Connect with us

Ethiopia

እኛ እና ጠመንጃ | ኪዳኔ መካሻ

Published

on

እኛ እና ጠመንጃ | ኪዳኔ መካሻ

ጠመንጃ እና እኛ | ኪዳኔ መካሻ

በባህላዊዎቹ ድምፅ አልባ የጦር መሳሪያዎች ሲቀጣቀጥ የኖረው ህዝባችን እሳት የሚተፋ ብረት መኖሩን ያየው ከግራኝ መሀመድ ሰራዊት ሲተኮስበት ነበር።

ግራኝ ከቱርኩ የዘቢድ ፓሻ ያገኛቸውን መድፎችና ነፍጦች እንዲሁም የአረብ፣የግብፅ፣ የቱርክ እና የፐርሽያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ይዞ ነበር የተከሰተው።

የጠመንጃ ጉዳቱ ብቻ ሳይሆን ውለታውም አለብን።ግራኝን እንድናሸንፍ የረዱን የፖርቹጋል 400 መስኬተርስ ወይም ነፍጥ የታጠቁ ወታደሮች ነበሩ።

የወቅቱ ተአምራዊ ቴክኖሎጂ የነበረው ተተኳሽ መሳሪያ ታያ ከምቱ ይልቅ ድምፁ ነበር ሚና የሚጫወተው።በውጭ ወረራም ላይ ሆነ በኋላ ብረቱን በታጠቁ ገዥዎች እና ይሄን መሳሪያ በማያውቀው ባላገር መሀል በተደረጉ ውጊያዎች፤ የባላገር ሰራዊት የሚፈታው በመሳሪያዎቹ የፍንዳታ ድምፅ ነበር።

የአፄ ሱስንዮስ ገድል ፀሀፊ እንደከተበው ከአፄ እያሱ ጋር በተደረገው ውግያ ብዙ ጥይት ቢተኮስም በጥይት የሞተው ከሱስንዮስ ገአንድ ወታደር ብቻ ነበር።ታጣቂ እንጂ አልሞ ተኲዋሽ አልነበረም ለነገሩ በወቅቱ የመሳሪያዎቹን አተኳኮስ የሚያውቅ የሀገር ልጅ ስላልነበር የሚመጣው ከተኳሹ ጭምር ነበር።ሱስንዮስ እና ኢያሱ የተዋጉት በቱርክና በአረብ ቅጥረኛ ተኳሾች ነበር።

በቆይታ ግን እነኚህ መሳሪያዎች ሕዝባችን ለመዳቸው።ለገዢም ለተገዢም ፤ለአመፀኛውም ለሽፍታውም፤ መመኪያ ሆኑ። በአንዳንድ አካባቢዎች ባህል እስከመሆን ደረሱ።ከጥቃት መከላከያ፣ ደመኛን መበቀያ፣ ለልጅ የሚያወርሱት የወንድነት መለኪያ ሆኑ።

ለዘመነ መሳፍንት መከፋፈል አንዱ ምክንያት በነፍጥ የበላይነት የተፈሩ አንጋሾች መብዛት ነበር።
አፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን አንድነት ቢመልሱም፤በዘመኑ ጦር መሳሪያ እራስን የመቻሉ አስፈላጊነትስለገባቸው፤ እንግሊዛውያን ሚስዮኖችን አስረው በጋፋት ላይ መድፍ ለማሰራት አሰርተዋል። ሰሪው የራስ ሰው ባለመሆኑ በውጊያው ላይ የተማመኑበት መድፍ ከሸፈና፤እስካፍንጫው በታጠቀው የእንግሊዝ ጦር ለመሸነፍ በቁ።

እምዬ ምኒሊክም የጣልያንን ማድባት አይተው ከሀምቡርግ መቶ ሺ ጠመንጃና አስር ሚሊዬን ጥይት ቀድመው አዘው ነበር። የጀርመን መንግስት ግን ማእቀብ ጥሎ መሳሪያውን እንዳያገኙ አድርጓል።

የጀግኖች አባቶቻችን የነፃነት መንፈስ ግን በጦር መሳሪያ ብልጫም የማይገታ ነበርና በአድዋ ጦርነት ድል አድርገው አኩሪ ታሪክ አኖሩልን።

ይህ የሀያላኑ የጦር መሳሪያ ማእቀብ በ1928 ዓ.ም ቀጥሎ ስለነበር፤ፋሽስት ጣልያን በወቅቱ ዘመናዊ መሳሪያ ፣በመርዝ ጋዝ እና በአውሮፕላን ታግዛ ወረረችን፤ አባቶቻችን ግን በቁጥርም በጥራትም ተመጣጣኝ ባልሆነ መሳሪያ ለአምስት አመታት በዱር በገደሉ ጥልያንን አስጨንቀው ነፃነታችንን አስከብረው አቆዮልን።

ከነፃነትም በኋላ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የጉሱን ስልጣን አፅንቶ፤ማእከላዊ አስተዳደርን አጠናክሮ፤ አልገዛ ያለውን ገዝቶ፤ አማፅያንን እየደመሰሰ የቻለውን ያህል እንዲዘልቅ አድርጎታል።

በንጉሱም ጊዜ የነበረው አገዛዝ ያልተመቻቸው የባሌ እና የትግራይ ገበሬዎች ያላቸውን ጠመንጃና ጫካቸውን ተማምነው አምፀዋል።
ታሪክ እንደዘገበው ለማመፅም አመፅን ለማፈንም ለነፃነት ታጋይም ለአሸባሪም የጦር መሳሪያ ያስፈልጋል።

በተማሪዎች፣ በተራማጅ ምሁራንና በህዝቡ አብዮት የተገዘገዘው የንጉሱ ዙፋንንም፤ ብረት ያነገቱት ወታደሮች ገረሰሱትና በጠመንጃ ሀይል የህዝቡን አብዮት ነጠቁት ።ስልጣኑንም ተቆናጠው የተቃወማቸውን በጥይት እየቆሉ መምራታቸውን ቀጠሉ።

የደርጉን አገዛዝ የተቃወሙት የሰሜን ኢትዮጽያ አማፅያንም፥ ያንኑ ብረት አነሱና ሌሎችንም የብሔር ድርጅቶች አብረው ለ17 አመታት አታግለው በጠመንጃ ሀይል ደርግን አሸንፈው ስልጣን ተቆናጠጡ።

ከዛም ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት ኢህአዲግን ጠመንጃም ምርጫም ሳያሸንፈው እዚህ ደርሰናል..

የጦር መሳሪያን ነገር ወደ ግል ስናወርደው፤ ቀላል የጦር መሳሪያም ቢሆን ለመታጠቅ ፍቃድ ያስፈልጋል።

ፍቃዱን ምታገኘው የጀርባ ታሪክህ ታይቶ ፤የወንጀል ታሪክ እንደሌለብህና የአዕምሮህ ጤንነት አስተማማኝነቱ በፓሊስ እና በሀኪም ተረጋግጦ ነው።

በግለሰብ ደረጃ መሳሪያ የሚፈቀደው ለአደን፣ለኢላማ ተኩስ፣እራስን ከጥቃት ለመከላከል እና እራስን ለመጠበቅ ብቻ ነው።

የጦር መሳሪያ ማስመጣትም ሆነ ማምረት ሚችለው መከላከያ ሚኒስቴር ብቻ ነው። የጦር መሳሪያ ፍቃድ ሕግን የሚያወጣውም ሆነ መዝግቦ ፍቃድ ሰጥቶ የመቆጣጠሩ ስልጣን የፌደራሉ መንግስት ነው።

የሀገራችን የጦር መሳሪያ ባለቤትነት እና ቁጥጥር ህግ ጥብቅ ከሚባሉት የሚመደብ ነው።

ያለፍቃድ መሳሪያ ይዞ መገኘት፣ መጠቀም፣ ማዘዋወርም ሆነ ማጓጓዝ እንደየ ክብደቱ በወንጀል ያስቀጣሉ።
የጦር መሳሪያ እና እኛ ያለንን ቁርኝት እነኚህ ስነቃሎች እና ፋከራና ሸለላዎች የበለጠ ያሳዮታል…

ስጠኝ ምንሽሬን ቢለየኝ
አልወድም
ደም ከፈሰሰ ነው
የሚደርሰው ወንድም፡፡

ጥይት ጀሞልሟሌ ጥይት
ጀሞልሟሌ
ከሩቅ ያስታርቃል እንደ
ሽማግሌ
ምን ያለ ሰላቶ እንደበግ
እሚነዳ
ጥይቱ ነጭ አመድ በጣም
ሰው አይጎዳ
ታጠቅ ያገሬለጅ
ለማይቀረው እዳ፡፡

በል ግፋ በል ግፋ ጨምር
ያልፋል አንድ ሰሞን ችግርና
ጦር፡፡

እጥፍጥፍ ያለው እንደ ኩታ ልብስ፤
አተኳኮሱ አንጀት የሚያርስ።

የጠብ መንጃው ጢስ የርሳሱ መሪ፤
የጠቅል አሽከር የንጉስ ተፈሪ።

አባቱ ነበር ወንዝ አሻጋሪ፤
ደረሰ ልጁ ቅልጥም ሰባሪ፤
ከጥይት ጥይት መርጦ ቀርቃሪ።

ከላላ ከላላ ነው ቤቱ
ያበራል ጥይቱ
በካሳ ተሰማ ግጥም እንሰናበት…

ዋናው መታጠቁ ብቻ ሳይሆን ተኩሶ ኢላማን መምታቱ ነው።እናም ካሳ በአስገምጋሚ ድምፁ ይህን አዜመ..

የምር ተኳሹን እኛ ስናውቀው፥
ዝናር በቅፌን ማን ደባለቀው።

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close