Connect with us

Education

ጤና ኬላ በሚያስፈልገው ሥፍራ ዩኒቨርሲቲ የገነባች ሀገር እንዲህ ያለ ፈተና ቢገጥማት አይደንቅም

Published

on

ጤና ኬላ በሚያስፈልገው ሥፍራ ዩኒቨርሲቲ የገነባች ሀገር እንዲህ ያለ ፈተና ቢገጥማት አይደንቅም

ጤና ኬላ በሚያስፈልገው ሥፍራ ዩኒቨርሲቲ የገነባች ሀገር እንዲህ ያለ ፈተና ቢገጥማት አይደንቅም፡፡ ልዩነትን የማስተናገድ ትከሻ ባለው ነዋሪ መካከል ያልተሰራ ዩኒቨርሲቲ ውጣልኝ ግባልኝ ሲል ይኖራል፡፡ *** ከስናፍቅሽ አዲስ

ኢትዮጵያ ችግሬን የሚፈታው ከዩኒቨርሲቲ ይወጣል ብላ ስትጠብቅ ችግሯ ከዩኒቨርሲቲ መጣ፡፡

ኢትዮጵያ ገና ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስትከፍት የመለመለቻቸው ተማሪዎች እስከ መገንጠል የሚያስቡ ሆኑ፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ዛሬ ድረስ የኢትዮጵያ ገበሬ ያቀናውን ሀገር የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሊያፈርሰው የሚታገልበት ሆነ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገጥማቸው ፈተና ደግሞ መልኩም ጠባዩም ተቀይሯል፡፡ በእርግጥ አንዳንዶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ያለ ቦታቸው የተሰሩ ናቸው፡፡ ጤና ኬላ በቅጡ ሳያዩ በግዙፍ የሕንጻ ከተማ ውስጥ ከሌላ አካባቢ መጡ የሚሏቸው ሲኖሩ ሲበሉ ተመለከቱ አንደኛ ደረጃን የማስተናገድ አቅም በሌላት ከተማ የተገነባው ይህንን መሳይ ዩኒቨርሲቲ ኮሽ ባለ ቁጥር ዱላ ይዞ በሚዘምት ማህበረሰብ ተከበበ፡፡

ብዝሃነትን ለማስተናገድ መጀመሪያ ከተሜ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ባልከተሙ ከተሞች ግዙፍ ዩኒቨርሲቲዎች ሲከትሙ ነዋሪው እንደጠላት ማየት ጀመረ፡፡ እንደ ጠላት ባያያቸው ኖሮ ስለ ዩኒቨርሲቲው ስም ይጨነቅ ነበር፤ ስለ አካባቢው መልካም ገጽታ ያስብ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ሀሳብ ቅንጦት በሚመስላቸው አካባቢዎች ዩኒቨርሲቲ ሰርተን ችግር ተከሰተ ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡

ቡሌ ሆራ የሆነው ነገር ሊገርመን አይገባም፡፡ ቡሌ ሆራ ከድፍን ኢትዮጵያ ተማሪ ተቀብሎ ለማሰልጠን የስነ ልቦና ዝግጅት ባለው ስፍራ ተገንብቷል ወይ ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ይመስለኛል፡፡ በሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከዶርም ተሰደው ወደ ባህር ዳር ገብተዋል፡፡ እንዲህ ያለ ችግር ከዚህ ቀደም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ይከሰታል፡፡

ለምሳሌ ባህርዳር ጅማ ጎንደር ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ብጥብጥ ቢነሳ ተማሪዎች ወደ ከተማዋ ገብተው እስኪረጋጋ ይጠብቃሉ፡፡ እኚህን የመሰሉ ከተሞችም ተማሪዎችን ለመሸከም፣ ለመቀበልና ለማረጋጋት ጠንካራ ማህበራዊ መሰረትና የስልጣኔ አቅም አላቸው፡፡ አሁን በቦሌ ሆራ ያ ሁሉ ተማሪ ሲሰደድ ቆሞ የሸኘው ሰው ምናልባትም ህንጻዎቹን ለቀቀልኝ ብሎ ከማሰብ በመጣ የዋህነት አሊያም በሌላ ሊሆን ይችላል፡፡ እውነቱ ግን የዩኒቨርሲቲ ግንባታችን ቦታ መረጣ ቅጥ ማጣት ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲ የምርምር ማዕከል ነው፡፡ እኛ ጋ እንዲያ አይደለም፡፡ መሠረተ ልማት ነው፡፡ የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በተወለደባት መንደር ሁሉ ዩኒቨርሲቲ ስለመስራት ይታሰባል፡፡ ዩኒቨርሲቲ እንደ ውሃ ጤና ጣቢያና መንገድ እያንዳንዱ ቀበሌ እንዲደርስ የሚያስቡ ተራ ሹመኞች ሀገሪቷ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለዚህ ሁሉ ጣጣ ምክንያት ሆኑ፡፡ አሁንም ይታሰብበት፡፡

አንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ አካባቢያዊ መንፈሱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እንዲህ ያሉ ተቋማት ወደ ቴክኒክና ሙያ ቢቀየሩ፤ በመላው ሀገሪቱ ህዝብ ስም የሚመደብ በጀት ሜዳ ባይፈስ፡፡ በአስገዳጅ ሁኔታ ትምህርታቸውን አቋርጠው ስለሚባረሩ ተማሪዎችም ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡

በንጉሡ ጊዜ ከከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የተወሰኑቱ ውጪ ሀገር ተልከው ስኮላር ይማሩ ነበር፡፡ አሁን ጭራሽ ከሰፈሬ ውጪ አትመድቡኝ እስከሚባልበት ያደረሰንን ችግር አጢነን ካልፈታነው ችግሩ ከፍተኛ ነው፡፡ የአማራ ክልልም ባህር ዳር የገቡትን የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ ቀዳሚ ስራው አድርጎ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close