Connect with us

Africa

ግብጽ በጅቡቲ በኩል ልትመጣ?!

Published

on

ግብጽ በጅቡቲ በኩል ልትመጣ?! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ግብጽ በጅቡቲ በኩል ልትመጣ?! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን@DireTube

የጅቡቲው አምባሳደር በግብጽ ፓርላማ ተገኝተዋል፡፡ ስብሰባቸው ምስጢራዊ አይደለም፡፡ ሆን ተብሎ የመገናኛብዙሃን ሽፋን እንዲያገኝ ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ መሀመድ ሆርሲ የሚናገሩበት ቅልጥፍናና ፍጥነት ቁጭት እና እልህ የሚነበብበት ነው፡፡

አምባሳደሩ‹‹ አንድ ሚሊዮን ኪሎሜትር ስኩየር ግዛታችንን እንሰጣችኋለን፤ አልሲሲን በጣም ነው የማደንቃቸው፤ በሚቀጥለው የአፍሪቃ ሕብረት ሊቀመንበር በመሆናቸው እኛ ጅቡቲዎች ደስ ብሎናል…››ወዘተ እያሉ ሲናገሩ ከኋላ ኪሳቸው አውጥተው የሚሰጡ ነው የሚመስሉት፡፡

ይህ የሆነው ባሳለፍነው ሳምንት ነው፡፡ ግብጽ ከጅቡቲ አንድ ሚሊዮን ስኩየር ኪሎሜትር ባሕር ተለገሳት የሚለው ዜና ጆሮ ገብ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ይህ ዜና ሀቅ ነው፡፡ የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ድቤ ሲመቱበት የከረሙመበት ዜና ነው፡፡በርግጥም ግብጽ እዚህ ኢትዮጵያ መውጫና መግቢያ ላይ ፣እዚች ኢትዮጵያ እስትንፋስ ላይ ሰፊ ባሕር ልትከራይ ነው፡፡

ግብጽ ግን ለምን ጅቡቲን መረጠች፣ ለኢትዮጵያስ ያለው ትርጉም ምንድን ነው፣ ጥያቄው ይህ ነው፡፡

ይህ የግብጽ መንገድ ታስቦበት እና የአፍሪቃ ቀንድን የወቅቱን ፖለቲካዊ አሰላለፍ ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ጅቡቲዎች በኢትዮጵያ ተከፍተዋል፡፡ በተለይም የኤርትራና የሱማሊያ መሪዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የባሕርዳሩን ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ፣ጅቡቲዎች ሆድ ብሷቸዋል፡፡

ከ85 በመቶ በላይ ወጪ ገቢዋን ኢትዮጵያ ላይ የመሰረተችው ጅቡቲ፣ዋነኛ ደንበኛዋ እየተወችኝ እየካደችኝም ነው ብላ አስባለች፡፡

ይህንን ጉዳይ ደግሞ ግብጽ በሚገባ ታውቃለች፡፡እናም ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው የካይሮ ሰዎች ወደ ጅቡቲ ለመምጣት ቢወስኑ የሚገርም አይሆንም፡፡

የአረባዊቷ ሀገር የደኅንነት መሥሪያቤትም ከአዲስ አበባ በ600 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ቢሮ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወጪ ገቢ ምርቷን ብቻ ሳይሆን፣ብሔራዊ ደኅንነቷን ለመጠበቅ የሚያስችላትን መሳሪያ ስታስገባም እየፈተሹ የሚልኩልን የግብጽ ደኅንነቶች ይሆናሉ፡፡

ጅቡቲዎች ለዚህ ውለታቸው የግብጽ ዩኒቨርሲቲዎች ቅርንጫፍ እንዲከፍቱ ጠይቀዋል፡፡እናም በቅርቡ የግብጽ የውሃ ኢንጂነሪንግ እና ኢንቴሊጀንስ ዩኒቨርሲቲዎች እዚሁ አጠገባችን መጥተው ‹ያስተምራሉ› ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ግብጾች የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ የሱማሌላንድን ባለሥልጣናት መሬትና ባሕር እንዲያከራዩአቸው፣ለዚህም ውለታቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደሚከፈላቸው፣ዩኒቨርሲቲ እንደሚከፈትላቸው፣ተማሪዎቻቸው ነፃ የት/ት እድል እንደሚሰጣቸው ቃል ገብተው ነበር፡፡

ሆኖም የሱማሊ ላንድ ባለሥልጣናት ይህንን ጉዳይ ውድቅ ያደረጉት ወዲያውኑ ነበር፡፡የግብጽን ልዑክ እየመሩ ወደ ሀርጌሳ ያመሩት ደግሞ አሁን የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይሚኒስትር ምክትል የሆኑት፣ ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ የግብጽ አምባሳደር የሆኑት መሀመድ ኢንድሪስ ነበሩ፡፡

በመጨረሻ ግን የሱማሊላንድ ባለሥልጣናት ‹‹ግብጽ ከዚያድባሬ ጋር ተባብራ ስትወጋን፣ ኢትዮጵያ መጠጊያችን ነበረች፤ እናም ከኢትዮጵያ ጥቅም በተቃራኒ የሆነ ሥራ አንሰራም››አሉ፡፡ የመሀመድ ኢንድሪስ ልዑክም ወደ ሐገሩ ተመለሰ፡፡

እናም ኤርትራን ጠበቅ አድርጎ መያዝ ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ ግብጾች አመኑ፡፡ ወዲያውም አቶ ኢሳያስን ካይሮ ጠርተው ምስጢራዊ ውይይት አደረጉ፡፡ ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ በኋላ ኤርትራ የግብጽ ዋነኛ አጋር ሆና ቀጠለች፡፡ ድንገት ከኢትዮጵያ ጋር የታረቀችው ኤርትራ ግን ለጊዜውም ቢሆን የግብጽ ወዳጅ ሆና እንደማትቀጥል ፈረኦኖቹ ተረዱ፡፡ ቢያንስ በየ አምስት ወራት ወደ ካይሮ ይጓዙ የነበሩት የኤርትራ ባለሥልጣናትም ላለፉት 10 ወራት የግብጽን ምድር ረግጠው አያውቁም፡፡ ለዚያም ነው ግብጾች ጅቡቲን ማመናቸውና መምረጣቸው፡፡ አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ የተከፋችው ሱማሊላንድ ቀጣይዋ የግብፆች መናገሻ ልትሆን ትችላለች፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close