Connect with us

Ethiopia

ደርግ እና የታደሰው ኢህአዴግ ምንና ምን ናቸው? | በጫሊ በላይነህ

Published

on

ደርግ እና የታደሰው ኢህአዴግ ምንና ምን ናቸው? | በጫሊ በላይነህ

ደርግ እና የታደሰው ኢህአዴግ ምንና ምን ናቸው? | ጫሊ በላይነህ

ለምን እንደሆን እንጃ!.. ደርግ እና የታደሰው ኢህአዴግ የመጀመሪያዎቹ የሥልጣን ወራት ፈተናዎቹ ይመሳሰሉብኛል።

#ደርግ

ደርግ በገጠመኝ ሥልጣን በእጁ ላይ ሲወድቅ ገና አንድ ፍሬ የምባል ሕጻን ልጅ ነበርኩኝ። ከታላቆችና ከተፃፉ የቃረምኩት ታሪክ ግን እንዲህ ይናገራል።

ደርግ ሥልጣን ሲይዝ ነጭ ሰሌዳ ነበር። ምሁራንና አማካሪ ተብዬዎች ያሻቸውን ጳፉበት።

አጋጣሚው አመቺ ነው ብለው የገመቱ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ወጠሩት፣ ትንፋሽ አሳጡት። በምስራቅ ሶማሌ፣ በመሀል የተማሪዎች፣ የሠራተኞች፣ የባለታክሲው፣ የወታደሩ.. ተቃውሞ ጨምሮ ኢህአፖ፣ መኢሶን፤…በሰሜን ሻዕቢያና ወያኔ ተጋግዘው ገዝግዘው ሊጥሉት ደረሱ።

ይባስ ብለውም በአዲስአበባ በጠራራ ፀሐይ ኮሎኔል መንግሥቱ ላይ ያልተሳካ የግድያ ሙከራ አደረጉ።

ጥቂት የማይባሉ ወገኖች ተቆጡ። “እርምጃ!..እርምጃ!” እያሉ በሁለት እግሩ ያልቆመው ደርግ ላይ ማንባረቅ ያዙ።

እናም “ነጭ ሰሌዳው” ደርግ፤ የተጻፈበትን እያጣቀሰ “ኢትዮጵያ ትቅደም!”፣ “አቆርቋዥዋ ይውደም!” እያለ የውስጥና የውጭ ትግል ውስጥ ተገፍቶ ወደቀ።

እንደዋዛ “ለእራት ያሰቡንን ለቁርስ አደረግናቸው” መባል ተጀመረ። “አብዮት ልጇን ትበላለች” ተባለ። ስንትና ስንት ምሁራንና ወገኖች በግራም በቀኝም ተቧድነው ተበላሉ።

ዘግይቶም ቢሆን ደርግ የተነሳበትን ተቃውሞ በኃይል መጨፍለቅ ቻለ። የለየለት አምባገነን ሥርዓትም የገነባበት መሠረትም ይኸው ነው።

እነዚያ አማካሪ ምሁራን ተብዬዎች አንዳንዶቹ ዛሬም አሉ። ዓይናቸውን በጨው አጥበው ደርግን ሲረግሙ የሚችላቸው የለም። ስለደርግ ጉድፎች አጠናን እያሉ ላለፉት 40 ዓመታት በየመድረኩ የማይነጥፍ ሳንቲም የሚቃርሙትም እነዚህ እርጉሞች ናቸው።

#ታዳሹ ኢህአዴግ!

ራሱን የለውጥ ኃይል ብሎ የሚጠራው በዶ/ር ዐብይ አሕመድ የሚመራው ኢህአዴግ ባልተጠበቀ ሁኔታ፣ በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን እጁ ላይ ወደቀ። በጣም በፍጥነት የሚታይና የሚዳሰስ ለውጥ በማሳየቱ ኢህአዴግ እንኳንስ በውን በቅዥት እንኳን ሊያየው የማይችለውን ከፍተኛ የሚባል የሕዝብ ድጋፍ ሊጎርፍለት ቻለ።

ይህም ሆኖ የመሪ ድርጅቱ አስኳል የሆነው ህወሓት መርጦ ካስቀመጠው ጠ/ሚኒስትር ላይ ኩርፊያውን ለመዘርገፍ አንድ ዓመት እንኳን መታገስ አልቻለም። በዚህ ላይ የለውጡ አካል የሆነውን ያለፉ ብልሽቶች ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረት አንድ ጊዜ ሕገመንግሥት ተጣሰ፣ ሌላ ጊዜ በወንጀል የተጠረጠረ ግለሰብ ለምን በካቴና ታስሮ ታየ አንካ ሰላንቲያ ውስጥ ተዘፈቀ። በሌብነትና በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦች መቀለ እንዲመሽጉ ፈቀደ።

በሌላ በኩል በህወሓት ይደገፋሉ የሚባሉ አንዳንድ ክልሎች ሰፊ የሕዝብ መፈናቀልን ያስከተሉ ግጭቶችን አስተናገዱ።

በመሀል አዲስ አበባ ሳይቀር ጠ/ሚኒስትሩን ኢላማ ያደረገ የግድያ ሙከራ መንግሥት ውስጥ በተሰገሰጉ አፈንጋጮች ተደርጎ የንጹሀን ዜጎችን ደም አፈሰሰ።

እስከአፍንጫቸው የታጠቁ አኩራፊ የሠራዊት አባላት ቤተመንግሥት ድረስ ገስግሰው ጠ/ሚኒስትሩ ባሉበት ድንገተኛ ሁከት ለመፍጠር የሞከሩት በለውጥ አደናቃፊ ኃይሎች ግፊት ነበር።

በዳውድ ኢብሳ የሚመራውና በቦሌ በቪአይፒ ሳሎን በከፍተኛ ክብር ወደ አገር የገባው ኦነግ በአራት ወር ቆይታው “ከመንግሥት ጋር የገባሁት ውል አልተከበረልኝም” ብሎ በተለይም በምስራቅ ወለጋና በሞያሌ አካባቢ ሕዝብ ላይ መተኮስ ከጀመረ ዋል አደር ብሏል።

የዶክተር ዐብይ መንግሥት ይህ ሁሉ እልቂት፣ የሕዝብ መፈናቀል፣ አለመረጋጋት… ሲደርስ አንድ ጥይት ላለመተኮስ ትግዕስትን መርጦ ቆይቷል። ግን በስተመጨረሻ ነገሩ “ፍቅር”፣ “ይቅርታ”፣ “መቻቻል”…በሚባሉ የቅዱስ መፅሐፍ አስጎምዥ ታሪኮች እንደማይሆን የተረዳ መስሏል።

የትላንትናው የኦህዴድ/ኦዴፖ የሥራ አስፈፃሚ ኮምቴ መግለጫ የትግዕስቱ ጊዜ ማብቃቱን ያወጀ ሆኗል።

እናም ፍቅር ሰባኪው የዶክተር ዐብይ መንግሥት ሳይወድ ተገድዶ የተነሳበትን የግጭትና የሁከት መንገድ በኃይል ለመጨፍለቅ የተገደደበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ደርሷል።

መጨረሻው ምን ይሆን?

የዶክተር ዐብይ መንግሥት ድል ቀንቶት እሾህ አሜከላውን አስወግዶ ዴሞክራት ሥርዓትን የመገንባት ዕድል ይኖረው ይሆን ወይንስ የኃይል፣ የጡንቻ መንገዱ ይጥመው ይሆን የሚለውን ቀጣይ የታሪክ ክፍል በቅርብ የምናየው ይሆናል።
ያሰንብተን!

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close