Connect with us

Ethiopia

ቁሳቁስን ማሻገር፤ ሕይወትን ሲያስገብር!

Published

on

ቁሳቁስን ማሻገር፤ ሕይወትን ሲያስገብር!

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን “ገንደውሃ” እና “ኮኪት” በተሰኙ ከተሞች የመከላከያ ሠራዊት አባላት፤ ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር በፈጠሩት ግጭት ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸው ተረጋግጧል። ለግጭቱ መንስኤ የሆነው በአካባቢው በመንገድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ የነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ ኢንዶውመንት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ሱር ኮንስትራክሽን የተባለው ድርጅት ንብረቶቹን ከአካባቢው ለማስወጣት መሞከሩ ተቃውሞ በማስነሳቱ ነው ተብሏል። በግጭቱ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አንዳንዶች ዘጠኝ መሆናቸውን ሲገልፁ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን እስከ 25 ያደርሱታል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት በትላንትናው ዕለት እንደዘገበው በምዕራብ ጎንደር ዞን ‹ገንደ ውሀ› እና ‹ኮኪት› በተባሉ ከተሞች ለሰዎች ሕይዎት ህልፈት እና ለአካል ጉዳት ምክንያት የሆነው በመከላከያ ሰራዊት አባላትና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረ አለመግባባት ነው ሲል የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የማህበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ጠቅሶ ዘግቧል።

በአቶ አደባባይ ገለፃ መሠረት ግጭቱ የተከሰተው ደግሞ ‹‹ሱር ኮንስትራክሽን›› የተባለ የመንገድ ሥራ ድርጅት ‹ከአይከል -ዙፋን› ሲሰራው የነበረውን የመንገድ ሥራ አቋርጦ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳን – ከመተማ ወረዳ ‹ኮኪት› ከተማ የሚያገናኘውን መንገድ ለመስራት ተሽከርካሪዎችንና የግንባታ ቁሳቁስ በማጓጓዝ ላይ እያለ ነው፡፡

ይህ የሆነውም ህብረተሰቡ ‹‹ሱር ኮንስትራክሽን›› የተባለው የመንገድ ሥራ ድርጅት ለአካባቢው ሠላም እጦት ምክንያት ነው ብሎ ስለሚያምንና ተገቢው ፍተሻ ሳይደረግ አከባቢውን ለቆ መውጣት እንደሌለበት ስለጠየቀ ነው፡፡ ‹ተሽከርካሪዎች እና የግንባታ ቁሳቁሱ እንዴት በሠላም ማለፍ እንደሚችሉ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣የዞኑ አመራሮችና የህብረተሰብ ተወካዮች ከትላንት በስቲያ ታህሳስ በ30 ቀን 2011 ዓ/ም ከረፋዱ 4፡00 አካባቢ ተወያይተው እንደነበረም ታውቋል፡፡

ተሽከርካሪዎቹ እየተፈተሹ በሠላም ወደ ሌላው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እንዲያልፉ የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች እና የህብረተሰቡ ተወካዮች ህብረተሰቡን እንዲያወያዩም ኃላፊነት ወስደው ነበር፡፡ ይህ ስምምነት በሂደት ላይ እያለ በዕለቱ ከቀኑ 9፡00 አካባቢ ‹‹የሱር ኮንስትራክሽን›› ተሽከርካሪዎች ‹መቃ› ከተሰኘ ቦታ ተነስተው ገንደ ውሀ ከተማ ሲደርሱ ነው ግጭቱ የተፈጠረው ተብሏል።

ህብረተሰቡን ለማወያየት ኃላፊነት የወሰዱት አካላት ውይይቱን ሳያጠናቅቁ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ተሽከርካሪዎቹን ለማሳለፍ መሞከራቸው ለግጭቱ መንስኤ እንደሆነ ታምኗል። በዚህም በመከላከያ ሠራዊት አባላት እና በነዋሪዎች መካከል የተኩስ ልዉዉጥ ተደርጎ ከአካባቢው ነዋሪዎችና ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ሕይወት አልፏል፤አካልም ጎድሏል፡፡

ትላንት ምሽት ላይ ደግሞ ‹ኮኪት› ከተማ ላይ የነበሩ 43 የሱር ተሽከርካሪዎች ተፈትሸው ወደ ገንደ ውሀ ከተማ መመለሳቸውን ኃላፊው አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ስለጉዳዩ በሰጡት አስተያየት ጉዳዩን በውይይት መፍታት ተገቢ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዥር ሹም ትላንት ማምሻውን ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ ሠራዊቱ ወደላይ እየተኮሰ እንደነበር፣ ነገርግን አስቀድሞ ተኩስ የተከፈተበት በመሆኑ ራሱን ለመከላከል የወሰደው እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።

በወጣቶች የተገነባው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወይንም የመከላከያ ሚኒስትሯ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ፣ በአጥፊዎችም ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል።

የአማራ ዴሞክራስያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት ትላንት ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ደግሞ በምዕራብ ጎንደር ዞን በተከሰተ የጸጥታ ችግር ምክንያት የሰዎች ህይወት በማለፉ የተሰማውን ሐዘን ገልጶ ዝርዝር ጉዳዩ ተጣርቶ አጥፊዎቹን ለህግ ለማቅረብ የሚያስችል አጣሪ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ስፍራዉ ተንቀሳቅሷል ብሏል።

ይህን ጥቃት በመቃወም በትላንትናው ዕለት የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን ለቅቆ እንዲወጣ የሚጠይቅ ሕዝባዊ ሰልፍ በገንደ ውሀ እና ኮኪት መካሄዱም ተሰምቷል።

*መከላከያን ማን አሰማራው?

የመከላከያ ሠራዊት ከክልሉ አቅም በላይ የሆነ የጸጥታ ችግር ሳይፈጠር፣ ክልሉም የፌደራል መንግሥትን ጣልቃ ገብነት ባልጠየቀበት ሁኔታ ሠራዊቱ የአንድ የንግድ ኩባንያ ንብረት አጅቦ እንዴት ሊንቀሳቀስ እንደቻለና ከሕዝብ ጋር እንዲወያይ የገባውን ስምምነት ጥሶ ንብረት ወደማንቀሳቀስ እንዴት እንደተሸጋገረ በየትኛውም አካል እስካሁን የተሰጠ ግልፅ ማብራሪያ የለም።

አንዳንዶች በትግራይ ክልል መከላከያ እንዳይንቀሳቀስ ሲታገድ፣ በምዕራብ ወለጋ ኦነግ ንጹሀን ዜጎችን ሲጨፈጭፍ ታጋሽ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት በምዕራብ ጎንደር የተከሰተውን ተቃውሞ እንዴት መታገስ አቃተው በማለት በንጽጽራዊ ዕይታ ድርጊቱን በማውገዝ ላይ ናቸው።

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close