Connect with us

Ethiopia

ከገዱና ደብረጽዮን መተቃቀፍ ጀርባ፤

Published

on

ከገዱና ደብረጽዮን መተቃቀፍ ጀርባ፤

ከገዱና ደብረጽዮን መተቃቀፍ ጀርባ፤
(በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን)

ኢትዮጵያውያን ፖለቲካን የምናይበት መነጽር የተሳሳተ ነው፡፡ ሴራ፣ ተንኮልና ክፋት አድርገን እናየዋለን፡፡ እከሌ ከእከሌ ጋር እየዶለተ ነው፤ እነ እከሌ ሊሸፍቱ ነው፤ እከሌ አመጽ ሊወጣ ነው፤ አቶ እንትና እና አቶ እከሌ በአቶ እከሌ ላይ እንዲህ እያሉ ነው…ወዘተ የሚለውን ጉዳይ የኖርንበትና የምንታወቅበት ነው፡፡

ፖለቲካ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን፣ ሴራ ምቀኝነትና ተንኮል ተደርጎ ይተነተናል፤ ለሰለጠነው ዓለም ግን ፖለቲካ ሳይንስና አርት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ፖለቲካን በሳይንስነቱም ሆነ በጥበብነቱ ማየት አልጀመርንም፡፡ በአጋጣሚ በአንድ ግብዣ ላይ የተገናኙ ሰዎችንም ለሴራና ለተንኮል የተገናኙ አድርገን እናቀርባቸዋለን፡፡ በዚህ ረገድ የፖለቲካ ልሂቃኑን የሚበልጣቸው የለም፡፡

ዶ/ር መረራን ኢሕአዴግ ያሰራቸው ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር በብራስልስ ተገናኙ ብሎ ነበር፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳና አቶ ጃዋር መሀመድ በኤርፖርት ውስጥ ለተለያየ ጉዞ በአጋጣሚ ተገናኝተው ቆመው ሲያወሩ የሚያሳይ ፎቶ በተለቀቀ ሰሞን በፌስቡክ ላይ የነበረውን የሴራ ፖለቲካ ተንታኝ ብዛት አንረሳውም፡፡ ልጅ ኢያሱን ከሥልጣን ያስወገዳቸውም ሆነ እቴጌ ጣይቱን ለእስርና ለግዞት የዳረጋቸው፣ ጉግሳ ወሌን ከአዲስ አበባ ያባረራቸውም ሆነ ንግሥት ዘውዲቱን የአገር መሪ ያደረጋቸው ሳይንሳዊ የፖለቲካ ትንተናና ትክክለኛ መረጃ አይደለም፡፡ ሴራና የፖለቲካ ክፋት ነው!!

እንዲህ ያለ ታሪክ እየሰማን ያደግን የዚህ ዘመን ፖለቲካ ታዳሚያንም ሀሜትና የሴራ ትንተና ልማዳችንና ሥራችን ነው፡፡ ሴራ እውቀት አይጠይቅም፤ አሉባልታ ብቻውን ትልቅ ግብዓቱ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ የሴራ ፖለቲካን አጠላልፎ እንደመተንተን የሚቀል ነገር የለም፡፡ ይህ ሰሞኑንም እየታየ ነው፡፡ በሁመራ ያለውን የኢትዮኤርትራ ድንበር ለመክፈት ሄደው ፎቶ የተነሱትን የትግራይና የአማራ ክልል መሪዎችን የተመለከተው የሴራ ትንተና አሁንም አልቆመም፡፡

የአማራና የትግራይ ሕዝብን ያህል የተዋለደ፣ የተዋደደ፣ አንድ ዓይነት ባሕልና ሥርዓት ያለው፣ በተመሳሳይ አለባበስ፣ አንድ ዓይነት አመጋገብ ያለው ሁለት ቋንቋ የሚናገር ሕዝብ የለም፡፡ ይህንን ተዋልዶ፣ ተዋድዶ፣ ተከባብሮና ተፋቅሮ የሚኖርን ሕዝብ ለማቃቃር ግን አሁንም ገመድ መጓተቱ አልቀረም፡፡ ‹‹ትግራይን እንጨብጣታለን፣ ምሽግ ቆፍራችሁ ቆቦ ላይ ጠብቁን፣ ከትግራይ ጋር ለመዋጋት ሕዝባችንን እያስታጠቅን ነው›› ከሚለው ጀምሮ፣ ‹‹የትግራይ ወጣቶች ሆይ ለየትኛውም ትግል ተዘጋጁ›› እስከሚለው ድረስ ጦረኛ ሐሳቦችን ስንሰማ ከርመናል፡፡ ይህ ሁሉ ነገር የሆነው በተዋለደ እና በተዋደደ መሀል ደም መቃባትን ለማምጣት ነው፡፡

በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ይህንን ጉዳይ በደንብ ገልፀውታል፡፡ ‹‹ይህ እንዋጋለን፤ ምሽግ እየቆፈርን ነው ወዘተ የሚለው ፎካሪ ሁሉ ጦርነት ቢከፈት እርሱ ገብቶ አይዋጋም››፡፡ ያንኑ የፈረደበትን የድሃ ልጅ ለማስጨረስ የታቀደ ነው፡፡ የግል የፖለቲካ ፍላጎትን በድሃ ልጅ ደም ለማርካት መጣር ነው፡፡

በዚሁ ሁሉ መሀል ለሰላም የሚደረግ አንድ ግራም ጉልበት እጅጉን መወደስና መደነቅ ነው ያለበት፡፡ የልሂቃኑ መቀራረብና መስማማት በአማራና በኦሮሚያ ሕዝቦች መሀል ያመጣውን መደጋገፍ አይተናል፡፡ የትግራይና የአማራ ልሂቃንም ተቀራርበውና ተነጋግረው ቢሰሩ ይህንን የምናየውን ገመድ መጓተት አርግበው ወደነባርና የሚታወቁበት መልካም ግንኙነት ይመለሳሉ፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የገዱና ደብረጽዮን መተባበር ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ይህ ለሁለቱ ሕዝቦች ትልቅ ገዲል ነው፡፡ የእነዚህ በታሪክም፣ በባሕልም፣ በሁሉም ነገር (ከቋንቋ በስተቀር ምንም ልዩነት የላቸውም) አንድ የሆኑ ዜጎች መልሶ አንድ መሆናቸው ያሳሰባቸውና መተሳሰባቸው ጥቅማቸውን የሚያሳጣ የመሠላቸው ነጋዴዎች የሁለቱን መሪዎች መገናኘት እያወገዙ ነው፡፡

‹‹የትግራይን ሕዝብ ከጎንደር ያባረረው ገዱ አንዳርጋቸው ትግራይ ውስጥ መግባት የለበትም፤ የትግራይ ሕዝብ ገዱን ተቃውሞ ሰልፍ ይወጣ›› ወዘተ የሚል ቅስቀሳ እያሰሙ ያሉ አክቲቪስቶች ምን ዓይነት በሽታ እንደያዛቸው እንጀ፡፡ ትናንት ምንም ዓይነት ወንጀል ተሰርቶ ይሆናል፡፡ ይህንን ክፉ ተግባር ለማደስ ግን ቂምና በቀል፣ በገዱ ላይ አመጽ መጥራት ወዘተ ምን ትርጉም እንደሚሰጥ እንጃ፡፡

ደግሞስ ገዱ አንዳርጋቸው በአገራቸው ውስጥ አይንቀሳቀሱ ብሎ ቅስቀሳ ምን የሚሉት ነው፣…ለገዱም ሆነ ለደብረጽዮን፣ መቀሌም ሞያሌም፣ አዲግራትም ባሕርዳርም…አገራቸው ነው፡፡ በዚህ ቦታ እንዳይገቡ፣ በዚህ ቦታ እንዳይታዩ ብሎ ቅስቀሳ ምን ከሚሉት ሞራል እንደመጣ ሰይጣንም የሚያውቅ አይመስለኝ፡፡

ዋናው ግቡ ጡዘት ላይ ያለውንና በሰላም-ጠል ኃይሎች እየተናጠ ያለውን የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት ወደ ቦታው መመለስ ነው፡፡ ለዚህ ሰላምና ትብብር አለመፈጠር ዋነኛው ሰበቦች ልሂቃኖቻችን ናቸው፡፡ የኢሕአዴግ መሪዎች አለመግባባት፣ በዘረኛ አክቲቪስቶች ታጅቦ ሕዝብን ለማናከስ ጫፍ በደረሰበት በዚህ ወቅት በምንም ዓይነት መመዘኛ ለሰላም አንድ ጠጠር የሚወረውር ሰው መወደስ ነው ያለበት-እንኳን ገዱና ደብረጽዮን ቀርቶ፡፡

በዚህ ረገድ የመቐለ ነዋሪዎች፣ የፋሲልና የወልዋሎ ተጨዋቾችና ደጋፊዎቻቸው ባሳለፍነው እሁድ ያሳዩት የሰላም ትብብርና ቅንነት መደነቅ ይገባዋል፡፡ ይህ ቀጣይ እንዲሆንና የፖለቲከኞች ሴራ እንዲከሽፍ መተጋገዝ ያስፈልጋል፡፡ እናም ገዱና ደብረጺዮን የጀመሩት ትብብር ከፎቶ መነሳት ባሻገር ሆኖ ወደሚመሩት ሕዝብም እንዲወርድ ማገዝ እንጂ ሴራና ምቀኝነት አይጠቅምም፡፡

ሁለቱም መሪዎች በሁለቱ ሕዝቦች መሀል ነገር እንዲባባስና ግጭት እንዲቀሰቀስ የሚያደርጉ ባለሥልጣናትን፣ አክቲቪስቶችን፣ ሚዲያዎችን ወዘተ ሥነ-ሥርዓት እንዲያሲዙና ለሕግም እንዲያቀርቡ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል እንጂ፣ ለምን ተገናኙ ብሎ ቡራከረዮ ማለት ለሀገርም ለሕዝብም አይጠቅምም፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close