Connect with us

Business

ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር መዘጋት ጀርባ እየታየ ያለው የፖለቲካ ሥሌት | ከፀጋው መላኩ

Published

on

ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር መዘጋት ጀርባ እየታየ ያለው የፖለቲካ ሥሌት | ከፀጋው መላኩ

ከኢትዮ ኤርትራ ድንበር መዘጋት ጀርባ እየታየ ያለው የፖለቲካ ሥሌት | ፀጋው መላኩ@DireTube

የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ተከፈተ ከመባሉ መዘጋቱን ሰማን፡፡ የኢትዮጵያ የዕለት ተዕለት የፖለቲካ የአየር ሁኔታ በሰዓታት ልዩነቱን የመለዋወጥ ሂደቱን ቀጥሎበታል፡፡ መስከረም 1 ቀን 2011 በአዲሱ ዓመት መገቢያ በፈንዲሻና በቡና አፈላል ሥነ ሥርዓት የተከፈተው የሁለቱ ሀገራት ድንበር ህዳር 17 ለ18 ምሽት መዘጋቱ ታውቋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት ድንበር ከሁለት አስርዕት ዓመታት መዘጋት በኋላ ሲከፈት ፍፁም ያልተጠበቀ የህዝቦች ግንኙነት ተፈጥሯል፡፡ የድንበሩ መከፈት ከነበረው ማህበራዊ ግንኙነት በሻገር የኢኮኖሚ ትስስሩንም ከሁለቱ መንግስታት ግምት በላይ ልቆ ሲሄድ ታይቷል፡፡

ሆኖም በተለመደው አኳኋን አገር ሰላም ብለው ድንበሩን አቋርጠው ወደ ኤርትራ ምድር ሊሻገሩ የነበሩ የጭነትና የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች በድንገት በኤርትራ ወታደሮች ክልከላ ተደርጎባቸዋል፡፡ እዚህ ጋር መነሳት ያለበት ክልከላ መደረጉ ሳይሆን ለምን ይህ እርምጃ ሊወሰድ ቻለ? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ከእርምጀው ጀርባ በብዙ መልኩ ሊታዩ የሚገባቸው ወሳኝ ነጥቦች አሉ፡፡ የደንበሩ መዘጋት በተለይ ከፖለቲካና ከኢኮኖሚ አንፃር ብዙ ሊያስብል የሚያስችል ነው፡፡

ለጊዜው የፖለቲካውን አንድምታ እንመልከተው፡-

የኢትዮጵያና የኤርትራ የየራሳቸው የውስጥ ፖለቲካ፤ ለኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት መሰረት ነው፡፡ ሌላውን ነገር እንተወውና አሁን ባለው ከባቢያዊ የፖለቲካ ለውጥ የኢትዮጵያና የኤርትራ ውሳጣዊ የፖለቲካ ሂደት ፍፁም የተራራቀ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በእርግጥ በሁለቱም ሀገራት የተለየ የፖለቲካ ድምፅ የሚሰማበት ዕድል ዝግ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ በቅርቡ የተካሄደው የፖለቲካ ለውጥ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ጠረን የለወጠው ሲሆን ይህም ትሩፋት ለኢትዮ-ኤርትራ አዲሱ ግንኙነት ሳይቀር መትረፍ ችሏል፡፡

በኢትዮጵያ የተካሄደው ተስፋ የተሞላበት የፖለቲካ ለውጥ በፖለቲካ አስተሳሰባቸው የተገለሉትን፣ የተሰደዱትንና የታሰሩትን ኢትዮጵያዊያን ነፃ ማድረግ ችሏል፡፡ ነፍጥ አንስተው መንግስትን በሀይል ለማስወገድ የተነሱ በርካታ ተጣቂ ኃይሎችን በፍላጎት ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊው የፖለቲካ ማዕድ መጋብዝ ችሏል፡፡ እናም ከዓመታት በፊት በውጥረት፣ በፖለቲካ ጥላቻና በመገፋፋት ውስጥ የነበረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ለዘብ በማለት ከገፊነት ወደ አቃፊነት ሂደት እየገባ ነው፡፡

በአንፃሩ ወደ ኤርትራ ጉዳይ እንመለስ፡- በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሲታሰሩ እንደነበር በኤርትራም ጋዜጠኞች ይታሰሩ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሰዎች በያዙት አመለካከት ተፈርጀው ይሳደዱና ይተሰሩ እንደነበር በኤርትራም እንደዛው፡፡ ኢትዮጵያዊያን በብዙ መልኩ ሀገራቸውን በገፍ ጥለው ይሰደዱ እንደነበረው፤ የኤርትራዊያን ታሪክም ያው ነው፡፡ በዚህ መልኩ የሁለቱን ሀገራት የፖለቲካ መስለ ገፅ ስንመለከት ተመሳሳይ ታሪክን እናገኝበታለን፡፡

ሆኖም ቢያንስ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ በርካቶቹ እውነታዎች“ነበር” ሆነዋል፡፡ በኤርትራ አቅጣጫ ግን የነበረው እንዳለ ነው፡፡ የተለወጠው ነገር ቢኖር ኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በአዲስ ምዕራ ውስጥ መገኘቱና በሀገሪቱ ላይ ለዓመታት ተጥሎ የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ ብቻ ነው፡፡ እናም በኤርትራ የውስጥ ፖለቲካ ሁሉም ነገር በነበረበት ቀጥሏል፡፡ በነበረበት መቀጠሉም ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም የታሰበ የለውጥ አዝማሚያ ስለመኖሩም አንዳች አይነት ፍንጭ አይታይም፡፡ እናም ኢትዮጵያና ኤርትራ በውስጥ ፖለቲካቸው የለውጥ ሂደት ሲመዘኑ ኤርትራ በነበረችበት ያለች ስትሆን፤ ኢትዮጵያ በአንፃሩ በብዙ አቅጣጫ ወደፊት ተራምዳለች፡፡

ከኢትዮ- ኤርትራ የድንበር ጦርነት በኋላ ኤርትራ ፤ ለቀሪው ዓለም እንደ ሰሜን ኮሪያ ዝግ ሆና ቆይታለች፡፡ የኤርትራዊያን ከሀገር የመውጣትና ወደ ሀገር የመግባት ሁኔታም በእጅግ በገደብ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከድንበር ጦርነቱ ጋር በተያያዘ የተጀመረው የግዳጅ ብሔራዊ ውትድርና ሥልጠና ከኢኮኖሚ ድቀቱ ባሻገር ሌላው ለዜጎች ሀገር ጥሎ መሰደድ ምክንያት ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡

ከድንበር መከፈቱ ቀደም ብሎ በገፍ ወደ ኢትዮጵያ ይሰደዱ የነበሩት ኤርትራዊያን በኤርትራ ምንመ አይነት ለውጥ አለመታየቱን ተከትሎ የተሰዳጅነት ቁጥራቸው በብዙ እጥፍ ቢጨምር እንጂ የሚቆምበት ወይንም የሚቀንስበት ሁኔታ አይኖርም፡፡

ይህ ደግሞ ድሮም በቋፍ ላይ የነበረችውን ኤርትራን የበለጠ ወጣት አልባ ሀገር የሚያደርጋት ይሆናል፡፡ ፕሬዝደንት ኢሳያስ ለዓመታት የተዘጋውን የኢትዮ-ኤርትራ ደንበር እንዲከፈት ፈቃደኝነታቸውን ሲገልፁ የውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ማድረግ እስካልቻሉ ድረስ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ኮብላዩ ኤርትራዊ ወጣት በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር ዘንግተውታል ማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ሁለቱ ሀገራት ሰላም እስካወረዱ ድረስ የሰላማዊ ግንኙነቶቻቸው አንዱ መገለጫ የድንበር ግንኙነቱ በመሆኑ ምንም ማድረግ አልቻሉም፡፡

እናም በኤርትራ የውስጥ ፖለቲካ ለውጥ እስካልመጣና የሁለቱ ሀገራትም ደንበር ክፍት እስከሆነ ድረስ የኤርትራዊያን ኤርትራን ጥሎ ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ቀደም ሲል ከነበረው ቢጨምር እንጂ ሊቀንስ አይችልም፡፡ ትላንት በተጠመደ ፈንጂ መሀል አቆራርጦ የኢትዮጵያ ምድር ሲገባ የነበረ ኤርትራዊ ወጣት፤ ዛሬ ደንበር ሲከፈት ባለበት አርፎ ቁጭ ይላል ማለት ከሞኝነትም ያለፈ ቂልነት ነው፡፡ ትላንት በነፍሱ በመወራረድ ከድንበር ጠባቂ ወታደሮች የጥይት ራትነት አምልጦ የኢትዮጵያን መሬት እንደ ቤተክርስቲያን ሲሳለም የነበረ ኤርትራዊ ወጣት በድንበር መከፈቱ ማግስት እግሩን አጣጥፎ ይቀመጣል ማለት የተሳሳተ የፖለቲካ ስሌት ነው፡፡

እናም በኢትዮጵያና በኤርትራ ግንኙነት በኤርትራ ያለው የታፈነ የፖለቲካ ጠረን የሚቀየርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ፤ በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ኤርትራዊያን ወጣቶች ሀገር ምድራቸውን እየጣሉ ወደ ኢትዮጵያና ቀሪው ዓለም የማይሰደዱበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም ለአሁኑ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መዘጋት አንዱ የኤርትራዊያን ወጣቶች ሀገር ጥለው በገፍ ወደ ኢትዮጵያ መፍለስ ምክንያት ተደርጎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የኤርትራዊያን በአዲስ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ መፍለስ ሁለት ምክንያቶችን ያዘለ ነው፡፡ አንደኛው ኢትዮጵያን እንደመሸጋገሪያ ተጠቅሞ ወደ ሶስተኛ ሀገር መሄድ ሲሆን ሁለተኛው በኢትዮጵያ ኑሮን መመስረት ነው፡፡

ከፍልሰቱ ባሻገር ሌላኛው ለድንበሩ መዘጋት ተጠቃሽ ሊሆን የሚችለው ፖለቲካዊ ምክንያት ደግሞ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ አወቃቀር የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው ህወሓትና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ መካከል የነበረው የፖለቲካ ኩርፊያ ዛሬም የቀጠለ መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮ ኤርትራ የእርቀ ሰላም የወረደው በህወሓት የሥልጣን የበላይነት ማሽቆልቆልቅል ነው፡፡ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የተመራው ህወሓት፤ ኤርትራ አሁን ላለችበት የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ዳርጓታል፡፡ ኤርትራ ለዓመታት በዘለቀው ማዕቀብ እንድትማቅቅ በማድረጉ ረገድ ከአቶ መለስ ጀምሮ በጊዜው የነበሩት የህወሓት ቁልፍ ሰዎች ሚና ቀላል አልነበረም፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦር ከተማዘዙበት እለት ጀምሮ እስከዛሬም ድረስ ህወሓትን በደመኛ ጠላትነት ነው የሚያዩት፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም ማውረዳቸውን ተከትሎ ፕሬዝዳንቱ በአንድ ወቅት በሰጡት ማብራሪያ “ወያኔ ጨዋታው አብቅቷል; Woyane….. the game is over” ነበር ያሉት፡፡ አቶ በረከት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በህወሓት ላይ የቋጠሩትን ቂም በቀጥታ ባይናገሩም፤ በመቀሌው ስብሰባ ላይ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ጋር አያይዘው የአቶ ኢሳያስን Woyane …the game is over አባባል ቃል በቃል ደግመውታል፡፡ እናም ትግራይና ኤርትራ ሰፊ ድንበር የመጋራታቸውን ያህል አቶ ኢሳያስ ድንበሩ እንዲዘጋ ሲያደርጉ አንዱም ይሄው የህወሓትና የፕሬዝደንት ኢሳያስ የፖለቲካ ቂመኝነት ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡

ህወሓቶች የኢትዮ ኤርትራን ሀገራዊ ግንኙነት ትግራይን ማዕከልና መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲከወን ፅኑ ፍላጎታቸው ነው፡፡ ለዚህም ከሚሰጧቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የትግራይ ክልልና የኤርትራን ሰፊ የደንበር አዋሳኝነት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በትግራይና በኤርትራ መካከል ያለውን የህዝቦች ተመሳሳይ መገለጫና ሥነ ልቦናዊ ተመሳስሎሽም አንዱ ነጥብ ተደርጎ ሲነሳ ይሰማል፡፡

ዶክተር ደብረፅዮን የኢትዮ ኤርትራን ሰላም መውረድ ተከትሎ የትግራይን እና የኤርትራን ህዝቦች የጋራ የባህል የቋንቋና የሀይማኖት አንድነት እያጣቀሱ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የጋራ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተሰምተዋል፡፡

ኢሳያስ ፊታቸውን አዞሩባቸው እንጂ ዶክተር ደብረፅዮን በኤርትራ ኦፊሴላዊ ጉብኝት የማድረግ ፍላጎቱም ነበራቸው፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአማራ ክልል ኦፊሴላዊ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ አቶ ጌታቸው ረዳ በኤል ቲቪ በነበራቸው ቆይታ፤ “ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ትግራይ ቢመጡ ኖሮ ያላስተርጓሚ ለህዝቡ ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡” በማለት ቁጭት ቢጤ የሚታይበትን የሾርኒ አነጋገርን ተጠቅመዋል፡፡ ያም ሆኖ ኤርትራዊያን ባለስልጣናት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ በርካታ የአማራና የኦሮሚያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ወደ አስመራ ያመሩበት ሁኔታ ሲታይ አንድም የህወሓት አስመራ ጎራ ሲል አለመታየቱ፤ አቶ ኢሳያስና መንግስታቸው ህወሓት የያዙት ቂም ገና ያልተወራረደ መሆኑን ያሳያል፡፡

አቶ ኢሳያስ በህወሓት ላይ ከቋጠሩት የቀደመ ቂም፤ እንደዚሁም የህወሓት ሰዎች በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስም የኤርትራን ወጣቶች ልብ ለማሸፈት ከጀመሯቸው ጥረቶች ጋር በተያያዘ ጉዳዩ እባብ ለባብ ካብ ለካብ ሆኖ ታይቷል፡፡ በተለይ የኤርትራ ወጣቶችን በህብረት እያደራጁ በመሀል አገር ገንዘብ ተገንብተው ያንኑ የመሀል አገር ገበያን ታሳቢ ያደረጉትን በርካታ የኢፈርት ግዙፍ ኩባንያዎችን በፓኬጅ የማስጎብኘቱ ሥራ በተከታታይ መካሄዱ ለኤርትራ ባለስልጣናት ምቾት የሚሰጥ ሆኖ አልታየም፡፡

ይህ የህወሓት የአማላይነት ሥራ በአካባቢው እንደ ሰሜን ኮሪያ ዝግ ለነበሩት ኤርትራዊያን ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀገራቸው ምንም አይነት የልማት ሥራ እንዳልተሰራ አድረገው እንዲቆጥሩት አድርጓቸዋል፡፡ ኤርትራዊያኑ በትግራይ በተመለከቷቸው ግዙፍ የልማት ሥራዎች በትግራይ ቴሌቭዥን ቀርበው አድናቆታቸውን ሲገልፁ የታዩባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡

እነዚህ አካሄዶች ከኢትዮ ኤርትራ የድንበር ግጭት ማግስት በኤርትራ ብዙም የልማት ሥራ ያልተሰራ መሆኑን በማሳየት፤ ህዝቡ እንደ ሀገር ኋላ የመቅረት ሥነ ልቦና ጫና ውስጥ እንዲገባ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ይህች የኤርትራዊያንነ ልብ የማማለል አካሄድ በሌላ ቋንቋ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ከኤርትራዊያን ልብ ውስጥ ተፈንቅሎ እንዲወጣ የሚያደርግም ተግባር ነው፡፡ እናም ጨዋታው የፖለቲካ የገና ጨዋታ ነው፡፡ ከመቀሌ አስመራ የሚላጋ የፖለቲካ የካብ ለካብ ጨዋታ፡፡

ወደ ሌላኛው አስረጂ ጉዳይ እንሂድ፡-

በአካባቢው ከሱዳን ደንበር እስከ አፋር ጫፍ ያለው ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርም አንዱ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሥጋት ነው፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በውስጥ የፖለቲካ አካሄዳቸው አንድም ጋት የለውጥ ጅማሮ እንኳን አለማሳየታቸው ዛሬም የበርካታ ኤርትራዊያንን ኩርፊያ ሊያለዝበው አልቻለም፡፡ በትጥቅ ትግል የሳቸውን መንግስት ለማሰውገድ የሚንቀሳቀሱ በርካታ ኃይሎች አሉ፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ሁለቱ ሀገራት ከገቡበት የመጠላለፍ ፖለቲካ ጋር በተያያዘ ኤርትራ ለበርካታ የኢትዮጵያ መንግስት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ሀይሎች የሥልጠና እና የመንደርደሪያ ሜዳ ሆና ስታገለግል ቆይታለች፡፡

ሆኖም በኢትዮጵያ የታየው የውስጥ ፖለቲካ ውጥረት መርገብ፤ እንደዚሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም መውረዱ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎችን ነፍጥ እንዲያወርዱ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ በኤርትራ የውስጥ ፖለቲካ ለውጥ አለመምጣቱ የኤርትራዊያን ታጣቂ ኃይሎች በነበሩበት እንዲቀጥሉ አድርጓቸዋል፡፡ ልዩነቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለኤርትራ ታጣቂ ሀይሎች እንደቀደመው መንግስት ድጋፍና መጠለያ የማይሰጥ መሆኑ ነው፡፡

ሆኖም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ትግራይን በገዢነት ከሚያስተዳድረው ህወሀት ላይ ቂም ይዘው በተለይ ከትግራይ ጋር የሚያዋስነውን ደንበር ልቅ የማድረጋቸው ጉዳይ በወራት ውስጥ አስመራ የሚገባ ታጣቂ ኃይል እንዲፈጠር ማድረጉ አይቀርም፡፡ ህወሓቶች የፕሬዝደንት ኢሳያስ መንግስት ከገፋቸው በነሱ አምሳል የተቀረፀ መንግስት በአስመራ እንዲቀመጥ ፍላጎት አይኖራቸውም ማለት አይቻልም፡፡

ይህንን ለማድረግ ደግሞ ህወሓት ነፍጥ ያላወረዱትን የኤርትራ ኃይሎች ሊጠቀም ይችላል የሚሉ ስጋቶችም ይኖራሉ፡፡ እናም የፕሬዝዳንት ኢሳያስ መንግስት ደንበርና ፖለቲካውን ከፍቶ መጫወቱ ሊያስከትለው የሚችለው ፖለቲካዊ ኪሳራ ስሌት ውስጥ በማስገባት ወለል ብሎ የተከፈተውን የኢትዮ ኤርትራ ደንበር አንድም መዝጋት አለበለዚያ ገርበብ ማድረግን መርጧል፡፡ እናም ፕሬዝዳንት ኢሳያስና መንግስታቸው በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በስተመጨረሻ ደምረው፣አካፍለው፣ቀንሰውና አባዝተው የደረሱበት የፖለቲካ ስሌታዊ ድምዳሜ በሩን ገርበብ አድርጎ መጫወቱ የተሻለ መሆኑን ይመስላል፡፡

በሌላ አቅጣጫ የኢትዮ ኤርትራን ደንበር መልሶ መዘጋት አንዳንድ የትግራይ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ትግራይን በከበባ ውስጥ ከማስገባት ጋር አያይዘው አስተያቶችን ሲሰነዝሩ ተደምጠዋል፡፡ በአማራና ትግራይ አካባቢ በተደጋጋሚ የሚታዩ የመንገድ መዘጋቶችንና በቅርቡም በአፋርና በትግራይ መስመር የተፈጠረውን ችግርንም በማያያዝ ሁኔታውን ትግራይን መተንፈሻ ከማሳጣት የፖለቲካ ሴራ ጋር ያያይዙታል፡፡ በእርግጥ አላማው ትግራይን እንደ አንድ ክልል በማግለል ህወሓትን መነጠል ከሆነ በእንደዚህ አይነት የታፈነ የፖለቲካ አየር ውስጥ ህወሓትም ቢሆን አየር ሳይስብ በህይወት ይኖራል ማለት ይከብዳል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close