Connect with us

Ethiopia

‹‹ኃላፊነት የጎደለው፣ ትክክለኛ ያልሆነ እርምጃ ተወስዷል፡፡›› አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

Published

on

‹‹ኃላፊነት የጎደለው፣ ትክክለኛ ያልሆነ እርምጃ ተወስዷል፡፡›› ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

‹‹ኃላፊነት የጎደለው፣ ትክክለኛ ያልሆነ እርምጃ ተወስዷል፡፡›› ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የሰሞኑን የምዕራብ ጎንደር ዞን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ በትላንትናው ዕለት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት አንድ የኮንስትራክሽን ድርጅት መኪኖቹን ከአንደኛው ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ በሞከረበት ወቅት በተፈጠረ አለመግባባት አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል፡፡

‹‹ባለፈው እሑድ (ታኅሳስ 28 ቀን 2011ዓ.ም) ጭልጋ አካባቢ በመንገድ ሥራ ላይ የሚገኝ ድርጅት በግጭ ምክንያት ሥራውን ለመቀጠል በመቸገሩ መኪኖቹን ከመተማ-አርማጭሆ ወደሚሠራው የመንገድ ፕሮጀክት ለማንቀሳቀስ ሞክሯል፡፡ በዚያ በአግባቡ እየሠራ ስለነበር፡፡ መኪኖቹን በሚያንቀሳቅስበት ጊዜ ግን ኅብረተሰቡ የተለያዩ ጥርጣሬዎች ስላደሩበት ግጭቶች ተፈጥረዋል›› ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

የተቋራጩን ተሽከርካሪዎች አጅቦ ይሄድ የነበረው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እንደነበር የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ ከአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ አንጻር ታጅቦ መንቀሳቀሱ ተገቢ እንደነበርና የተፈጠረው ሁኔታ ግን መሆን ያልነበረበት እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በተፈጠረው ግጭት አሳዛኝ በሆነ መልኩ ንጹኃን ዜጎች ጭምር ሞተዋል፤ በዚህም ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ቤተሰቦች በራሴና በክልሉ መንግሥት ስም የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እገልጻለሁ፤ መጽናናትንም እመኛለሁ፡፡ ሁኔታው አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ምንም ዓይነት ምክንያት ይቅረብለት በዚህ ዓይነት የግጭት ወቅት ንጹኃንን መጠበቅና ጥንቃቄ ማድረግ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን በግጭቱ ውስጥ ምንም ሚና ያልነበራቸውን ጨምሮ ጉዳት ደርሶባቸዋል›› ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት ይህን ዓይነት ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ መወሰድ አልነበረበትም፤ ችግሩ ቢያጋጥም እንኳ እሑድና ሰኞ እንደተደረገው በትዕግስትና በውይይት ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት መደረግ ነበረበት፡፡ ‹‹በውይይትና በትዕግስት ችግሩን ለመፍታት ጥረት አለመደረጉ በእጅጉ አሳዝኖናል›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድር ገዱ በድርጊቱ ማን ምን እንደፈጸመ ዝርዝሩን ከፌዴራል የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የሚያጣራ ቡድን ወደ አካባቢ በአስቸኳይ እንደሚላክ አስታውቀዋል፡፡

ዝርዝሩ ተጣርቶ ያልተገባና ተመጣጣኝ ያልሆነ እምጃ የወሰዱ አካላት በሕግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ እንደሚኖርም አቶ ገዱ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሕዝቡና መንግሥት በጋራ እንደሚሠሩ አመልክተዋል፡፡ ‹‹የሕግ አስከባሪ አካላት በሲቪል ኅብረተሰብ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ ይገባው ነበር፤ ሪፖርቱ በዝርዝር ወደፊት የሚጠናና ይፋ የሚሆን ቢሆንም እስካሁን ከአካባቢው አመራሮች በደረሰኝ መረጃ ኃላፊነት የጎደለው፣ ትክክለኛ ያልሆነ እርምጃ ተወስዷል››

በኮኪትም ይሁን በገንዳውኃ በደረሰው ጉዳት ከመከላከያ ጋር ኅብረተሰቡ ወደ ግጭት መግባቱ ተገቢ እንዳልነበር ያስታወቁት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹ግጭት ቢፈጠር እንኳ ሥርዓት ባለው መንገድ ለመፍታት ጥረት መደረግ ነበረበት፡፡ የኃይል አማራጭ በምንም መንገድ ተመራጭነት የሌለው በመሆኑ በደረሰው ጉዳት ኃላፊነት መውሰድ ያለበት አካል ኃላፊነት መውሰድ ይኖርበታል›› ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም በምዕራብ ጎንደር አካባቢ የእርስ በእርስ መገዳደል እየቀጠለ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አንስተዋል፡፡ ‹‹የእርስ በእርስ መገዳደሉ ዓላማ ቢስ፣ መዳረሻ የሌለው፣ ንጹኃንን ከመግደልና ከመጉዳት ባለፈ ምንም ዓይነት ጥቅም የሌለው ፀረ-ሰላም እንቅስቃሴ ስለሆነና ንጹኃኑን የአማራና የቅማንት ሕዝብ ለአደጋ ያጋለጠ አደገኛ አካሄድ ስለሆነ በአስቸኳይ መቆም አለበት›› ብለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በምዕራብ ጎንደር አካባቢ ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን ለመወጣት ሕጋዊና ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ የሚንቀሳቀስ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ከሁለቱም ወገን ታጥቀው ሰላማዊ የሆነውን ሕዝብ ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረጉ ያሉ ወገኖች በአስቸኳይ ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታረሙና አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ›› ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡፡

አጋጣሚውን በመጠቀም የክልሉ ሰላም እንዲናጋ፣ የሕዝቡንና የመንግሥትን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በማስተጓጎል የልማትና የሰላም እንቅስቃሴዎች እንዲደናቀፉ የሚደረግን ጥረት ለመቆጣጠር የክልሉ መንግሥት ሰፊ ሥራ እንደሚሠራም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል፤ ሕዝቡም በአንድነት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፀጥታ አካላት በክልሉ ውስጥ ሕግ እንዲከበርና ሰላም እንዲሰፍን መሰዋዕትነት እየከፈሉ ጭምር ከሕዝብ ጎን ቆመው እያበረከቱ ላለው አስተዋጽዖኦም ርዕሰ መስተዳድሩ ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ ‹‹የክልሉ ሁኔታ እንዳይረጋጋና ሰላም እንዲጠፋ ሕዝቡን እርስ በእርስ በማናቆር ወደ ግድያ፣ መጠፋፋትና የንብረት ውድመት የሚመሩ ኃይሎችን በመቆጣጠር ለሕግ እንዲያቀርብም ለፀጥታ ኃይሉ ጥሪዬን አስተላፋለሁ›› ሲሉም መልዕክት ማስተላለፋቸውን የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት ዘግቧል፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close