Connect with us

Business

ድንበሩ ለምን ተዘጋ? | ከስናፍቅሽ አዲስ

Published

on

ድንበሩ ለምን ተዘጋ? | ከስናፍቅሽ አዲስ

ድንበሩ ለምን ተዘጋ? ኤርትራም ያለ ሥርዓት ማስገባት የለባትም፤ እኛም ያለ ሥርዓት መሄድ የለብንም፡፡ ሌባው ባገኘበት እየሾለከ ድንበር ላይ ይለፍ አስፈለገ ብሎ መጮህ አያስፈልግም፡፡ *** ከስናፍቅሽ አዲስ

የኢትዮጵያ ኤርትራ ድንበር ከሃያ ዓመታት የጠብ ዘመን በኋላ ሲከፈት ሥርዓት የሌለው ሁኔታ ታይቶ ነበር፡፡ ሁለት ሀገር እንዲህ በፈለግህበት ግባ በፈለግህበት ውጣ መባባል የለባቸውም፡፡

ሁለት ሀገር ድንበር ከፍተው የኮንትሮባንዲስቶች መፈንጫ መሆን የለባቸውም፡፡ ኤርትራውያን ከዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን በተሻለ ሀገር የመውደድ ባህል አላቸው፡፡ ቢያንስ ብር ጭነው ድንበር እናሻግር አይሉም፡፡ ቢያንስ ቢሊዮኖችን የዘረፈ የሚሸሽግ ሞራል የላቸውም፡፡

ከእኛ በኩል ደግሞ ስርዓታችንን መስለን ያለፈውን ሃያ አመት ከመሪዎች የተማርነው ሀገር መዝረፍ ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ነው፡፡ ህግና ስርዓት መጣስ ነው፡፡ ናፍቆት ድንበሩን ሲያፈርሰው ህግና ሥርዓትን ለማሰብ ጊዜ አሳጥቶን ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን እስከመጨረሻው ስርዓት አልበኛ ሆኖ መቀጠሉ ለሁለቱም ህዝቦች ለሁለቱም ሀገራት አይጠቅምም፡፡

የጎጃም ጤፍ ወደ አስመራ መጫን ካለበት በቀጥታ ከጎጃም መጫን ይኖርበታል፡፡ የወለጋ ቡናን ምጽዋ ለመውሰድም መነሻ ወለጋ መሆን ይኖርበታል፡፡ ተቀባብሎ መነገድ የኮንትሮባንድ ባህል ነው፡፡

ኤርትራ ሉዓላዊት ሀገር ናት፤ መንግስቷም ቢሆን ልቡን ከከፈተ ይበቃል፤ ድንበሩን መክፈት ያለበት እንደ ዓለም ወግ ነው፤፤ አሁን ስርዓት አልበኝነቱ ሲያሰጋ ድንበር ላይ ያለ ይለፍ መውጣት አይቻልም በሚል ተከልክሏል፡፡ ይሄ ለሀገራቱ ጠቃሚ አሰራር ይመስለኛል፡፡

ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ሲመጡ የመንግስታቸውን ኢሚግሬሽን ይለፍ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ ኤርትራ ለመሄድ የሀገራችን መንግስት ይለፍ ባይነት መኖር አለበት፡፡ እንዲህ ሲሆን ማን ማን ሀገር እንደገባ ይታወቃል፡፡ ወንጀልን በመቀነስ በኩልም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

ሰሞኑን ኤርትራ ያለ ይለፍ መግባት ከለከለች የሚለውን ወሬ ለማራገብ ሲሞከር አይተናል፡፡ አሰራሩ ትክክለኛ መሆኑን ከመናገር ይልቅ ድንበሩ ለምን ተዘጋ የሚለው ጥያቄ ተስተጋብቷል፡፡ የጉሉ መኽዳ ወረዳ አስተዳዳሪም ለቢቢሲ አዲስ አሰራር መኖሩን ስለማየታቸው ተናግረዋል፡፡

የየቱም ክልል ነዋሪ ከሀገር ሲወጣ የፌዴራል መንግስቱን የዜግነትና ኢሚግሬሽን መምሪያ ይለፍ ማግኘት እንዳለበት ግን ማወቅ ይኖርብናል፡፡ አሰራሩ ስለሚወጡ ሰዎች ብቻ አይደለም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያም የሚገቡት በተመሳሳይ ሁኔታ ይስተናገዳሉ፡፡ ልቅ አድርጎ የነበረው የፌዴራል መንግስትም ቢሆን የድንበር ላይ ኬላዎች የእሱ ሃላፊነት መሆኑን አውቆ ደጃፉ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ድንበር ለቆ ከኢንተርፖል ጋር መፈራረሙ ምንም የሚጠቅመው ነገር የለም፡፡ በሌላ በኩል ኮንትሮባንድ ንግዱ ራስ ምታት የሆነው በዛላምበሳና ራማ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በአሰብ በኩል ማንዳም ሆነ ቡሬ ለሁለቱም ሀገራት ራስ ምታት የሚሆኑ ችግሮች አልተስተዋሉም፡፡

ከድፍን ኢትዮጵያ ተሸሽጎ ትግራይ የገባው አንድ ሺ የማይሞላ ኮንትሮባንዲስት ምናልባትም ቀጣዩ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት እንቅፋት እንዳይሆን እንዲህ ያሉ ውሳኔዎች መወሰናቸው ትክክል ነው፡፡

ንግዱም ፍቅሩም ጉብኝቱም ቤተስኪያን መሳሙም በህዝብ ልብ አንዳች ክፋት ባይሰንቅም ህዝብን መሸሸጊያ ያደረጉ ሌቦች ግን የሁለቱን ሀገራት ጥቅም በሚጎዳ መልኩ ሊቃኙት አልፎም የሀገራቱን ግንኙነት የሚያበላሽ ተግባር ሊፈጽሙበት ይችላሉ፡፡ እናም ሁሌም የድንበር ፖለቲካ ዋጋ እያስከፈለን እንዳንኖር መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close