኔታ መንግስትም ቢሆን ከልማት ይልቅ የፖሊሰነት ሚናን ብቻ ትኩረቱን እንዲያደርግ አስገድዶታል፡፡

ጉዳዩ ዘውግ ተኮር አከላለል ባይሆን ኖር ጎንደር እስከ አደዋ ቢከለል የትግራይ ህዝብ አንዳች ቅሬታን የሚያነሳበት ሁኔታ አይኖርም ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ትግራይ እስከ ጎንደር ከተማ ቢከለል አማራው ከፋኝ ብሎ በቅሬታ የሚኖርበት ክስተትም አይፈጠርም፡፡ እዚህ ጋር አንድ ማሳያ ቁምነገር እናንሳ፤በቀደመው አከላል አፋርና አማራ ወሎ ክፍለ ሀገር በሚባለው የክፍለ ሀገር ስያሜ በአንድ ክልል ውስጥ ኖረዋል፡፡

የዛሬ የሰሜን ሸዋ ዞን የአማራ ክልልና የኦሮሚያ ምስራቅና ምዕራብ ሸዋ ከአምቦ እስከ ሻሸመኔ እንደ አንድ የሸዋ ክፍለ ሀገርነት ተጠቃለው ሲኖሩ ከማንነት ጋር በተያያዘ አንድ ቀን ድምፃቸው የተሰማበት የታሪክ አጋጣሚ አልነበረም፡፡ እናም እነዚህን ሁሉ ሁኔታዎች ደምረንና ቀንሰን ስንመለከት የትግራይንና የአማራ ክልሎችን ጨምሮ አሁን እየታዩ ያሉት መገፋፋቶችና ውጥረቶች በህዝቦች መካከል የተፈጠረ ሳይሆን የአንድ ዘመን ፖለቲካ ወለድ በሽታ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም በዚህ ፖለቲካ ወለድ በሽታ ሰዎች ፈልገው ባላመጡት ማንነት የጥቃትና የውጥረት ሰለባ ለመሆን ተገደዋል፡፡

ዛሬ ይህንን የፖለቲካ ወለድ ሸንኮፍ መንቀል ካልቻልን በስተቀር ችግሩ ችግርን እየወለደ ከቀላሉ መፍትሄ እያራቀን ወደ ውስብስቡ የፖለቲካ ጫካ ይወስደናል፡፡ እናም የአቶ ገዱና የዶክተር ደብረፅዮን የሰላም ጥሪ መሬት ላይ ጠብ ብሎ ፍሬ ማፍራት የሚችለው የችግሩን ቅርንጫፍ በመመልመል ሳይሆን የዛፉን ሥር በመመርመር ጭምር መሆን ሲችል ብቻ ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close