Connect with us

Ethiopia

ሕወሓትን ከሥልጣን ያስወገደችው አሜሪካ ትሆን?

Published

on

ሕወሓትን ከሥልጣን ያስወገደችው አሜሪካ ትሆን?

ሕወሓትን ከሥልጣን ያስወገደችው አሜሪካ ትሆን? | ፀጋው መላኩ@DireTube

•የስብሃት ነጋ ፀፀት

በቅርቡ በመቀሌ የተካሄደው ስብሰባ ላይ ለህወሓት ከስልጣን መወገድ የአሜሪካ እጅ እንደነበረበት አቶ ስብሀት ነጋ ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ነገርየው ከሥረ መሰረቱ ሲመረመር መልሱ “አዎ ከህወሓት ከሥልጣን መወገድ ጀርባ የአሜሪካ እጅ አለበት” የሚለውን የማያሻማ ምላሽ እናገኛለን፡፡

እንዴት የሚለውን ጉዳይ በጥቂቱም ቢሆን እንመርምረው፡-

የአሜሪካኖች አንዱ የፖለቲካ ጥንካሬ በየትኛውም አካባቢ ያለውን ማንኛወንም መረጃ መሰብሰብ መቻላቸው ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰቡት መረጃዎች ለሁለት መሰረታዊ ጥቅሞች እንዲውሉ ይደረጋል፡፡ የመጀመሪያው ለሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት አገልግሎት ግብአትነት የሚያገለግል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለምትከተለው የውጭ ፖሊሲ ዋነኛ አቅጣጫ ጠቋሚ ሆኖ ያገለግላል፡፡

ሥራው በመረጃ ስብሰባ ብቻ አያበቃም፡፡ የተሰበሰበው መረጃ በሚገባ ይተነተናል፡፡ አሁንም ምዕራፉ በስብስባና ትንተናም ብቻ አይጠናቀቅም፡፡ የተሰበሰበውን መረጃ ተንተርሶ ምን አይነት ተግባራዊ ለውጥ እንደሚከተል የራሱ የሆነ የአተገባበር መርሃ ግብር ይወጣለታል፡፡ በዚህ መሰረት በተለይ ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሲሰበሰብ የነበረው መረጃ በአብዘሃኛው አሜሪካ በአካባቢው ሽብርን በመከላከል ላይ መሰረት አድርጋ ፖሊሲዋን እንድትቀርፅ ግብዓትና ምክንያት ሆኗል፡፡

ለዚህ የአሜሪካ የምስራቅ አፍሪካ የፀረ ሽብር ፖሊሲ መነሻ የሆነው ደግሞ የሶማሊያን መንግስት አልባነት ተከትሎ ሀገሪቱ እንደ እስላማዊ ፍርድቤቶችና አልሸባብን የመሰሉ አሸባሪዎች መነሀሪያ መሆኗ ነበር፡፡ አሜሪካዊያን አንድ ሀገር መንግስት አልባ ሲሆን በአሜሪካ ላይ ምን አይነት ሀገራዊ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል በአፍጋኒስታን በሚገባ አይተውታል፡፡ አፍጋኒስታን መንግስት አልባ መሆኗ ቢላደን እና አጋሮቹ ባገኙት ነፃ ምድር ዶልተው በአሜሪካ ላይ የመስከረም አስራ አንዱን ከባድ ጥቃት አድርሰዋል፡፡ እናም ከዚህ ትምህርት የወሰዱት አሜሪካዊያን ከአፍጋኒስታን ቀጥሎ ሌላኛዋ መንግስት አልባ በሆነችው ሶማሊያ ላይ የትኩረት አቅጣጨውን አደረጉ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ“ሥጋት” ተብለው የተፈረጁ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎችና መሪዎቻቸው በሶማሊያ ምድር መሰብሰባቸው ደግሞ የፖለቲካ ግለቱን አናረው፡፡ የአፍጋኒስታንን የሽብር እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ፓኪስታን ለአሜሪካዊያኑ አስፈላጊ እንደነበረች ሁሉ፡፡ የሶማሊያን የሽብር ሥጋት ለማስወገድ ደግሞ ኢትዮጵያ ዋነኛ የማጫወቻው ማዕከል ሆና ተመረጠች፡፡

ይህች ውሳኔ ለህወሓት ኢህአዴግ ወሳኝ የሥልጣን ማጥበቂያ ምዕራፍ ነበረች፡፡ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው አሜሪካዊያን የሚሰበስቧቸው መረጃዎች ለሀገሪቱ ብሄራዊ ደህንነት ብሎም ለውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ግብዓትነት የሚጠቀሙባቸው ናቸው፡፡

የሶማሊያ ጉዳይ ደግሞ በመንግስት አልባነቷ የአሸባሪዎች መነሀሪያ መሆኗ ከአሜሪካ ብሄራዊ ደህነነት ሥጋት በመነጨ የምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲ በፀረ ሽብር ዘመቻ ላይ ተመስርቶ እንዲያጠነጥን ማድረጉ የደስታ ጡዘት ውስጥ ያስገባው ህወሓት፤ በፀረ ሽብር ሥም የሶማሊያ አክራሪ እስላማዊያን ኃይሎች የሽብር እድሜ እንዲራዘምለት አንጋጦ መፀለይ ጀመረ፡፡

አሜሪካዊያን “የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምናደርገው የፀረ ሽብር ዘመቻ ዋነኛ አጋራችን ነው” በማለት በየዓለም አቀፉ መድረግ በይፋ መዋጅ ጀመሩ፡፡ እናም በሁለቱ መንግስታት መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብርና የመረጃ ልውውጥ ጦፈ፡፡ በዚህ መሀል ግን በሁለቱ መንግስታት መካከል አንድ መግባባት ላይ ተደረሰ፡፡ ይህም ሥምምነት የኢትዮጵያ መንግስት ጦሩን ወደ ሶማሊያ በማስገባት በጊዜው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤት ወይንም ኢዝላሚክ ኮርትስ ዩኒየን የሚባለውን ኃይል እንዲደመስስ ወታደራዊ ተልዕኮን የሚሰጥ ነበር፡፡

በጊዜው የነበረው የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መንግስት በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ሳያቅማማ የኢትዮጵያን ጦር ወደ ሶማሊያ ምድር አስገባ፡፡ የመደበኛ ጦር የውጊያ ሥልት ያልነበረው የእስላማዊ ፍርድ ቤት ጦር በአሜሪካ መሳሪያ የታገዘውን የኢትዮጵያ ጦር ብዙም ሳይከላከል በየአካባቢው ተበታተነ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ጦር ነፃ ስለወጡት የሶማሊያ ከተሞች ይናገሩ የነበሩት የመንግስት መገናኛ ብዙኋን የጦርነት ስትራቴጂው ተቀይሮ የሶማሊያ ምድር ለኢትዮጵያ ጦር የእግር እሳት ስትሆን ላንቃቸውን ዘጉ፡፡ እስላማዊ ፍርድቤቱ ቢደመሰስም አልሸባብ የተባለው የወጣቶች ኃይል በአዲስ መልክ ራሱን አደራጅቶ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ግንባር አልባ ውጊያን ማካሄድ ጀመረ፡፡

አሜሪካዊያኑም በጊዜው በፀረ ሽብር ዘመቻ ከህወሓት ኢህአዴግ መንግስት ጋር በፈጠሩት ያለአቻ ጋብቻ ቁርኝት፤ ረብጣ ዶላራቸውን ማፍሰስ ጀመሩ፡፡ የሀገሪቱ አየር ኃይል ሚሊዮን ዶላሮችን አፍስሶ የአርባምንጭ ኤርፖርትን በማደስ ከፍተኛ የሆኑ የስለላ ወታደራዊ መሳሪያዎችን በአካባቢው በመትከል የሶማሊያ አሸባሪ ኃይሎችን በቅርብ ርቀት መከታተል ጀመረ፡፡

ልዩ የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎች የተገጠሙላቸው ሰው አልባ አውሮፕላኖችም ከአርባ ምንጭ እየተነሱ እስከ ህንድ ውቅያኖስ የሚዘልቀውን የሶማሊያ ግዛት ማካለሉን ተያያዙት፡፡ የሚሰበሰበውን መረጃ መሰረት በማድረግም የአልሸባብና የአልቃይዳ አመራሮችን ለይቶ በሰው አልባ አውሮፕላን የመግደሉ ሥራ በስፋት ተሄደበት፡፡ ውጤትም አስገኘ፡፡

በሰሜን ኤርትራ በሽበር ሰፖንሰርነት ተመዝግባ በተበባሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ ሥር መውደቅ ግድ ሆኖባታል፡፡ በኢትዮጵያ ምዕራብ አቅጣጫ ያለችው ሱዳን በአሸባሪነት ስም የአሜሪካ ማዕቀብ ልጓም ውስጥ ገብታ በመማቀቅ ላይ ናት፡፡ በስተምስራቅ የምትገኘው ሶማሊያ ዋነኛ የአሸባሪዎች መፈልፈያ ሆናለች፡፡ የደቡብ አቅጣጫዋ ኬኒያ የምዕራባዊያኑ ፖለቲካ ደጋፊና አቀንቃኝ ብትሆንም፤ ብዙም በአካባቢያዊ ጂኦፖለቲካ ሽርጉዱ የለችበትም፡፡

እናም በጊዜው በአካባቢው በምዕራባዊያኑ የፀረ ሽብር አጋርነት ዋነኛ የተውኔቱ ገፀ ባህሪ ሆና የገነነችው ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
አቶ መለስ የሶማሊያን መንግስት አልባነትና የምዕራባዊያኑን የናረ የፀረ ሽብር ዘመቻ ተጠቅመው ራሳቸውን በከፍታ ማማ ላይ ሰቀሉ፡፡ የሀገር ውስጡን የፖለቲካ ውጥንቅጥ ትተው ራሳቸው በዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ ልኬት ውስጥ አስቀመጡ፡፡ በቡድን ሰባትና በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ፎረም ላይ ቋሚ ተሰላፊ ሆኑ፡፡ በዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ተንታኝና ዋነኛ ተሟጋች ሆነው ብቅ አሉ፡፡ በንግግር አዋቂነታቸውና በሞጋችነታቸው ብዙ ይባልላቸው ገባ፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ከምርጫ 97 ማግስት እልቂት በኋላ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ በእነዚያ በድህረ ምርጫ 97 ተከታታይ ዓመታት ሕወሓት ኢህአዴግ በአቶ መለስ ዋነኛ ተዋናይነት የአፍሪካ ቀንድን ስስ የጂኦ ፖለቲካ የፖለቲካ ብልትን በመለየት የአሜሪካዊያንን የሽብር ሥጋት ተጠቅሞ የሹም ዶሮ ሆኑ፡፡

እናም

አቶ መለስና ድርጅታቸው ህወሓት ኢህአዴግ የዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር አጋርነታቸውን ለሀገር ውስጥ የፖለቲካ አፈና መሳሪያነት በሚገባ ተጠቀሙበት፡፡ ከሀገሪቱ ሕገ መንግስትም ሆነ ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ቃል ኪዳኖች ውጪ በፓርላማው የፀደቀው የፀረ ሽብር ህግ በርካቶችን ሰለባ ሲያደርግ፣በክቡር የዳኝነት ሙያ ላይ ሲቀለድና ሲዘበት፣ ራስ ከሳሽ፣ ምስክርና አቃቤ ህግ ሆኖ ሰብአዊ በሆነው የሰው ልጅ ላይ የግፍ ፍርድ ሲሰጥ አሜሪካዊያን ሰምተው እንዳልሰሙ፣ አይተው እንዳላዩ ሆኑ፡፡

በምርጫ 97 ማግስት እንኳን የኢትዮጵያን መንግስት እርምጃ በማውገዝ የአውሮፓ ሕብረት አቋም ሲይዝ አሜሪካ ዝምታን መረጠች፡፡

አሜሪካዊያን ዜጎቻቸውን ከሽብር ጥቃት ለመጠበቅ ሲያካሂዱት የነበረው ዓለም አቀፍ ዘመቻ ለኢትዮጵያ ጥቁር መጋረጃ ሆነ፡፡ በመላ ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በየአደባባዩ እየወጡ ድምፃቸውን ቢያሰሙም፣ አምንስቲ አኒተርናሽናልና ሂውማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ እየተሰራ ያለውን ግፍ ቢያጋልጡም አሜሪካና አጋሮቿ “አውቆ የተኛን “ ሆኑና ቢቀሰቅሷቸው አልሰማም አሉ፡፡

አቶ መለስ ከመጋረጃ ጀርባ የሚደርሳቸውን ስስ ግሳፄ እንኳን መስማት የማይፈልጉ ሆኑ፡፡ ይባስ ብለው በምዕራባዊያኑን የኢኮኖሚ ፍልስፍና ላይ ኒኦሊብራል፣ የገበያ አክራሪ፣ የሌሊት ዘበኛ ወይንም ናይት ዎችማን በማለት የሰላ ትችታቸውን ማዝነብ ጀመሩ፡፡

ነገርየው ጠንከር ሲልም የአሜሪካን የኢኮኖሚ ባላንጣ የሆነችውን ቻይና በአፍሪካ ምድር መንሰራፋት ትችል ዘንድ ኢትዮጵያን የአፍሪካ በር አድርገው ለመጠቀም ሽርጉዱን ተያያዙት፡፡ እናም የቻይና ብድርና እርዳታ ወደ ኢትዮጵያ ይጎርፍ ጀመር፡፡ ባቡሩ፣ መንገዱ፣ ቴሌኮም ድርጅቱ፣ የኤርፖርት ማስፋፊያው ሁሉ ነገር ቻይና በቻይና ሆነ፡፡

የኢትዮ ቻይና የኢኮኖሚ ትስስር ለመላው አፍሪካ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በሞዴልነት መቅረብም ጀመረ፡፡ ኢህአዴግም ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነቱን መሰረተ፡፡ እናም አቶ መለስና ድርጅታቸው ህወሓት ኢህአዴግ የምዕራባዊያኑንና የቻይናን የተለያየ መንገድ ተከትለው በአንድ ጊዜ መሮጥ ፈለጉ፤ ሞከሩትም፡፡ እናም ነገርየው “ሁለት እግር አለኝ ተብሎ ሁለት ዘፍ ላይ አይወጣም” ሆነና አንዱን ጠበቅ ሌላውን ለቀቅ የማድረጉ ጉዳይ ግድ ሆነ፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ከተረጋጋ፣በሶማሊያ መንግስት መቆም ከቻለና የዓለም አቀፉ የሽብር ሥጋት የሙቀት መጠን መውረድ ከጀመረ፤ በምዕራባዊያኑ በኩል ሕወሓት ኢህአዴግ የሚመዘነው በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ምግባሩ እንጂ፤ በፀረ ሽብር አጋርነቱ አይደለም፡፡

ይህችን እውነታ የህወሓት ሰዎች ጠንቀቀው ያውቋታል፡፡ እናም በጊዜ ወደሚበጀው የፖለቲካ አሰላለፍ መጠጋት ግድ ማለቱ አልቀረም፡፡ ይህቺ የሰልፍ መስመር ደግሞ ሰብዓዊ መብት፣ የፕሬስ ነፃነት፣ ምርጫ ማናምን የሚባሉት የዲሞክራሲ መገለጫዎች የሀገርና የመንግስት መገለጫዎቿ ያልሆኑት ቻይና ናት፡፡ ቻይና በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት ወይንም ፕሪንስፕል ኦፍ ነን ኢንተርፊራንስ በሚለው መርኋ መሰረት የሀገርን ስኬት የምትለካው ቁሳዊ በሆነው የኢኮኖሚ ልማት ብቻ እንጂ፡ ሌላ የምታስቀምጠው ፖለቲካዊ ጉዳይ የላትም፡፡

በጊዜው አቶ መለስ በኒኦሊብራል ስም አሜሪካና አጋሮቿን እያወገዙ ቆዳቸውን ከቻይና ጋር ሲያዋድዱ የማይነካውን ማኖ እየነኩ ነበር፡፡ እናም እስከዛሬም ድረስ አቶ መለስ አሟሟተቸው ግልፅ ባልሆነ መልኩ ከሜክሲኮ ካንኩን ዓለም አቀፍ ስብሰባ ሲመለሱ ፊታቸው ላይ የሞት ጣረሞት ተነበበ፡፡ ብዙም ሳይቆዩ በዚያው በምዕራቢያኑ ሀገር ቤልጂየም ሴንት ሉክ ሆስፒታል ሕክምናቸውን በመከታተል ላይ እያሉ ህይወታቸው አለፈ፡፡ እንዴት ሞቱ? በምን ሞቱ? የሚለው ጉዳይ እስከዛሬም ግልፅ አይደለም፡፡ በጊዜው የአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት ለህወሓት ፖለቲካ ንጉሱን ተበልቶ ጨዋታውን ለማሸነፍ እንደመሞከር ሆነ፡፡ የቁልቁለት ጉዞው አንድ ብሎ የጀመረውም ያኔ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ በሂደት የዓለም አቀፉ ሁኔታ መቀየር ጀመረ፡፡ አልቀይዳ ተዳከመ፣ መሪው ቢላደን ተገደለ፡፡ በሶማሊያ የሽግግር መንግስት ተቋቁሞ፤ በሂደትም የፌደራሉ መንግስት ተመሰረተ፡፡ ሶማሊያዊያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው መወጣት ይችሉ ዘንድ ከአሜሪካና ከአውሮፓ ሰፊ እገዛ ይደረግላቸው ጀመር፡፡ የአልቃይዳ፣ የቦኮሀራም፣ የአልሸባብ፣ እንደዚሁም ድምፁ የጠፋው አይ ኤስ አይ ኤስን እና የመሳሰሉ አሸባሪ ኃይሎች መዳከም ፋታ የሰጣት አሜሪካ ዓለም አቀፍ የፀረ ሽብር ዘመቻዋን በብዙ መልኩ አቀዛቀዘች፡፡ ጦሯን ከአፍጋኒስታን እና ከኢራቅ አስወጣች፡፡ በብዙ መልኩም በዘርፉ ባለው እንቅስቃሴዎች ላይ የበጀት ቅነሳ አደረገች፡፡

የህወሓት የመጫዋቻ ካርድ መነጠቅ የጀመረውም እዚህ ጋር ነው፡፡ በምዕራባዊያኑ ድጋፍ የሶማሊያ ጉዳይ በራሳቸው በሶማሊያዊያን መፈታት ሲጀምር የኢትዮጵያ መንግስት የፀረ ሽብር ዘመቻ አጋርነት በብዙ ፐርሰንት ወረደ፡፡

አሜሪካዊያን በሱዳን ላይ ጥለውት የነበረውን ማዕቀብ አነሱ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከሽብር ጋር በተያያዘ ከኤርትራ መንግስት ጋር የነበራቸውን አለመግባባት ለመፍታት ፍላጎታቸውንም ማሳየት ጀመሩ፡፡ እናም የአፍሪካው ቀንድ የፖለቲካ ጠረን መቀየር ጀመረ፡፡ በዚህ የአፍሪካ ቀንድ ውጥረትና የዓለም አቀፉ የሽብር ዘመቻ ተባባሪነት ሥም በብዙ ያተረፈው የህወሓት ኢህአዴግ መንግስት የአካባቢው የፖለቲካ አየር ሲለወወጥ ተፈላጊነቱ አሽቆለቆለ፡፡

ይባስ ብሎም በ2008 የሀገር ውስጥ ተቃውሞው ሲቀሰቀስ የድርጅቱ ሀገራዊ መቆሚያ መሰረቱም መናድ ጀመረ፡፡ በዚህ ወቅት አሜሪካዊያን ሕወሓትን በፀረ ሽብር አጋርነቱ ሳይሆን በሥራው መመዘን ጀመሩ፡፡

የአቋም ለውጦች፣የቃላት ሽንቆጣዎች በአደባባይ ይሰሙ ጀመር፡፡ በቀደሙት ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈፀመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ አካል እንዲጣራ፤ እንደዚሁም አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የሚጠይቀው ኤች አር 128 በአሜሪካ ኮንግረንስ ፀደቀ፡፡ ግፊቶች በተለያየ አቅጣጫ ቀጠሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሁለተኛውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲጥል ፤ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ የተቃውሞ ድምፁን አሰማ፡፡ ኢምባሲው በጊዜው ባወጣው መግለጫም “በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር ነፃነትን በማብዛትና ሁሉን አቀፍ ዲሞክራሲን በማስፈን እንጂ ገደብ ሊፈታ አይችልም” በማለት የተለየ አቋሙን አንፀባረቀ፡፡
እናም የአሜሪካ መንግስት ያረጀ ያፈጀውን የህወሓት ኢህአዴግ አስተሳሰብ እንዳበቃለት ሲረዳ የተለየ አቋምን መያዙ የአደባባይ ሚስጥር እየሆ ሄደ፡፡ በሰፈሩት ቁና መሰፈር ማለት ይህ ነው፡፡

በደርግ መውደቂያ ዋዜማ በሻዕብያ መካናይዝድ ጦር የታጀበው የኢህአዴግ ጦር አዲስ አበባ እንዲገባ በማድረጉ ረገድ በለንደኑ ኮንፍረንስ አረንጓንዴ መብራት በማሳየት በትረ መንግስቱን ለአቶ መለስና አጋሮቻቸው የሰጠችው አሜሪካ፤ ከ27 ዓመታት በኋላ ፊቷን በህወሓት ላይ አዞረች፡፡ በለንደኑ ኮንፍረንስ ህወሓት ኢህአዴግ የመንግስትነት ስልጣኑን እንዲረከብ ያመቻቹት አሜሪካዊው ዲፕሎማት ሚስተር ኸርማን ኮኽን በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ቀርበው፤ በህወሓት አፀያፊ ተግባር ማዘናቸውንና መፀፀታቸውን ገለፁ፡፡ እናም ህወሓት በሀገር ውስጡ ተቃውሞ ብርታና በአሜሪካ ተፅዕኖ ከሚያመልከው የሥልጣን ማማ መውረድ ግድ ሆነበት፡፡

በአንድ ቡድን አምባገነንነት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ትርምስ ውስጥ ከሚገባ ይልቅ ያንን ቡድን ከሥልጣን ማስወገድ እንደሚገባ ያመኑት አሜሪካኖች፤ በኤችአር-128 ማስፈራሪያነት እና በዕውቁ ዲፕሎማት ዶናልድ ያማሞቶ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በህዝብ አመፅ የተፍረከረውን የህወሓት አገዛዝ አስወገዱት፡፡

ያማሞቶም ኤርትራ በመሄድ ኢሳያስን አግባብተው ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም እንዲወርድ አደረጉ፡፡ የህወሓት የፀረ ሽብር ዘመቻ አጋርነት መጫወቻ ካርድ በነበረችው ሶማሊያ አንፃራዊ ሰላም በመውረዱም አሜሪካ ከ28 ዓመታት በኋላ በሶማሊያ ኢምባሲዋን ከፈተች፡፡ በኤርትራ ላይ የተጣለውም ማዕቀብ ተነሳ፡፡ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሶማሊያ መሪዎችም በጋራ ሲመክሩ ታየ፡፡ የአካባቢው ፖለቲካዊ ውጥረት ምንጭ የነበረው ህወሓት የሥልጣን እድሜው ማብቃቱ ሀገራዊም ሆነ አካባቢያዊ የፖለቲካ ውጥረቱን አረገበው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close