Connect with us

Ethiopia

ብራቮ ገዱ፣ ቪቫ ደብረጽዮን | ከበኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

Published

on

ብራቮ ገዱ፣ ቪቫ ደብረጽዮን | ከበኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ብራቮ ገዱ፣ ቪቫ ደብረጽዮን | ከበኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

በቴሌቭዥኑ ላይ የማየውን ነገር ማመን አልቻልኩም፡፡ ቀጥታ ስርጭት እንደሆነ የሚገልጽ ጽሁፍ ተጽፎበታል፡፡ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እየተናሩ ነው፡፡ የሚናገሩት ነገር አንዳች ስሜትን ያጭራል፡፡ ሊሆን አይችልም ብዬ ተጠራጠርሁ፡፡ ሪሞቴን ተጭኜ ቻናል ቀየርሁ፡፡ተመሳሳይ ነገር ገጠመኝ፡፡ ‹‹እኔ ሥራዬ ይህንን ሁለት ወንድማማች ሕዝብ ወደ ሰላም ማምጣት ነው፤ ይህ ንግግሬ ፊርማዬ ነው››የሚለውን የአቶ ገዱን አንደበት አደመጥሁት፡፡ እንደገና ቀየርሁ፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን እየተናሩ ነው፡፡ ‹‹እንዲህ ያለ ደረጃ ላይ በመድረሳችን አዝናለሁ፡፡ ስንት ገድል በጋራ የፃፈ ሕዝብ፣ በእኛ ዘመን ለጠብ እንዲፈላለግ ያደረግነው እኛ ነን›› የሚል ይዘት ያለውን ንግግራቸውን ጆሮዬ ማመን አልቻለም፡፡

ዓይኖቼ ትኩስ እምባ ሲያንቀረዝዙ አገኘሁዋቸው፡፡ ሪሞቴን በመዳፌ ይዤ አገጬን ደገፍ እንዳልሁ እምባዬ እጄን ሲነካው ታወቀኝ፡፡

በርግጥም እንዲህ ያለው ስሜት ባይሰማኝ እመርጥ ነበር፡፡ የሁለት ሀገር ሕዝብ ለእርቅ የተቀመጠ ያህል ገዱንና ደብረጽዮንን ጎንለጎን ሳያቸው የተለየ ስሜት ባይኖረኝ ይሻለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ የሚመሩ ሰዎች ለአንድ አገር ሕዝብ የጋራ እሴቶች ተባብረው መሥራት እየተገባቸው ሊያቃቅሩት፣ ደም ሊያቃቡት ጫፍ ላይ ስለመድረሳቸው በየቀኑ አስብ ነበር፡፡

የአማራንና የትግራይን ሕዝብ ኑሮ፣ ባሕል፣ ስነ-ልቦና፣ ሕብረትና እምነት በደንብ ከሚያውቁ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ሁለቱንም ሕዝብ በደንብ አውቀዋለሁ፡፡ የእለት ጉርሱን፣ የአመት ልብሱን ለማግኘት ከድንጋይ ጋር ሲታገል የሚውል ገበሬ ያለበት፣ ችግርን ተዛዝኖና ተጋግዞ ለማሳለፍ ሲጥር የሚውል አርሶ አደር ያለበት፣ በአንድ ገበያ ላይ በትግርኛና በአማርኛ እየተገበያየ የሚውል፤ በአንድ ቤተክርስቲያን ሲያስቀድስ አርፍዶ፣ ለጋራ ሰላም ሱባኤ የሚያደርግ፣ በአንድ መስጂድ ሰግዶ ፈጣሪውን የሚማጸን ደግ ሕዝብ ነው፡፡

እውነቱን ለመናገር እንደ ትግራይና አማራ ሕዝብ የተዋለደ፣ የተዋደደና የተሳሰረ ባለሁለት ቋንቋ ሕዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አይመስለኝም፡፡ ጎንደር ላይ የተደገሰ ሰርግ የሚደምቀው ሹርባ ተሰርተው ትግርኛ በሚደንሱ እናቶች ነው፡፡ ሽሬ ላይ ያለ ደስታን ታደሰ ዓለሙ ካልዘፈነበት አይሞቅም፡፡ የመቐለ ጭፈራ ቤቶች ድምቀት እነ ይሁኔ በላይ ናቸው፤ የባሕርዳር ምሽት ቤቶችም ‹‹ናኢባባ ናኢባባ›› የሚል ዘፈን ከፍተው ገበያቸውን ያደሩ ነበር-እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ይህ ተቀይሮ ዘፈንን ሳይቀር የሚከለክል፣ ሰዎችንም የሚያሳድድ ነገር ስመለከት እንደ አንድ ሀገር ወዳድ ዜጋ አልቅሻለሁ፡፡ መዝናኛ ቤት ገብቼ የምሰማቸው ዘፈኖች የጦርነት ዋዜማ ላይ እንዳለን ተሰምቶኝ ቆዝሜያለሁ፡፡ ፖለቲከኞቹ በፈጠሩት ፖለቲካዊ ስህተት ሕዝብ እሴቶቹን ሸርሽሮ፣ መዋደዱን ትቶ፣ መዋለዱን ረስቶ ደም እንዲቃባ ስለት የሚስሉ ሰዎች በዙ፡፡

ጦር መሣሪያን በገፍ መታጠቅ፣ በወገን ሕዝብ ላይ ጦርነት ማወጅ፣ መዛዛት በረከተ፡፡ የፌደራሉ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሲሰጥ አልታይ አለኝ፡፡ የክልል መሪዎች ‹‹ግባ በለው›› እያሉ ጎራዴ መሣል ሥራቸው ሆነ፡፡ በትልልቅ ክልላዊ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ሳይቀሩ፣ ሕዝቡን ለጦርነት እያዘጋጀነው ነው ሲሉ መግለጫ ሰጡ፡፡ ድሃን አርሶ አደር ፣ ምስኪን እናቶችን አባልተው እነርሱ እሳቱን ሊሞቁ ፣ የተዋለደንና የተዋደደን ሕዝብ ደም አቃብተው ሊያራርቁ፣ ዘራፍ አሉ፡፡ በርግጥም ስሜቱ አስፈሪ ነበር፡፡

በዚህ መሀል ነው እንግዲህ የምመኘውን ነገር በቴሌቭዥን ያየሁት፡፡ አቶ ገዱ፣ ዶ/ር ደብረጽዮንና ዶ/ር ዓቢይ ይህንን ውጥረት ለማርገብ ብቸኛ መፍትሔ ናቸው ብዬ አስብ ነበር፡፡ እነዚህ መሪዎች በየዘርፋቸው ያላቸውን ተደማጭነት ተጠቅመው ከልብ ቢሰሩ ጸቡ እንደሚበርድ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡ ወዲያው ከአንድ ሳምንት በፊት ዶ/ር ዓቢይ ሁለቱ መሪዎች በቴሌቭዥን ቀርበው የጋራ መግለጫ እንዲሰጡ ማዘዛቸውን ሰማሁ፡፡ ሆኖም በአንድ ወገን በኩል በታየ ቸልተኝነት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ እንዳልተፈጸመ መረጃው ደረሰኝ፡፡ አዘንሁ፡፡ ሀዘኔን ሳልጨርስ ግን ገዱንና ደብረጽዮንን በጋራ መግለጫ ላይ አየኋቸው፡፡ ማይ ጋድ!! እንዴት ደስ የሚል ስሜት ነው!!

መዋሸት አልፈልግም፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ ታርቀው ዶ/ር ዓቢይና አቶ ኢሳያስ እንኳ ሲተቃቀፉ እንኳ እንዲህ ያለ ደስታ አልተሰማኝም፡፡ በሁለቱ ሕዝቦች መሀል ባለ ነባር የአስተዋይነት፣ የአንድነትና የልብ ወዳጅነት ምክንያት እንጂ እንደ ፖለቲከኞቹ ፍላጎት፣ ሴራና ስራ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ደም አፋሳሽ ውጊያ ተደርጎ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን የሁለቱ ክልል መሪዎች ለዚህ ሰላም በጋራ ለመስራት አንድ ዓይነት ቋንቋ ሲያወሩ በዓይናችን ዓየን፤ በጆሮአችንም ሰማን፡፡ ጥር 7-20111 ታሪካዊ ቀን ነበረች፡፡

ሆኖም ይህ ሁለቱ መሪዎች ለሰላም ስንል እንሰዋለን ሲሉ የተናገሩት ንግግር የፖለቲካ ሸቃጮችን ማስደንገጡ አይቀርም፡፡ በዋናው የንግድ ወረዳቸው ላይ ስለተመጣባቸው ሌላ አቅጣጫ ተከትለው አሁንም ይህንን ሕዝብ ለማፋጀት ሊሰሩ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡

መሪዎቹ ይህንን ሰላም ከልብ ለማምጣት፣ ይህንን በታሪክ አብሮ ገዲል ሰርቶ በአንድ መቃብር የወደቀን ሕዝብ፣ ይህንን ለአገር ምሥረታና ሉዓላዊነት ክብር ሲል በአንድ ገደል የተዋደቀን ሁለት ሕዝብ መልሶ አንድ የማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እጃቸው ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ፕሮጀክታቸው ባሰቡት ልክ እንዲሳካለቸው ሁላችንም ልንተባበራቸው ይገባል፡፡ እነርሱ ደግሞ ከዋናው ስራቸው በተጨማሪ የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን አለባቸው፡፡

1ኛ-በየቀኑ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰሙ፣ የጦርነት አዋጅ እና ቀረርቶ የሚያሰሙ ሚዲያዎቻቸውን በአንድነትና ሕብረት ላይ እንዲሰሩ ማድረግ፤ በየሬዲዮና ቴሌቭዥኖቻቸው እየመጡ፣‹‹መጣንላችሁ ጠብቁን››፣‹‹ኑና እንተያያለን›› እያሉ የሚሸልሉ ጋዜጠኞችን፣ የሚዲያ እንግዶችን ወዘተ ከወዲሁ ጠብሰቅ ባለ ማስጠንቀቂያ መገሰጽ፡፡

2ኛ-ይህንን ሁለት ታሪካዊ ሕብረት ያለውን ሕዝብ በመነጣጠል ሥልጣን ለማግኘት ሲሉ ኧረ ጎራው ሲሉ የሚውሉ የመንግሥት ሹማምንት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ፤ የእነዚህ ባለሥልጣናት ዋነኛ አላማ ከግል ጸብ እንጂ ለሕዝብ ከማሰብ የመነጨ እንዳልሆነ ጥርት ባለ ቋንቋ ማጋለጥ፤

3ኛ-ሁለቱም ክልል ላይ ያሉ አድራሻቸው የሚታወቅ፣ አንዳንዴም በራሳቸው በክልሎቹ መንግሥታት ቀለብ የሚሰፈርላቸው አክቲቪስቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሁለቱን ሕዝብ የጋራ መገለጫዎች እንዲያጎሉ፣ ያን ማድረግ ካልቻሉ ግን ቢያንስ አርፈው እንዲቀመጡ በሚገባ መገሰጽ፤ ለማለያየት ሲሰሩም ወደ ሕግ ማቅረብ፤

4ኛ- በሕዝባዊ ስብሰባዎች ላይ እርካሽ ተወዳጅነትን ለማምጣት ሲባል፣‹‹እነ እንትና ጠላቶቻችን ናቸው›› የሚል ተናግሮ አናጋሪን በሕግ እንዲጠየቅ ማድረግ
እነዚህን ተግባራት መከወን ሰላሙን ጥልቀት ያለውና ዘላቂ ያደርገዋል፡፡

ሰላምና ፍቅር ለአማራና ትግራይ  ሕዝቦች፣ አንድነትና ሕብረት ለጎንደርና ሽረ ሰዎች፣ መዋደድና ሰላም ለሰሜን ኢትዮጵያዊያን!!

ብራቮ ገዱ፣ቪቫ ደብረጽዮን!!!!!

የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close