Connect with us

Ethiopia

ያልተጣላው ሕዝብ እንዳይጣላ፤ የጠብ ሰበቦችን መፍታት መፍትሔ ነው

Published

on

ያልተጣላው ሕዝብ እንዳይጣላ፤ የጠብ ሰበቦችን መፍታት መፍትሔ ነው

ያልተጣላው ሕዝብ እንዳይጣላ፤ የጠብ ሰበቦችን መፍታት መፍትሔ ነው፡፡ በአማራና በቅማንት መካከል ችግር የሚፈጥሩ ሰርጎ ገቦችን ህወሃት አደብ ያስገዛ፡፡

በትግራይና በአማራ መካከል የጦርነት ነጋሪት የሚጎሽሙትን አዴፓ አደብ ያስይዝ፤ | ከስናፍቅሽ አዲስ

አቶ ገዱና ዶክተር ደብረ ጽዮን ሠላም ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ሁለቱም የሚመሩት ህዝብም ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ ያ ባይሆንማ እስከአሁን የተጎሸመው ነጋሪት ምድሩን የደም ጎርፍ ባጥለቀለቀ፡፡ ነገር ግን ያልተጣላው ህዝብ መጣላት አለመፈለጉ ብቻ ላለመጣላት ዋስትና አይሆነውም፡፡ ጠብ የሚርቀው የሚያጣላን ነገር በማራቅ ነው፡፡

በህወሃት በኩል አሁንም ቅማንት ነኝ ብሎ ቅማንትን ሳይወክል ሚስትን ባሏ ላይ የሚያዘምት ተልእኮ የተሰጠውን ቡድን የሚደግፉ የህወሃት ሴረኞችን አደብ የማስዛት ስራ ያስፈልጋል፡፡ ዶክተሩ ጉያቸው ተቀምጠው ውጊያ ቀስቃሽ ጽሑፎችን የሚጽፉ አክቲቪስት ነኝ ባይ ወንበዴዎችን ቀለብ መቁረጥ ማቆም ብቻ ሳይሆን ከአጠገባቸው ማባረር አለባቸው፡፡

በሌላ በኩል ከሰብዓዊ መብት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የአቶ ጌታቸው አሰፋን ጉዳይም የህግ የበላይነት ይከበር ዘንድ ህወሃት ቁርጠኛ መሆኗን ማረጋገጥ ይኖርባታል፡፡ ይህ ካልሆነ ነገም የአማራ ህዝብ አንድ ነገር ያደረገኝ ሽፍታ መቀሌ ገብቶ ቢሸሸግ መቀሌ ሀገሬ ስላልሆነች ምንም አይደረግ የሚል መንፈስ እንዲያንሰራራበት ያደርገዋል፡፡

በሌላ በኩል አዴፓም ሆነ አቶ ገዱ ብዙ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ጠዋት ማታ የትግራይ ህዝብ ላይ የጦርነት ነጋሪት የሚጎሽሙ ዘረኞችን መመንጠርና አደብ ማስገዛት አለበት፡፡ ህጋዊ ያልሆኑ የመንጋ ፍርዶችን ማስቆም አለበት፡፡ ራያና ወልቃይት በህግ አግባብ እንጂ ከምክንያቱ በሚርቁ አመጾች መፈታት እንደሌለባቸው ማመን አለበት፡፡

ህዝቡ ጠብ አይሻም፡፡ ብዙ ጊዜ የጦር አውድማ ብዙ ግዜ ሞቶ አንዴ መኖር ያልታደለ ህዝብ ነው፡፡ የተጋባ የተዋለደ ህዝብ ነው፡፡ አንዱ የአንዱ ጠላት አይደለም፡፡ ሁለቱም ክልሎች ተተኪውን ሀገር በታኝ እንቢተኛና ራዕይ አልባ ትውልድ ማረቅ ይኖርባቸዋል፡፡

ሌላው የሁለቱም ፓርቲዎች የቤት ስራ የሃይማኖት አባቶችን መተው ነው፡፡ ህወሃት ካህናቱን መልምላለች፤ አዴፓ የታጠቀውን ቄስ አይዞህ ትላለች፡፡ ይህ ክፉ ቀን ሲመጣ አንተም ተው አንተም ተው ለመባባል ችግር እንደፈጠረ አይተናል፡፡ ከዚህ በኋላ የሀገር ሽማግሌውንና የእምነት አባቱን በፖለቲካና በጎሳ ላለማሰለፉ ጥረት ይደረግ፡፡

መሪዎቹ የፈጠሩት መልካም ውይይት ወደ መሬት መውረድ አለበት፡፡ ድባቡን የሚቀይር መሆን አለበት፡፡ ከአቶ ገዱ እና ከዶክተር ደብረ ጽዮን በፊት እግር ኳስ ክለቦች መልካም ነገር አሳይተውን ነበር፡፡ ያን ተከትሎ ይሄ ሆነ ነገ የተሻለ እንዲሆን ሁሉም የራሱን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል፡፡

የጠብን መንስኤ ካራቅን ጠብ ሊኖር አይችልም፡፡ የጠብ መንስኤ ውስጥ ከኖርን በየወንዙ ብንማማልም ከግጭት አንድንም፡፡ እናም ፍቅር በፍቅር መንገድ ሲሄዱ የሚገኝ መልካም እሴት መሆኑን አውቀን ስለ ፍቅር ብዙውን ነገር እንተወው፤

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close