Connect with us

Ethiopia

የገዱ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ! | ማዕረግ ጌታቸው

Published

on

የገዱ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ! | ማዕረግ ጌታቸው

የገዱ ፖለቲካዊ አጣብቂኝ ! | ማዕረግ ጌታቸው

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው የፖለቲካ አጣብቂኝ በዘመን የሚረታ አልሆነም፡፡ ባለፈው አመት በዚህ ወቅት በወለድያ መከላክያው የወሰደው እርምጃ ከዛሬው አለመለየትም ለዚህ ምስክር ነው፡፡ በርግጥ ርዕሰ መስተዳደሩ ያለፉትን ጥቂት ወራት የለወጥ ኃይል ተብለው በየአደባባዩ ተንቆለጳጵሰዋል፡፡ በየከተሞችም ፎቷቸው በጉልህ የሚታየበት ቦታ ላይ ተቀምጦል ፡፡ ነገር ግን አቶ ገዱ ፋታ አግኘተዋል ለማለት ያዳግታል፡፡ ወዲህ ክንፍ ያወጣው የክልሉ የብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ወዲያ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ ያለው የኃይል ሚዛን መዋለል እንቅልፍ ነስቷቸዋል፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም በክልሉ የሚሰተዋለው አለመረጋጋት በተለይም የቅማንት ማኅበረስብ ግጭትም ለሰውየው ስላም መንሳቱ አይቀርም፡፡

በዚህ የተነሳም የርዕስ መስተዳደሩ እያንዳንዱ ውሳኔ ፖለቲካዊ መነታረኪያ ይሆናል ፡፡ አቶ ገዱ በኢህአዴግ ላይ ጨክነው ስለብሄርተኝነት ሲሰብኩ ሚሊዮኖች የሚጎርፉላቸው ሲሆን የድርጅታቸው ሰዎች ግን ፊት ይነሷቸዋል፡፡ ለስልጣን ያበቃቸውን ድርጀት አስበልጠው የክልሉን ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ የዘነጋ ንግግር ሲያደርጉ ደግሞ በክልሉ ያለው የከተማ ወጣት ዘለፋ ይከተላቸዋል፡፡ ይህ እውነት በአቶ ገዱ የፖለቲካ መንገድ ላይ የትናንት ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን የዛሬም ጭምር ነው፡፡

በአማራ ክልል ከሰሞኑን የሚሰተዋለውን አለመረጋጋት ተከትሎ በእሳቸውና በድርጅታቸው ላይ የሚሰነዘረው አስተያየትም ከዚህ ይመዘዛል፡፡ ርዕስ መሰተዳድሩ ትናንት የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ የተጋጋለው የማኅበራዊ ድረ-ገጾች ንትርክም መነሻው ይኼው ነው፡፡ አቶ ገዱ በሚመሩት ክልል በርካታ ንጹሐን የጥይት ሲሳይ ሁነዋል ፡፡በተዓምር የተረፉትም በሞትና በህይወት መካከል ተገኝተዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ርዕስ መሰተዳድሩ ጥቃቱን አውግዘው የሚመለከተው አካል በህግ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል ፡፡ እንዲህ ያለው መግለጫቸው ግን በእሳቸው ላይ የሚሰነዘረውን ትችት ያናረው እንጅ ያለዘበው አይመስልም፡፡

እዚህ ላይ አንድ ነገርን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ የአቶ ገዱ የትናንት መግለጫ ያልተዋጠላቸው ወገኖች እነማን ናቸው ?የሚለውን፡፡ የርዕሰ መሰተዳድሩ የትናንት አስተያየት ያልተዋጠላቸውን ወገኖች ከፊሎቹ በደረሰው ሀዘን ስሜታዊ የሆኑ ሲሆኑ የቀሩት ከግርግሩ ፖለቲካዊ ትርፍን ያሰሉ ናቸው፡፡ በሁለተኛው ጎራ ያሉትን የአቶ ገዱ አስተያየት ተችዎች እንመልከት፡፡ በዚህ ወገን ያሉት የአቶ ገዱ ተቃዋሚዎች ርዕስ መሰተዳድሩ መከላክያ ሰራዊትን በአግባቡ ስሙን ጠርተው ማውገዝ ነበረባቸው ይላሉ፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም አቶ

ለማ ከአመት በፊት እንዳደረጉት ሁሉ ከመከላክያ ይልቅ ውግንናቸው ለሚመሩት ህዝብ ማድረግ እንደነበረባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲህ ያለው አሰተያየት በቁሙ ሲመለከቱት ክፋት የሌለበት ቢመስልም በአቶ ገዱ ቦታ ላለ ፖለቲከኛ ግን የሰበዕና ራስን ማጥፋት መሆኑ አያከራክርም፡፡

የአማራ ክልል ርዕስ መስተዳደር ባለፉት ወራት የመጣውን ለውጥ ከፊት ከመሩት ተርታ መሆናቸው ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡ ይህ የለውጥ አጋፋሪነታቸው ደግሞ ከትናንት የተሻለ ስርዓትን አምጥቻለሁ የሚል አሰተሳሰበን የያዘ መሆኑ አያከራክርም፡፡ እንዲህ ከሆነ ለውጥ አመጣን የሚሉት አቶ ገዱ ተመልሰው መካላከያ ንጽሐንን ገደለ ብለው የሚወቅሱበት ምክንየት በጭራሽ ሊኖር አይችልም፡፡ ነገሩን “እንደ መከላከያ ሰራዊት ሪፎርም ያካሄደ ተቋም የለም” ከሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር አንጻር ከተመለከትነው ደግሞ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡

አቶ ገዱ በትናንት በስቲያ መግለጫቸው መከላከያ ሰራዊትን እንደ ተቋም ለመተቸት ቢሞክሩ በመጀመሪያ ከራሳቸው የለውጥ ሃዋርያነት በመቀጥልም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጋር ይላተሙ የነበረውም ለዚህ ነው፡፡ መሰረታዊው ነገር ግን ርዕስ መስተዳደሩ ካላይ ያልነውንም ዘንግትው ሰራዊቱን በጠንካራ ቃላት ቢያሰጠነቅቁ ፋይዳው ምንድን ነው የሚለው ነው?

አቶ ገዱ በሚመሩት ክልል ንጹሐን እንደተገደለባቸው መሪ ሁነው በአደባባይ ቢቃወሙ ይህ ነው የሚባል ጥቅምን ለሚመሩት ህዝብ ያስገኛሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ህዝብ ውስጥ ያለን ስሜት ተላብሶ ከመሪነት በራቀ መንገድ ነገሩን ከማባባስ ይልቅ በፖለቲካዊ ቃላት ሀሳባቸውን መግለጻቸው የሚደነቅ ይመስላል፡፡ በተለይም የፌደሬሽኑ አባል ሁነው ተወክየበታለሁ የሚሉትን የፌደራል መንግስት ሰራዊት መተቸትም ከፖለቲካ አንጻር የዜሮ ድምር ጨዋታ መሆኑ አያከራክርም፡፡ እናም አቶ ገዱ ለክልላቸው ህዝብ ጥቅም እውነተኛ ታጋይ መሆን አለመሆናቸው ሊመዘን የሚገባው በመንግስትና በፓርቲያቸው ውስጥ በሚያደርጉት ትግል አንጅ በሚዲያ በሚሰጡትን መግለጫ ቃላት ማማር አይደለም ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close