Connect with us

Ethiopia

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምን ይፈይዳል? | ከሬሞንድ ኃይሉ

Published

on

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምን ይፈይዳል? | ከሬሞንድ ኃይሉ

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ምን ይፈይዳል ? | ከሬሞንድ ኃይሉ

ኢህአዴግ ጉባዔውን ካከሄደ በኋላ አዳዲስ ፈተናዎችን እየተጋፈጠ ነው፡፡ በኦዲፒና በኦነግ መካከል ያወለው ዕሰጣ ገባ ብረት ባነገቡ ወገኖች የታጀበ ሁኗል፡፡ አዴፓም በምዕራብ ጎንደር በኩል ያለው አለመረጋጋት ስላም ነስቶታል፡፡ እየተንከባለለ የመጣው የቅማንት ማኅበረሰብ ጥያቄም መልኩን እየቀያየረ ደመ አፋሳሽ ሁኗል፡፡

ደኢህዴን ከስምንት በላይ የክልል እንሁን ጥያቄዎችን የማስተናገድ ህገ-መንግስታዊ የቤት-ስራ ላይ ወድቋል፡፡ አማራና ኦሮሚያ ክልል ላይ የሚሰተዋለው መንገድ የመዝጋትና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት የማድረስ ልምድም ከእሱም ደጃፍ ደርሷል፡፡

ህወሓት የትግራይን ህዝብ ወደ መማጸን ወርዷል፡፡ ወዲህ ከአመራ ክልል ወደ ትግራይ የሚሻገር ዕህል በተደጋጋሚ መታገድ ወዲያ የፕሬዘዳንት ኢሳይያስ አስተዳደር የዛላምበሳን ድንበር መዝጋት ድርጀቱ በጥንቃቄ ካልተጓዘ የነካው ሁሉ ዕሳት እንደሚሆን አስገንዝቦታል፡፡

አንጻራዊ ሰላም የነበረባቸው የአፋርና የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ወቅታዊ ሁኔታም ሀገራዊ ቀውሱ በጊዜ ሂደት ከመቀነስ ይልቅ የመስፋፋት አዝማሚያ እያሳየ እንደሆን ያስገነዝባል፡፡ ኢህአዴግ በዚህ የዘመን ምስቅለቅ ወቅት 36 ዓባላቱን ለመፍትሄ ጠርቷል፡፡

በርግጥ ከድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ አንጻር የየግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ስልጣን ከጉባዔውና ማዕከላዊ ኮሚቴው በታች ነው፡፡ ይህ ደግሞ ስራ አስፈጻሚው ቢሰበሰብም የጉባዔውንና የማዕከላዊ ኮሚቴውን ውሳኔዎች አተገባበር ለመከታታል ብቻ ያደርገዋል፡፡

እንዲህ ያለው የተለምዶ አሰራር ግን ለዛሬው ኢህአዴግ እንደማይሆን አያከራክርም፡፡ ለዚህ ደግሞ የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የመጀመሪያውና መሰረታዊው ነገር የኢህአዴግ ጉባዔ ኢትዮጵያን ከገባችበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለማላቀቅ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ውጤታማ አለመሆናቸው ነው፡፡

የድርጅቱ ትልቁ የስልጣን አካል በወርሃ መስከርም ተሰብስቦ አፋጣኝ መፍትሄዎችን ቢያስቀምጥም ሀገሪቱ ግን መረጋጋት አልቻላችም፡፡ በዚህ ምክንያትም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ጉባዔው ካሳለፈው ውሳኔ ጋር የሚተሳሰሩ አማራጭ መፍትሄዎችን ማሰቡ የሚቀር አይመስልም፡፡ እነዚህ መፍትሄዎች ደግሞ ሀገሪቱን ወደ ተሻለ አልያም ወደ ባስ መንገድ ሊወስዱ የሚችሉ ናቸው፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ በአባል ድርጅቶቹ መሃል ያለው አለመግባባት መካረሩ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ በሰጠው መግለጫ በዕህት ድርጅቶች መካካል ያለውን ልዩነት የሚፈቱ ውሳኔዎች መተላላፋቸውን ገልጾ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔ ከወረቀት የዘለለ ፋይዳ ያለው አልሆነም፡፡ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዎን ገ/ሚካዔል (ዶ/ር ) ከሰሞኑን በአደባባይ ኢህአዴግ ውስጥ መካካድ ነግሷል የሚል አስተያየት መስጠታቸውም ለዚህ ማሰረጃ ይሆናል፡፡

ይህ አይነቱ መካካድ ግን በማዕከላዊ መንግስቱና በክልል መንግስታት ብቻ ሳይሆን በክልልና በዞን አመራሮችም የሚሰተዋል ሁኗል፡፡ የደኢዴን ሊቀመንበር ሙፋረያት ከሚል የዞኖች የክልል እንሁን ጥያቄ ድርጅታችን ካስቀመጠው አቅጣጫ ውጭ የሚካሄድ ነው ሲሉ መደመጣቸውም ለዚህ አብነት ነው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ጉዳዮች ኢህአዴግ ከጉባዔው በኋላም ቢሆን የነበረበት በሽታ እየጸናበት እንጅ እየተፈወሰ አለመሄዱን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ ለስልጣን ብቁ የሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ በሌለበት ሁኔታ ለሀገር ህልውና አሳሳቢ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ምክነያትም ድርጅቱ በመግለጫዎቹ ተስፋ እየሰጠ ሊቀመናብርቱንም በየአዳራሹ እያስተቃቀፈ ለአንድ ሳምንት የሚሆን የማገገም ዜና ከመስጠት ያለፈ ተግባር ሊኖረው ይገባል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close