Connect with us

Ethiopia

ስለአብን ምሥረታ እውነቱ ይኸው!

Published

on

ስለአብን ምሥረታ እውነቱ ይኸው!

ስለአብን ምሥረታ እውነቱ ይኸው!
(ጋሻው መርሻ እንደጻፈው)

ይህን ባልጽፈው ደሥ ይለኝ ነበር፣ የሚያውቁንን ሠዎች ጨምሮ አብንን በክፉ የሚከሡት በመብዛታቸው ግን ጻፍኩት
…..

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እንዴት ተመሠረተ የሚለውን መንገር አሁን ጊዜው እንዳልሆነ አውቃለሁ። ይሁን እንጅ በረከት ሥምኦን መሠረተው፣ አዴፓ ቀፈቀፈው፣ ህወሐት ጋር መፈንቅለ መንግሥት ሊሞክር ነው፣ ኦነግ ጋር አብሮ እየሠራ ነው አይነት ክስ ከዚህም ከዚያም ሲበረክት “ድንጋይ የሚወረወረው ፍሬ ወደያዘ ዛፍ ነው” ብለን ንቀን ልናልፈው ሞክረን ነበር። ይሁን እንጅ ያ ሁሉ ድካማችንን እያወቁ፣ ጓደኞቻችን የነበሩ ሠዎች ሳይቀር ስማችንን እየጠቀሡ በክፉ ሲያነሡን ዝም በማለታችን ነገሩ እውነት እንደመሠላቸው አንዳንድ ቅን ሠዎች በተለያዬ ዘዴ ይጠይቁናል። እውነት ነው ለማለት የመገደዳቸው ምሥጢር ደግሞ ከሳሾቹ የቀድሞ ወዳጆቻችን መሆናቸው ከእኛ ዝምታ ጋር ተጨምሮ እንደ እውነተኛ ምሥክር ወሥደውት መሆኑ ነው። የአብንን ምሥረታ በአጭሩ ልግለጽ

አንድ ቀን ከቤቴ ቁጭ ብየ ሥለ አማራ መደራጀት አሥፈላጊነት መጻፍ ጀመርኩኝ። አማራ እንደ ብላክ ሆል የደነደነ እና ለማንም የማይደፈር አደረጃጀት ሊኖረው ይገባል እያልኩኝ ጻፍኩኝ። የራሴን ጽሁፍ መልሸ ሳነበው ያንን አይነት አደረጃጀት እውን እንዲሆን ሻትኩኝ። ሥራ መጀመር አለብኝ ብየ ተነሳሁ። ከራሴ ጋር ብዙ ተሟገትኩኝ። ቀደም ብሎ የሠማያዊ የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ ሆኘ ብዙውን የሀገራችንን ክፍል ዞሬ ህዝብን በአንባገነኖች ቀንበር ሥር ማደራጀት ምን ያክል አደገኛና አድካሚ እንደሆነ አውቀዋለሁ።

ይሁን እንጅ ሁልጊዜ ለቅሶ ከመቀመጥ ሞክሮ ማየት የተሻለ ነው በሚል በግሌ አማራ አቀፍ ድርጅት መኖር አለበት በሚል ወሠንኩኝ። ሀሳቤን ያኔ እኔ ቤት እየመጣ አብሮኝ ያድር ለነበረ ጓደኛዬ ለሲሳይ አልታሠብ ነገርኩት። ከብዙ ሙግት በኋላ ተሥማማን። በማግስቱ ለጋዜጠኛ በላይ ማናዬ አጫወትነው። በላይ ጋር ተሥማማን። እንቅስቃሴ ጀመርን። እንቅሥቃሴው እጅግ ጥናትን መሠረት አድርጎ ጥንቃቄ በተሞላበትና ምስጢር በሆነ መልኩ ተጀመረ። ቀጥሎ በጓደኝነት ለረጅም ጊዜ የምናውቃቸውን ልጆች መቅረብ ጀመርን። አሁን እየከሠሡን ያሉ ወጣቶችንም አናገርን። ይሁን እንጅ ወቅቱ የአማራ ተጋድሎ የተፋፋመበት ሥለነበረ አማራ በምንም አይነት ሁኔታ ተሠባስቦ ቢገኝ የሚጠብቀው ሞት እና እሥር ሥለነበረ አንዳንዶቹ ፈሩ። ሌሎቹ ደግሞ የትጥቅ ትግል ነው የሚያዋጣው በሚል ምክንያት ራቁን። ያኔ አንድ ሠው ብርቅ ሥለሆነ አንድ ሠው ለማግኘት አርባምንጭና ጎንደር ድረስ ተጉዘናል። በዚህ ሁኔታ አሁን ያሉት የአብን ትንታግ ወጣቶች ተሠባሠቡ። ይህ ሁሉ ሲሆን አብዛኛው ሠው ምን እየተካሄደ እንደነበረ አያውቅም ነበር። በ

እርግጥ ለአንዳንድ ውጭ ሀገር ላሉ አክቲቪስቶች (ለሙሉቀን፣ ምሥጋናው፣ አያሌው፣ መሳፍንት፣ ሄኖክ አበበ…) ለመሳሰሉት ነገሩን ምሥጢር አድርገው እንዲይዙት አድርገን ተናግረናል። ይህ ሁሉ የሆነው 2009 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ነው። አንድ ቀን አራት ኪሎ ተሠባስበን ሥንለያይ ደህንነቶች ሊገድሉኝ እንደሚችሉ ዝተውብኝ ሄዱ። ከፍተኛ የሆነ ክትትልና ማሥፈራራት ተሞከረ።

በወቅቱ እኔ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለው ልዩነት ጠፍቶብኝ ሥለነበረ ብዙም አልደነቀኝም ነበር። አንድ አብሮን የነበረ ሠው ግን በሶሻል ሚድያ ሥሜን አጥፍቶ ተለየኝ። በእርግጥ ዝም ብለው የተለዩንም ነበሩ። የሆነው ሆነና ሲዝቱብን የነበሩ ሠዎች ዛሬ እምጥ ይግቡ ሥምጥ አይታወቅም። በትግላችን እነሡም የሚገባቸውን እኛም የሚገባንን ቦታ ይዘናል። ይህ ሁሉ አልፎ በ2010 ህዳር ላይ ብዙ ሠዎችን አሠባስበን ሥለነበር ለምርጫ ቦርድ ፈርመን አሥገብተን እንቅሥቃሴ ጀመርን። በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ መካከል ቅድመ ጉባኤ እናድርግ በሚል ባህር ዳር ላይ ተሠባሥበን ሥንወጣ ተይዘን ተደብድበን ታሠርን። ያኔ ከሞት እንዳመለጥን በቦታው የነበሩ ጓዶች የሚረዱት ነው። ከዚያ ሁሉ የተቀባበለ መሳሪያ አፈሙዝ አምልጠን ለዛሬ መብቃታችን በራሡ ታሪክ ነው።

በታሠርን ጊዜ ከእሥር ቤት ውጭ የነበሩ ጓዶቻችን ነገሩን በደንብ አቀጣጥለውት ሥለነበረ ያኔ ብዙው ህዝብ አወቀን። እሥከዚያች ቀን ድረስ እንዴት ባለ ችግር አልፈን ከዚያ እንደደረስን የምናውቀው እኛው ነን። አሥቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሆኑ ሠብሠብ ለማለት እንኳን እንዴት አሥቸጋሪ እንደነበረ፣ አንድ ሁለት እያልን ቀሥ በቀስ ከአንድ ጓደኛችን ቤት እየገባን ሥንት ቀን ተሠባሥበናል። ይህ ሁሉ ታሪክ ነውና በጊዜው ዘርዘር ብሎ ይገለጻል። ድካሙ ግን እሥካሁን ድረስ ይሠማኛል።

ይህ ሁሉ ሆኖ አብን ተመሠረተ። የአብን ምሥረታ እለት ገና ከአዳራሽ ሳንወጣ የትግራይ አክቲቪሥቶችን ጨምሮ የአንድነት ኃይል ነኝ ባዩ ወደ ጨቅላው ድርጅት ድንጋይ መወርወር ጀመረ። በሙሉዓለም የባህል ማዕከል የተሠባሠበው የአማራ ህዝብ የእምባ ጎርፍ ሲያወርድ እኔ ተጨንቄ ነበር። በእውነት የዚህን ህዝብ ተሥፋ መሸከም እንችል ይሆን? በሚል ውጥረት ነፍሴ ተጨነቀች። ይሁን እንጅ ፈጣሪም እረድቶን በተወሠነ ደረጃም ቢሆን የህዝባችን ተሥፋ እንድንሆን አደረገን። ይህ ሲሆን ማየት የማይፈልጉ ኃይሎች ከዚህም ከዚያም አሉቧልታና እርግማን ማውረድ ጀመሩ። በእርግጥ ከላይ እንዳልነው “ድንጋይ የሚወረወረው ፍሬ ወደያዘ ዛፍ ነው” ብለን ዝም ለማለት ሞክረን ነበር። የነገሩ አድማስ መሥፋት ግን ጉዳዩን በደንብ ማብራራትና የሀሳብ ብዥታ ያለባቸውን ሠዎች መታደግ ይኖርብናል በሚል ይህንን ጻፍኩኝ።

የአማራ ህዝብ ላይ ከተጫወቱበት ሠዎች አንዱ ምን አልባትም ዋነኛው በረከት ሥምኦን ነው። ለዚህም ህዝባችን ይህን ግጥም ሸልሞታል፦

በረከት በሠው በሠው ቤት ሲገባ ሲወጣ፣
ከእኔም ቤት አልቀረ መርገምት ይዞ መጣ።

በማለት የበረከትን መርገምትነት ተናግሯል። ይህንን የሚያውቁ መሠሪዎች አብንን ከበረከት ጋር ማያያዝ መረጡ። በእርግጥ የአማራ ህዝብ በረከትን አብዝቶ ሥለሚጠየፈው ከእሡ ጋር የተያያዘን በሙሉ መጠራጠር ይችላል የሚለው የተጠና የያ ትውልድ ንቅዘት የተሞላበት አካሄድ በጊዜው ባንኖር እንኳን በጡረታ ዘመናቸው በጻፉት ጥራዝ ማወቅ በመቻላችን የነገሩን ክፉነት ለመረዳት አልቸገረንም። እውነቱ ግን በረከትን በአማራ ምድር ዝር እንዳይል ያደረጉት የአብን ልጆች የመሆናቸው ነገር ነው። የኃይቅ፣ የወግዲ፣ የማርቆስ አድባሮች ይመሥክሩ! ብአዴንም የልብ ልብ አግኝቶ እነ በረከትን ያባረረው አብንን ተማምኖ ለመሆኑ ምሥክር ነው።

አሁን አብን ግዙፍ ድርጅት ነው። ብዙ የተማሩና ለአማራ የሚያስቡ ጭንቅላቶች በአብን ዙሪያ ተኮልኩለዋል። ምንም ቢመጣ የማይበገር አደረጃጀት ፈጥረናል። ይኸ ተመስገን ነው! የአማራ አደረጃጀቶች እየበረከቱ ነው። ከአብን ጎን ለጎን የአማራ ወጣቶች በሚገባ ተደራጅተዋል፣ ተማሪዎች እየተደራጁ ነው፣ የክህምና ባለሙያዎች ተደራጅተን የሚደነቅ ሥራ እየሠሩ ነው፣ የህግ ባለሙያዎች እየተሠባሠቡ ነው፣ ዲያስፖራው ወደ ቀልቡ እየተመለሠ ነው፣ ግዙፍ የአማራ ሚድያ እየመጣ ነው። የአማራ የቢዝነስ አክሲዮኖች እየገሠገሡ ነው። አሁን የሚቀረን እነዚህን አደረጃጀቶች ማናበብ ብቻ ነው። የዘላለም ጠላቶቻችን በአማራ ፋኖ ተገርፈው መቀሌ ከተባለ በረተ ከከተሙ ሠነባብተዋል። ህወሐት ከአሁን ወዲያ የሽፍታ ሥራ ከመሥራት ባለፈ የሚያመጣው ምንም ነገር አይኖርም። ይህ ሁሉ እየሆነ ሳለ ከውሥጥም ከውጭም የአማራን አደረጃጀት ለመሠነጣጠቅ የሚጥሩ ነቀርሳዎች አልታጡም። ገና ለገና አብን የአማራን ምድር ከተቆጥልጠረው ለእኛ መግቢያ አናገኝም ያሉ ነጋዴዎች ከተራ አረቂ ቤት ጀምሮ እሥከ ውሥኪ ቤት ድረስ በተዘረጋ የሀሜት ሠንሠለት ሥም በማጥፋት ተጠምደዋል። አንድ ነገር ግን አልተረዱም። የአማራ ትግል በድማሚት እንኳን ሊፈራርስ የማይችል የመሆኑን ምሥጢር።

ተጨማሪ፦ አሁን በአንብ ላይ የተነሱት ጓደኞቻችን በተደጋጋሚ አብረን እንድንታገል ያናገርናቸውና የተለያየ (በዋናነት ፍርሃት) ምክንያት እየዘረዘሩ የተሸበለሉ ናቸው። ዛሬ ሁሉም እኩል የሚሰለፍበት ወቅት ላይ ደረሥንና እኩል አወራን! ይሁን እሥኪ!

አማራ በልጆቹ ትግል ታሪኩን ያድሳል ማለትስ ይህም አይደል!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close