Connect with us

Ethiopia

የኦነግና የመንግስት፡ የአቶ ደውድ ኢብሳና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውዝግብ…

Published

on

የኦነግና የመንግስት፡ የአቶ ደውድ ኢብሳና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውዝግብ... |  ፀጋው መላኩ

የኦነግና የመንግስት፡ የአቶ ደውድ ኢብሳና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ውዝግብ… |  ፀጋው መላኩ@DireTube

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ሰሞኑን ከመምህራን ጋር ባደረጉት ውይይት ከኦነግ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም ስለኦነግ ሲናገሩ ፈተና እና ቀለል አድርገው ነበር፡፡ አሁን ግን ቆጣ ባለ ድምፅና ቆምጨጭ ባለ ፊት ነበር አስተያየታቸውን የሰጡት፡፡ ደመውዝ ይጨመርልን ያሉ ወታደሮች የአራት ኪሎን ቤተመንግስት ቅጥር ጊቢ ጥሰው በገቡበት ዕለት ከፑሽ አፑ መልስ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚያው አጋጣሜ ስለኦነግ እንቅስቃሴ ሲጠየቁ ቀለል አድርገው ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

ከዚያ በኋላ በፓርላማ ቀርበው ስለወታደሮቹ የቤተ መንግስት ጊቢን ጥሶ መግባትን አስመልክተው በዕለቱ ማብራሪያ ሲሰጡ ደግሞ ለተፈጠረው ድንገተኛ ድርጊት ምላሽ የሰጡበት መንገድ ውጥረትን በሚያረግብና ሀገርንም ያለመረጋጋት ጥርጣሬ ውስጥ በማይከት መልኩ መሆኑን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡ የፑሻፕ ስፖርቱ እንደዚሁም መግለጫውን ለህዝብ ሲሰጡ የታዩበት የተዝናና የፊት ገፅታም ከዚሁ ጋር የተያያዘ እንጂ ውስጣቸው ግን ር…ር!… ..ድ..ብ..ን…! ብሎ እንደነበር ነግረውናል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከወራት በኋላ በዚሁ በመምህራኑ መድረክ ላይ ስለ ዳውድ ኢብሳው ኦነግ ሸኔ ሲናገሩ ግን ያንን የውስጥ ስሜታቸውን ለመደበቅ የሚያስችላቸውን የተዝናና ፊታቸውን ግን ሊያሳዩን አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በንግግራቸው መሀል የስሜት ግለታቸው እየጨመረ ሄዶ የኦነግን የወቅቱን አካሄድ አካፋን አካፋ በማለት ያህል ነው የገለፁት፡፡

የአቶ ደውድ ኢብሳው ኦነግ በድል አጥቢያ አዲስ አበባ ገብቶ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ባለበት ሰዓት የገለሳ ዴልቦው ኦነግ አዲስ አበባ ገብቶ እኔም አለሁ ብሏል፡፡ ሆኖም በአቶ ገለሳ ዴልቦ የሚመራው ኦነግ ከስም አንድነት ውጪ ተግባሩን ለይቶ ከለማ ቲም ጋር በጋራ ለመስራት ሁሉን አቀፍ ንግግር በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ኦነግ በተለያዩ ጊዜያት የመከፋፈል አደጋ ገጥሞታል፡፡ ከዚህም ባለፈ ከመስራቹ አቶ ዲማ ነገዎ ጀምሮ እስከ አቶ ሌንጮ ለታ ድረስ ያሉት ከፍተኛ አመራሮቹ ከድርጅቱ ውጪ ሆነው የራሳቸውን ፓርቲ ከመመስረት ባለፈ፤ በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አማካኝነት ከከልሉ ገዢ ፓርቲ ኦዴፓ ጋር በመዋሃድ በሥራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ድርጅቱ የመከፋፈሉ አደጋ በተለያዩ ጊዜያት የገጠመው ሲሆን፤ አሁን ባለው ሁኔታም ሶስት በድርጅቱ ስም የሚጠሩ የተለያዩ ግንባሮች አሉ፡፡ እነዚህም በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ሸኔ ኦነግ፣ በአባ ነጋ ጃራ የሚመራው የኦነግ አንድነት እና በአቶ ገላሳ ዴልቦ የሚመራው ኦነግ ሽግግር ናቸው፡፡ ስመ ሞክሼዎቹ ሰለስቱ ኦነጎች በቀጣይ ወደ ተጨማሪ ስንት ኦነግነት እንደሚሸነሸኑም አይታወቅም፡፡

አሁን ካለው የድርጅቱ ክፍፍል አንፃር ሁለት አበበዎችን በአባታቸው እንደምንለያቸው ሁሉ ኦነግንም እስከነአባቱ ኦነግ አንድነት፣ኦነግ ሽግግርና ኦነግ ሸኔ እየተባለ ካልተጠራ በስተቀር እንዲሁ በደምሳሳው ኦነግ የሚለው ስም የአንድ ፓርቲ ወይንም ድርጅት መጠሪያ ስም መሆኑ አክትሞለታል፡፡ ምን አልባት ኦነግ ሸኔ ወይንም ሌላው አንጃ ከነ አባት ስሙ የሚከፈል ከሆነ ደግሞ አንዱን ከሌላው ለመለየት የአያት ስም ፍለጋ ለመሄድም እንገደድ ይሆናል፡፡

ከእነዚህ ሶስቱ የኦነግ አንጃዎች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ከመንግስት ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የገባው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራውና ኦነግ ሸኔ በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው ግንባር ነው፡፡ በተለያየ አቅጣጫ የወጡ መረጃዎች እንደሚመለክቱት ከሆነ ግንባሩ በምዕራብ ኢትዮጵያ ዜጎችን የሽምቅ ውጊያ ሥልጠና ከመስጠት እስከ ደፈጣ ውጊያ የዘለቀ ኦፕሬሽን በማከናወን ላይ ነው፡፡ ሆኖም መንግስት እየወሰደ ባለው አፀፋዊ እርምጃ የኦነግ ሸኔ ኃይል ከበድ ያለ ጉዳት ሳይገጥመው አልቀረም፡፡

ለመሆኑ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ሸኔ ኦነግ ለምን እንደዚህ አይነት ውጥረት ውስጥ መግባቱን ለምን ፈለገ የሚለው ጉዳይ በብዙ አቅጣጫ ሊያነጋግር ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተለያዩ ምክንያታዊ መላምቶች ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡

አንዷን ብቻ መዘዝ አድርገን እንመልከታት፡፡

አንዱ አቶ ዳውድ እና ጓዶቻቸው ከመሸጉበት አስመራ ከተማ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ በአዲሱ የኢትዮጵያ መንግስትና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ለውጥ ከልብ ያለማመናቸው ጉዳይ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ኤርትራ ከኦብነግ እስከ ኦነግ ብሎም አስከ አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሉ የኢትዮጵያ ምንግስትን በነፍጥ ለመፋለም የትጥቅ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉ ሃይሎችን በጉያዋ አቅፋ ቆይታለች፡፡ ሆኖም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በድንገት መቶ ሰማኒያ ዲግሪ ለውጥ ውስጥ መግባቱ በኤርትራ ለመሸጉ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች ዱብዳ ነበር፡፡

በጥቂት ቀናት ልዩነት ውስጥ የሁለቱ ሀገራት አስርት ዓመታትን ያሰቆጠረ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ውጥረት መርገቡ በኤርትራ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚ ኃይሎች በቂ የሆነ የሥነ ልቦና ዝግጅት እንኳን ማድረግ ሳይችሉ የኤርትራን ምድር የመልቀቃቸው ጉዳይ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በአንድ ዲንጋይ ሁለት ወፍ እንዲሉ፤ ከኤርትራ ጋር ሰላም ሲያወርዱ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እዚያው ኤርትራ ምድር ላይ የመሸጉ የኢህአዴግ ተቋሚዎችን የመጨረሻ ምሽጎችንም እየደመሰሱ እንደነበር ግልፅ ነው፡፡ ለምን ቢባል? በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀል ሰላም መውረዱ የአንዱ መንግስት ተቃዋሚ በሌላው ሀገር እንዳይመሽግ ያደርጋልና ነው፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም አወረዱ ማለት፤ አርበኞች ግንቦት ሰባትም ሆነ ኦነግ ወይን ሌላ ተቀዋሚ ኃይል በኤርትራ ያለው ህልውና አከተመ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የትኛውም ታጣቂ የፖለቲካ ድርጅት አንድም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ተባብሮ የለውጡ አካል መሆን ነበረበት፤ አለበለዚያም የሚቀርው ብቸኛ አማራጭ የኤርትራን ምድር ለቆ መውጣት ነው፡፡

በመሆኑም በፍጥነት ከተለወጠው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት አኳያ በኤርትራ መሽገው የነበሩ ታጣቂ የፖለቲካ ድርጅቶች በሁለት ተከፍለው የሚታዩ ናቸው፡፡ እነዚህም ለውጡን ከልብ ደግፈው ሀገር ውስጥ የገቡና ለውጡን ባይፈልጉትም ከአዲሱ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ጋር በተያያዘ በካልቾ ፖለቲካ ተገፍተው ወይንም ተጎትተው የኤርትራን ምድር ለቀው የወጡ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ ከልብ ሳያምኑ ሀገር ውስጥ ከገቡት ኤርትራ መሻጊ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የአቶ ደወድ ኢብሳው ኦነግ ሸኔ በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ አዲሱን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ተጠቅመው በሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ ትግል እንዲያደርጉ ጥያቄ ሲቀርብላቸው ብዙም ፍላጎት ያላሳዩት አቶ ዳውድ፤ ከኤርትራ ምድር መልቀቅ ግድ የሆነባቸው ከሁለቱ ሀገራት አዲሱ ግንኙነት ባሻገር በፕሬዝደንት ኢሳያስ ጫና እንደዚሁም በጊዜው አስመራ ድረስ ጉዞ ባደረጉት አቶ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ ግፊት ነው፡፡

እናም በጫና እና በግፊት ውስጥ የወደቁት አቶ ዳውድና አመራሮቻቸው ለውጡን ተቀበሉም፤አልተቀሉም ከዚያ በኋላ በኤርትራ ምድር መቆየቱ የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ሲረዱ የግድ ሀገር ውስጥ መግባት ነበረባቸው፡፡ እናም የድርጅቱ አመራሮች በቦሌ፤ አንድ ሺህ ሶስት መቶ አካባቢ የሚሆኑት የድርጅቱ ታጣቂዎች ደግሞ ትጥቃቸውን ፈተው በዛላንበሳ በኩል ሀገር ውስጥ ገቡ፡፡

አቶ ዳውድ በለውጡ ጭላንጭል ውስጥ ጥቂት የተስፋ ጠብታ እንኳን ማየት እንዳይችሉ ያደረጋቸው ደግሞ በአዲስ አበባ የተደረገላቸው ከፍተኛ ህዝባዊ አቀባበል ሥነ ሥርአት ነበር፡፡ አቶ ዳውድ በለውጡ መንፈስ ውስጥ የነበረውን የድጋፍ አቀባበል ከለውጡ አውድ ውጪ የተረዱት ይመስላል፡፡ እሳቸውና ድርጅታቸው በአሸባሪነት በተፈረጁበት ቅድመ አቢይ ኢህአዴግ ሚሊዮኖች ወጥተው እሳቸውን በአደባባይ መቀበል በውን አይደለም በህልም ሊታሰብ የማይችል ነው፡፡

ይህ የሳቸው ታሪክ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ተሰዳጅ ፖለቲካ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ነው፡፡ለውጡ ኦነግን ጨምሮ በማናቸውም የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች የመጣ ለውጥ ሳይሆን፤ ባልተደራጀ ህዝብ እምቢተኝነትና መስዋዕትነት የተገኘ መሆኑ ቢታወቅም፤ በለውጡ ላይ የጎደለውን ከመሙላት፣የቀረውን ከመጨመር፣የተረሳውን ከማስታወስ ይልቅ “ሻማውን እናጥፋው” የሚመስል አካሄድ ሲታይ፤ ለመሆኑ ከመጀመሪያው ትግሉ ለህዝብ ነበር? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡

እንግዲህ በዚህ መልኩ የተጀመረው የፖለቲካ ልፊያ መልኩን ቀይሮ ከዚያ በኋላ ሁኔታዎች ቀስ ቀስ መለወጥ የጀመሩት አቶ ዳውድ የመጀመሪያውን የቃላት ተኩስ ካሰሙ በኋላ ነበር፡፡ አመራሩ የመጀመሪውን መነጋገሪያ አጀንዳ ያቀበሉት ከትጥቅ መፍታት ጋር በተያያዘ “ማነው ትጥቅ ፈቺ?፤ማነውስ አስፈቺ? ያሉ ቀን ነበር፡፡

ይህች አባባል ሰፊ የማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኗ ደግሞ መንግስትን ይበልጥ ስለከነከነችው በአንድ ራስ ሁለት ምላስ ሊኖር እንደማይችለው ሁሉ በአንድ ሀገር ሁለት ትጥቅ ሊኖር የማይችል መሆኑን በሚገልፅ መሆኑን በመግለፅ ኦነግን በጥብቅ አስጠነቀቀ፡፡ እናም አሁን ከዳውድ ኢብሳው ኦነግ ሸኔ ጋር የተገባው የፖለቲካ ሰጣ ገባ አንዱ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችለው ይሄው በለውጡ ያለማመን ምክንያት ነው፡፡

አቶ ዳውድ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ከአሜሪካ ድምፅ የአማርኛው ክፍል ጋር ባደረጉት ቆይታ “ኢህአዴግ ራሱ ለፈጠረው ችግር የመፍትሄ አካል መሆን አይችልም፡፡” በማለት አሁን ያለውን የቲም ለማ የለውጥ ኃይል መሪነት ሲያጣጥሉ ተደምጠዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በ2010 መጨረሻ ክረምት ላይ በአሜሪካ ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሽግግር መንግስት እንዲቋቋም ምክር አዘል መሰል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ስልታዊ ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጊዜው “በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጦ ህዝብን ለማገልገል ከሆነ ሁሉም መንግስት ቆይታው በጊዜ የተገደበ የሽግግር መንግስት ነው፡፡ ከዚህ ውጪ የሽግግር መንግስት የሚፈለግ ከሆነ ስጋት አይግባችሁ እኔ አሸጋግርላችኋለሁ” በማለት ነበር ሌላ የሽግግር መንግስት የማያስፈልግ መሆኑን የገለፁት፡፡

ከአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ አቶ ዳውድ በበኩላቸው “ቡድኖች እና የድርጅቶች የሚያስተናግድ አንድ ሁሉን አሳታፊ የሆነ ሽግግር ያስፈልገናል፡፡” በማለት ነገሮች እንደ አዲስ የሚጀመሩበት ሁኔታዎች የሚያስፈልጉ መሆኑን ሲገልፁ ተደምጠዋል፡፡ ከዚህ አለፍ ስንል አቶ ዳውድ ገና አስመራ እያሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ማብራሪያቸው ለታጣቂ ኃይሎች ባስተላለፉት ጥሪ ትጥቅ ትግል ፋሽን ያለፈበት መሆኑን በመግለፅ ኦነግ፣ኦብነግም ሆነ አርበኞች ግንቦት ሰባት ሀገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲታገሉ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው፡፡

አቶ ዳውድ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዚያው በአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ አማርኛው ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ትጥቅ ትግል ፋሽን ያለፈበት ነው መባሉ ያስከፋቸው መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡…….. “የትጥቅ ትግል ፋሽን ያለፈበት ነው ብሎ መናገር፤ የእኛን አባሎችና ወጣቶች ያስከፋል፡፡ ወደ ትጥቅ ትግል የገባንበት ዋነኛው ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የተዘረጋው ሥርዓተ መንግስትና የሚጠቀምባቸው መዋቅሮች ናቸው፡፡ ይሄ መዋቅር ደግሞ አሁንም አለ፡፡” ነበር ያሉት፡፡

ይህንን የአቶ ዳውድ ኢብሳ አባባል ማንም በዩቱብ ገብቶ ሊሰማው የሚችል እውታ ነው፡፡

እናም

“ትጥቅ ፍታ…..! ማነው ፈቺ?…….. ማነውስ አስፈቺ…..?

“የሽግግር መንግስት ያስፈልጋል” …… “የለም አያስፈልግም”

“እኛ እናሸጋግርላችሁን”…….. “እናተ የችግሩ አካል እንጂ የመፍትሄው አካል መሆን አትችሉም” የሚሉት የቃላት ልውውጦች በአቶ ዳውድ ኢብሳና በመንግስት መካከል እየተደረጉ ያሉ የበላ ልበልሃ ፖለቲካዊ ሙግቶች ናቸው፡፡ እና ይሄ የአቶ ዳውድ ኢብሳው ኦነግና የመንግስት የወቅቱ በላ… ልበልሀ የፖለቲካ ሂደት የፍፃሜው ጥግ የት ይሆን?

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close