Connect with us

Ethiopia

ከህወሓት ድጋፍ አንጠብቅም!

Published

on

ከህወሓት ድጋፍ አንጠብቅም! | በአብርሃ ደስታ

ከህወሓት ድጋፍ አንጠብቅም!
(በአብርሃ ደስታ)

ዓረና የህወሓት ተቃዋሚ ነው፤ ደጋፊ አይደለም። የህወሓት ደጋፊዎችና ተላላኪዎች ህወሓትን አትንኩብን እያሉ ነው። ልክ ናቸው። ምክንያቱም ህወሓት ከተነካች ትጋለጣለች። ከተጋለጠች ከስልጣን ትወርዳለች። ከስልጣን ከወረደች ጥቅማቸው ይነካል። ጭቁን የትግራይ ህዝብ ነፃ ይወጣል፣ በእኩል ዓይን ይታያል። ሰዎች በብቃታቸው ይመዘናሉ፣ ስራ ያገኛሉ። የተዘረፈው ገንዘብ ለህዝብ ይከፋፈላል። ህዝብ ይጠቀማል። ትግራይ የህዝቧ እንጂ የህወሓት ተላላኪዎች የግል ንብረት አትሆንም። እናም ይጎዳሉ (ከህዝብ ጋር እኩል ይሆናሉ) ለብቻ መብላት አይኖርም።

ስለዚህ ህወሓትን ስንተች ቢንገበገቡ አይገርምም፤ የጥቅም ጉዳይ ነውና። ዓረና የህወሓት ተቃዋሚ እንደመሆኑ መጠን የህወሓት ደጋፊዎች እንዲደግፉን አንጠብቅም። ስለዚህ ቢቃወሙን አይደንቀንም። ከቁብም አንቆጥረውም። (ህወሓት ስትነካ የሚያንገበግበው ሰው የህወሓት ደጋፊና ተጠቃሚ እንጂ ሌላ ማን ሊሆን ይችላል? ያልሆነማ የተለያዩ አማራጭ ሐሳቦች ማየት አለበት)። የህወሓት ሰዎች ሲቃወሙን ልክ ናቸው። የጥቅም ጉዳይ ነውና።

ግን አንድ ነገር ተሳስተዋል። ዓረና የህወሓት ደጋፊ እንዲሆን ይፈልጋሉ። ሊሆን አይችልም። ዓረና ከህወሓት የተለየ ዓላማ ያለው ድርጅት ነው። ህወሓቶች ለውጥ አይፈልጉም፤ ዓረና ለውጥ ለማምጣት ነው ሚታገለው። ስለዚህ የተለያየን ነን። ለውጥ ከመጣ እንደግፋለን። ለለውጥ እየታገልን ለውጥን አንቃወምምና! የኛ ጉዳይ ለውጡ ህዝብ ሚጎዳ ሳይሆን ሚጠቅም መሆን አለበት ነው።

ለውጥ ለማምጣት ትግል የጀመርነው ከ10 ዓመት በፊት ጀምሮ ነው (የወራት ዕቅድ አይደለም)። ዴሞክራሲ ሰፍኖ ህዝባዊ መንግስት እስኪመሰረት ድረስም ይቀጥላል።

አሁን ለኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ ለትግራይ ህዝብ ደግሞ በተለይ የሚጠቅም አማራጭ ሐሳብ ስናቀርብ የስድብ ዘመቻ ያካሂዳሉ። ህወሓትን አትንኩብን ይላሉ። ህወሓትን የተቃወመ የጠቅላይ ሚኒስተር ዶር ዐብይ አሕመድ ተላላኪ በማለት ለማጥላላት ይሞክራሉ (ዶር ዐቢይ ግን የዓረና አባል ሆነንዴ?!)። “ወደኛ ተቀላቀልና ሌሎችን ሁሉ በመሳደብ የተጋሩን ደሕንነትና ጥቅም እናስከብር” ይሉሃል። ሌሎችን በመሳደብ የተጋሩን ጥቅምና ደሕንነት የሚከበር ይመስላቸዋል። ህወሓት ያልደገፈ ትግራዋይ እንዳልሆነ ይሰብካሉ፤ ትግራዋይነት የሚታደለው እንደ ፓርቲ መታወቅያ በህወሓት ይመስል!

አሁን ህወሓቶችን በሚተቹ አክቲቪስቶች ላይ የስድብ መዓት በማውረድ የማጥላላት ዘመቻ እንዲከፍቱ መመርያ ተሰጥቶዋቸዋል (መደብ ወርዶላቸዋል)። የስድብ ጦርነት ከፍተዋል። ዋና አዛዥ የህወሓቱ ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ሲሆን በደሕንነት፣ በኮሙኒኬሽን ቢሮ እና በክልሉ ሚድያ ተቋማት አስተባባሪነት በተለየ በሚከፈላቸው አክቪስቶች ነን ባዮች የሚከናወን ነው፤ የማይከፈላቸው ግን በህወሓት “የተከበናል” (የፀጥታ ችግር) ፕሮፖጋንዳ የተሸወዱም አሉ። የፀጥታ ችግር ቢያጋጥም እንኳ በህወሓት መሪነት ሊፈታ እንደማይችል ያልተገነዘቡ አሉ።

ከነዚህ ቅልብተኛ አክቲቪስት ነን ባዮች አንዱ በክልሉ ቴለቪዥን ጣብያ ቀርቦ “እነዚህ ፀረ ህወሓት አክቲቪስቶች ከፌስቡክ ወደ ትዊተር አባረናቸዋል” ብሏል (በመንጋ ስድብ መሆኑ ነው)። ዓላማቸው የስድብ ዘመቻ በመክፈት ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ደጋፊ የለንም ብለው እንዲሸማቀቁ፣ ስድብ ፈርተው ህወሓትን ከመተቸት እንዲቆጠቡና ህወሓት መልሳ እንድታገግም ዕድል ለመስጠት ነው።

አሁን ስለ ህወሓት ጥሩ ነገር ብፅፍ ራሱ መሳደባቸው አያቆሙም። ምክንያቱም መደብ (መመርያ) ተሰጥቷቸዋል። ዝም ብለው ስድብ ይፅፋሉ። እንደ ፓሮት የተነገራቸውን ይደግማሉ። ከነዚህ ተከፋይ ተሳዳቢዎች በቅርቡ በትእምት ስፖንሰርነት “አንዳንድ ነገሮች” እንዲጎበኙ ተጋብዘው ነበር። ከተጋበዙት አብዛኞቹ ብዙ የፌስቡክ አካውንቶች ከፍተው እንዲሳደቡ የሚከፈላቸው ናቸው።

ዓረና ግን እንኳን በስድብ በጠመንጃም አይሸማቀቅም፤ ዓላማ ነዋ። ከህወሓትም ድጋፍ አይጠብቅም። በትግራይም ለውጥ እንፈልጋለን። ሊያስተዳድረን የሚገባ በህዝብ የተመረጠ መንግስት ነው። ህወሓት የህዝብ ድጋፍ አለኝ ብሎ የሚያምን ከሆነ አማራጭ ሐሳብ ለምን ይፈራል?

ይህን የትእምት ገንዘብ ለቅልብተኛ ተሳዳቢዎች ከሚከፈል ዩኒቨርስቲ ተመርቀው ስራ ያላገኙ ግን ብዙ ማምረት የሚችሉ ወጣቶች ስራ የሚጀምሩበት ዕድል ለምን አይከፈትላቸውም? ያመርታሉኮ! መሳደብ ግን ምርት የለውም! እናም የትእምት ገንዘብ ለተሳዳቢዎች ከሚሰጥ ለአምራች ወጣቶች ቢውል ውጤታማ ይሆናል።

አትድከሙ! ከህወሓት ተላላኪዎች ድጋፍ አንጠብቅም፤ የራሳችን ለውጥ ፈላጊ ወጣት ደጋፊዎች አሉን። የህወሓት ደጋፊም አንሆንም፤ የምንደግፈው የራሳችን ድርጅት አለን። የዓረና ማሕበራዊ መሰረት (Social Base) የህወሓት አባል ወይ ደጋፊ አይደለም። ለዚህም የትግራይን ህዝብ እንጂ ህወሓቶችን ለማስደሰት አንሰራም። ከድርጅት ህዝብ ይቀድማል!

ዴሞክራሲ ያሸንፋል!

It is so!!!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close