Connect with us

Ethiopia

የአይኤስና አልሸባብ ፉክክር በኢትዮጵያ…

Published

on

የአይኤስና አልሸባብ ፉክክር በኢትዮጵያ…

የአይኤስና አልሸባብ ፉክክር በኢትዮጵያ… | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ኢትዮጵያዊያንን በሊቢያ በረሃ ያረደው አይኤስ የተባለው የሽብር ሃይል አሁን እዚሁ አጠገባችን ሱማሊያ መግባቱ ተረጋግጧል፡፡ከቀናት በፊት በሸኘነው የፈረንጆቹ ዓመት የአውሮጳ ሕብረት ይፋ እንዳደረገው፣ አይኤስ ሱማሊያ ገብቶ በፑንትላንድና በሌሎች የአገሪቱ የወደብ ከተሞች ከትሟል፡፡

በመጪው የፈረንጆቹ ዓመት ከ2007 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ደግሞ በጸረ-አልሸባብ ውጊያ ላይ የተሰማራው የአፍሪቃ ሕብረት ጦር-አሚሶም-መቀነስ ይጀምራል፡፡ ከአካባቢው ሃገራት ደግሞ ኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ኡጋንዳና ጅቡቲ በርከት ያለ ሠራዊት በዘመቻው ላይ አሰማርተዋል፡፡

ይህ ጦር መውጣት እንዲጀምር ቀነ ገደብ የተቀመጠለት እንግዲህ በሱማሊያ ያለው የሽብር ቡድኖች በምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት ላይ ጥቃት የመሠንዘር እቅድ ላይ ሆነው ነው፡፡ አልሸባብ አብዛኛው ሠራዊቱ ከሱማሊያ ይሁን እንጂ ከኬኒያና ሱዳን፣ ከግብጽና ሞሮኮም እንዳሉት ይታመናል፡፡ ይህንን የታጣቂ ምልመላውን በቀጣይ አስፍቶ እንደሚቀጥልም ድርጅቱ በተደጋጋሚ ከሚለቅቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች መረዳት ይቻላል፡፡

አይኤስም ቢሆን ከአልሸባብ የተሻለ ገቢና ማማለያ ይዞ ስለመጣ (በኢራቅና ሶሪያ በርካታ የነዳጅ ጣቢያዎችን ያስተዳድር ነበር፤ ይህንን ነዳጅም በጥቁር ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ሲሸጥ ሰንብቶ ዶላር በመርከብ ጭኖ የመጣ ስለመሆኑ ይታመናል) የአካባቢውን ወጣቶች በቀላሉ ማማለል ይችላል፡፡

በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የሚታወቀው ምሥራቅ አፍሪቃም ለዚህ የሽብር ቡድን መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ ኑሮ አማርሮት ባሕር ሊያቋርጥ የተዘጋጀን መናኛ ሁሉ በሊቢያ በረሃዎች እየጠለፈ በማስቀረት ልምድ ላካበተው አይኤስ ሕንድ ውቅያኖስን የሚያቋርጡ ስደተኛ ወጣቶች በግድም በውድም (በጉልበትና በገንዘብ) የአይኤስ ወታደር የማይሆኑበት ምክንያት አነስተኛ ነው፡፡ ብዙ ስደተኛ ያላቸው ደግሞ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ራሷ ሱማሊያ ናቸው፡፡

እንዲያም ሆኖ አይኤስ በሱማሊያ አለሁ ለማለት ያህል ባሳለፍነው ዓመት ኃላፊነት የወሰደበትን ጥቃት አድርሷል፡፡ በቦሳሶ ወደብ ላይ ባደረሰው ጥቃት ሰዎችን ገድሏል፤ንብረትም አውድሟል፡፡

አይኤስና አልሸባብ በኢትዮጵያ፤ ኦሮምኛ የሥራ ቋንቋ?

አይኤስ ነፃ የሚያወጣቸውንና ካሊፌቱን የሚያውጅባቸውን ሀገራት በገለጸበት ካርታ ላይ እንዳስቀመጠው ምሥራቅ ኢትዮጵያ ኢላማ ነው፡፡ Ethiopia’s Strategic Importance: US National Security Interests at Risk in the Horn of Africa September 12 በሚል ርዕስ ላይ እንደሚነበበው ትንታኔ ለአልቃኢዳ የሚታዘዘው አልሸባብም ሆነ፣አይኤስ ከኢትዮጵያ ግዛቶች ቆርሶ በመውሰድ ታላቋን ሱማሊያ መፍጠር ላይ ልዩነት የላቸውም፡፡ሁለቱም እንግሊዞች ቀብረውት የሄዱትንና ኋላ ላይ ዚያድ ባሬ ሊያፈነዳው የሞከረውን የታላቋ ሱማሊያ ፕሮጀክት ይደግፉታል፡፡

ይሁን እንጂ አልሸባብ ከአይኤስ በበለጠ የኢትዮጵያን ወጣቶች ለመማረክ እየሠራ ነው፡፡ ለዚህም ከቡድኑ የሥራ ቋንቋዎች አንዱ አፋን ኦሮሞ እንዲሆን ወሥኖ በዚሁ ቋንቋም የተለያዩ መግለጫዎችን እያወጣ ነው፡፡

እነ ጃሰን እንደሚሉት አልሸባብ በፕሮፓጋንዳ መሣሪያዎቹ ለወትሮው ከሱማሊኛ በተጨማሪ ይጠቀም የነበረው ቋንቋ እንግሊዝኛ፣አረብኛና ስዋኅሊ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አፋን ኦሮሞም ተጨምሯል፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉና የተከፉ ወጣቶችን ትኩረት ለመሳብ የተከተለው ዘዴ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡

በዚህ ረገድ አይኤስ ግልጽ ነገር የለውም፡፡ በሚታወቁት ልሳኖቹ (አማቅና ዊላያት) በሱማሊያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የለቀቃቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችም ሆኑ ጽሁፎች አዘውትሮ ከሚጠቀምበት ቋንቋ ተሻግሮ እንደ አልሸባብ የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ሲሰጠቀም አልተስተዋለም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close