Connect with us

Business

የወልቃይት ጉዳይ በኤርትራ በኩል ዞሮ መጣ

Published

on

የወልቃይት ጉዳይ በኤርትራ በኩል ዞሮ መጣ | ፀጋው መላኩ

የወልቃይት ጉዳይ በኤርትራ በኩል ዞሮ መጣ | ፀጋው መላኩ@DireTube

ጎበዝ ሁሌም እየተነጋገርን ቢሆንም፤ ዛሬም ትኩስ መነጋገሪያ አጀንዳን አላጣንም፡፡ አንዱ ንግግር ሌላ የመነጋገሪያ አጀንዳ እየወለደ ዕለት በዕለት እየተነጋገርን ቢሆንም ሁነቶችና ድርጊቶችም የንግግሮቻን እና የመነጋገሪያ አጀንዳዎቻችን ምንጭ እየሆኑ ሰው፡፡

የኦነግን ጉዳይ አላምጠን ሳንውጠው ከኤርትራ ተሰነይ በሁመራ በኩል የተከፈተው የኢትዮጵዮ ኤርትራ ድንበር ጉዳይ ሌላ ትኩሳት የተላበሰ አጀንዳ ሆኖ ብቅ ብሏል፡፡ ድንበሩ በዕለተ ገና የሁለቱ ሀገራት መሪዎችና የሁለት ክልል መስተዳድሮች በተገኙበት ሞቅ ባለ ሥነሥርዓት ተከፍቷል፡፡

ጉዳዩን መነጋሪያ ያደረገው የደንበሩ መከፈት ሳይሆን ከዚያ ጀርባ ያለው አንድምታ ነው፡፡ የእንግሊዘኛ ተናጋሪ ነጮች አንድ አነጋጋሪ ነገር ሲፈጠር “Read between the lines” ይለሉ፡፡

ባጭሩ ፤ከድርጊቱ ጀርባ ያለውን እውነታ ፈትሽ፣ በቅኔው ውስጥ ከሰሙ ጀርባ ያለውን ወርቅ ፈልግ ማለታቸው ነው፡፡

እናም የዕለተ ገናው አዲሱ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈት የፈጠረውን የማህበራዊ ሚዲያ ጫጫታ ሲታይ በእርግጥ የድንበሩን መከፈት ብቻ ሳይሆን ከዚያ ጀርባ ያለውን ፖለቲካዊ አንድምታ መፈተሹ ከሰሙ ጀርባ የተደበቀውን የፖለቲካ ቅኔ መመርመር ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ከሺህ ኪሎ ሜትሮች በላይ ድነበርን ቢጋሩም ዋነኛ የግንኙነት መስመሮቻቸው ውስን ናቸው፡፡ በአሰብ በኩል፣ በዛላንምበሳና አሁን በሶስተኝነት የተከፈተው የሁመራው መስመር ነው፡፡ ከሶስቱ የግንኙነት መስመሮች ውስጥ የአሰቡ መስመር በአፋር ክልል የሚገኝ ሲሆን ቀሪዎቹ የድንበር ግንኙነቶች ያሉት በትግራይ ክልል በኩል ነው፡፡ በአዲግራት ሰንአፌ፣ አዲቀይህ በኩል አብዛሃኞቹን የትግራይ ከተሞች ከኤርትራ ደገኛው ትግርኛ ተናጋሪ ክፍል ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡

በዚህ መስመር በሚኖረው የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግኙነት ከአዲግራት እስከ መቀሌ ያሉት የትግራይ ክልል ከተሞች ተጠቃሚነት ከፍተኛ ነው፡፡ ሆኖም ይሄኛው መስመር በተከፈተ በጥቂት ወራት ውስጥ በፌደራሉ መንግስትና በኤርትራ መንግስት አማካኝነት መልሶ እንደዚጋ ተደርጓል፡፡ ይህ የድንበር ግንኙነት እንዲቋረጥ ተደርጎ በሱዳን ጥግ በኩል ባለችው የሁመራ ከተማ በኩል ድንበሩ እንዲከፈት ተደርጓል፡፡

ይሄኛው መስመር ከኤርትራ ተሰነይ ተነስቶ በጎልጂ ኦማሃጅር በኩል ሁመራ ከተማን መዳረሻው በማድረግ ቀጥታ ጎንደር ከተማ የሚገባ ነው፡፡ መስመሩ በአንድ መልኩ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል የግዛት ይገባኛልና የማንነት ጥያቄን ያዘለውን ወልቃይትን በማቋረጥ ጎንደር ከተማ የሚገባ ሲሆን፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ እንደ ሽረ፣ አድዋ፣ አዲግራት መቀለ፣ ወቅሮና አክሱምን ከመሳሰሉ ከተሞች በእጅጉ የራቀ የግንኙነት መስመር ሆኖ ይታያል፡፡

እናም “ይህ መስመር በዋነኝነት የሚያገለግለው ለትግራይ ከተሞች ሳይሆን ከጎንደር ከተማ በመለስ ላሉት የአማራ ክልል ከተሞች ነው” በሚል ጥያቄን አስነስቷል፡፡ ጉዳዩን ከዚህ ባለፈ መነጋገሪያ አጀንዳ ያደረገው ደግሞ በዛንበሳ ያለው መስመር ተከፍቶ በድንገት በተዘጋበት ሁኔታ ለምን አዲስ መስመር መክፈት አስፈለገ? የሚለው ነጥብ ነው፡፡

የዛላንባሳው መስመር ሲዘጋ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በጊዜው እንዳላወቀና ከዚያ በኋላ ግን ለፌደራሉ ጥያቄ ቀርቦ የጉምሩክና አንዳንድ ነገሮች እስኪስተካከሉ ድረስ የተወሰደ እርምጃ መሆኑ እንደተገለፃቸው፤ ዶክተር ደብረፅዮን በእለቱ በመቀሌ ኤርፖርት ለጋዜጠኞች በሰጡት አጠር ያለ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

አንዳንድ የትግራይ አከክቪስቶችና ፖለቲከኞች “ጉዳዩ የጉምሩክና የኬላ ጉዳይ ከሆነ፤ ነገሮች በአጠቃላይ ሳይስተካከሉ በአንዱ አቅጣጫ የተዘጋው ድንበር ባልተከፈተበት ሁኔታ ለምን በሌላ አቅጣጫ መክፈት አስፈለገ? የሚል ጥያቄን በማንሳት ላይ ናቸው፡፡
ሁኔታው የጦዘ መነጋሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ጉዳዩ ሌላ የጥርጣሪ አቧራም አስነስቷል፡፡

አነጋጋሪውን ጉዳይ የጫረው ሌላኛው ምክንያት ደግሞ ከሁለቱ የሀገራት መሪዎችና ድንበሩ የሚገኝበት ክልል ፕሬዝዳንት ከሆኑት ዶክተር ደብረፅዮን ባሻገር አቶ ገዱ በቦታው መገኘታቸው ነው፡፡ አሁን ባለው የሀገሪቱ የፌደራል አከላለል መሰረት አዲሱ የተከፈተው መስመር በትግራይ ክልል ወልቃይትን በስፋት የሚያቋርጥና የድንበር መጋራቱም በዚሁ አካባቢ በሚገኝበት ሁኔታ ጉዳዩ በቀጥታ የማይመለከታቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቦታው እንዴት ሊገኙ ቻሉ ? የሚለው ጉዳይ ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የፖለቲካ ትኩሳት አንሮታል፡፡

እናም በዕለቱ በአቶ ገዱ በቦታው መገኘት የተበሳጩት በአካባቢው የተሰባሰቡ ወጣቶችም በዶክተር አቢይና በአቶ ገዱ ላይ የስድብ ናዳ ማውረዳቸው ታውቋል፡፡ ወጣቶቹም በፅጥታ ኃይሎች እንዲበተኑም ተደርጓል፡፡

ከአቶ ገዱ በቦታው መገኘት ባለፈ በጃፓን የኤርትራው አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር እስጢፋኖስ በትዊተር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት ዘገባ “ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድና ፕሬዝደንት ኢሳያስ ከምዕራቡ የንግድ ቀጠና ጎንደር ተሰነይ የሚያገናኘውን መስመር በድጋሜ ከፈቱ፡፡ “ በማለት አስፍረዋል፡፡ አምባሳደሩ በዚሁ መልዕክታቸው ትግራይን ዘለው ጉዳዩን ጎንደር አስገብተውታል፡፡

የወልቃይት የማንነት ጉዳይ በአንገብጋቢ የፖለቲካ ጥያቄ ውስጥ ባለበት ሁኔታ አምባሳደሩ ደግሞ የኤርትራና የጎንደር ግንኙነት መስመር የተከፈተ መሆኑን አብስረዋል፡፡ ሁኔታውና አባባሉ በትግራይ በኩል ያሉ አክቲቪስቶችን በከፍተኛ ስሜታዊ ብስጭት ውስጥ ሲከት፤ በአንፃሩ የአማራ አክቲቪስቶች በመፈነደቅ ላይ ናቸው፡፡

ለማንኛውም የዚች ሰሞን የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መከፈትና መዘጋት የማህበራዊ ሚዲያውን የብሽሽቅ ገበያ አድርቶታል፡፡ የትግራይ ፌስቡከሮች፣ ትግራይ ኦንላይን እና አይጋ ፎረም በአንድ በኩል፤ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ የአማራ አክቲቭሰቶችና ኤርትሪያን ፕሬስ ጎራ ከፈለው የማህበራዊ ሚዲያወን የቃላት ጦርነት በመምራት አጡዘውታል፡፡

እናም አንዱ ደንበር ተዘግቶ የሌላው የመከፈቱ ጉዳይ ከመክፈትና ከመዝጋት ያለፈ ፖለቲካዊ አንድምታን ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለው እውነታ ደግሞ ቢወቀጥም፣ቢፈለጥም እስከዛሬም ያው የሆነው የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ ቅድመ ኢህአዴግ በነበረው የበጌምድር ጠቅላይ ግዛትና የክፍለ ሀገር አከላል ወልቃይት በጎንደር ክፍለ ሀገር ሥር ስለነበር ኤርትራና ጎንደር በቀጥታ አዋሳኝ ደንበር ይገናኙ ነበር፡፡ ሆኖም በኢህአዴግ ዘመን በተካሄደው የክልሎች አወቃቀርና የወሰን አከላለል መሰረት ወልቃይት በዞንነት በትግራይ ክልል ውስጥ መካተቷ ኤርትራና ጎንደር ቀደም ሲል የነራቸውን የድንበር ተጋሪነት አስቀርቶታል፡፡

እናም ኤርትራ እንደሀገር በአሁኑ ሰዓት ድንበር የምትጋራው ከአፋርና ከትግራይ ክልሎች ጋር ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ በቀድሞው አከላለል መሰረት ቢቀጥል ኖሮ ትግራይ ክልል የምታስነው ጎረቤት ሀገር ኤርትራን ብቻ ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም በአዲሱ አከላለል መሰረት ግን የቀድሞው የትግራይ ክፍለ ሀገር ወደ ክልልነት ሲቀየር ወደ ምዕራብ ሽግሽግ ባደረገበት ወቅት ወልቃይትን በመጠቅለሉ ትግራይ ከሱዳን ጋር የምታወሰንበትን ሀኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚያው መጠን የኤርትራና የጎንደር የድንበር ታጋሪነት እዚያው ላይ አክትሟል፡፡

እናም ይህም በዕለተ ገና የተከፈተውን አዲሱን የሰሜን ምዕራባዊ የኢትዮ ኤርትራን ድንበር ሙሉ በሙሉ በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህ ሶስተኛው የኢትዮ ኤርትራን ድንበር መከፈት አወዛጋቢነትን ያጦዘውም የጀርባ ፖለቲካ ቢኖር ይሄው የወልቃይት የማንነት ጉዳይ ነው፡፡ እናም የወልቃይት ጉዳይ ከሀገራዊ ፖለቲካዊ አጀንዳነት ባለፈ በኤርትራ በኩል ዞሮ መምጣቱን ልብ ይሏል፡፡

የመካከለኛው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር በድንገት ተዘግቶ ባልተከፈተበት ሁኔታ የወልቃይቱን መስመር መክፈት፣ የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው በቦታው መገኘትና የኤርትራው አምባሳደር አነጋጋሪ የትዊተር ገፅ መልዕክት ጠቅለል ተደርጎ ሲደመር የሚሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ብዙ ያነጋግርናል እና እንነጋገርበት፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close