Connect with us

Ethiopia

የፈርኦናዊው ሕወሓት አወዳደቅ

Published

on

የፈርኦናዊው ሕወሓት አወዳደቅ | ፀጋው መላኩ

የፈርኦናዊው ሕወሓት አወዳደቅ | ፀጋው መላኩ@DireTube

በቅርቡ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተካሄደው የፖለቲካ ውይይት የበርካታ የሕወሓት አመራሮችን ፊት አሳይቶናል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጥ በብርሃን ፍጥነት እየተምዘገዘገ ቢሆንም በህወሓት በኩል የአንድ ጋት እርምጃ አለመታየቱን የስብሰባው ውይይት ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል፡፡ አቶ ስብሀት ነጋ ቢያልቅባቸውም አልጨረሱም፡፡ የአረና ትግራይ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አምዶም ገብረስላሴ በመቀሌው ምሽግ ላይ ከበድ ከበድ ያለ የሀሳብ የመድፍ ጥይት ወርውሯል፡፡

ሕወሓት የዛሬን አያድረገውና የሚያስርና የሚፈታ፤ የሚተክልና የሚነቅል ከቁመቱ በላይ የገዘፈ የፖለቲካ ድርጅት ነበር፡፡ ሕወሓት የኢትዮጵያን ህዝብ የታገለው በሚያወጣቸው ሕጎች፣ በፖለቲካና በኃይልም ነው፡፡ በዘመነ ህወሓት በተለይ አፋኙ የፀረ ሽብር ህጉ ሥራ ላይ መዋሉን ተከትሎ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶች፣ ብሎገሮች፣ ደራሲያን፣ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የሀይማኖት ሰዎች ሳይቀሩ በገፍ በየእስር ቤቱ መታጎር ግድ ሆኖባቸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀድሞ የጨለመ ቢሆንም የያን ወቅት ደግሞ የበለጠ የድቅድቅ ጨለማው መግቢያ መጀመሪያ ሆነ፡፡ እናም የህወሓት የደህንነት መዋቅሮች በስፋት ተዘረጉ፤ የግለሰብ ስልኮች ሳይቀሩ መጠለፍ ጀመሩ፣ የሳተላይት ቴሌቭዥኖች በማፈኛ ሞገድ መታፈን ግድ ሆነባቸው፡፡ የተለየ ድምፅ የሚያሰሙ ድረገፆች አንድ በአንድ እየተለቀሙ አፈና ተደረገባቸው፡፡ ጋዜጦችና መፅሄቶች ከገበያ ውጪ እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ ጋዜጠኞችም በገፍ ተሰደዱ፡፡

በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የሀገሪቱ ኢምባሲዎች ሳይቀሩ በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን መሰለያና መከታተያ ማዕከል ሆኑ፡፡ በሶማሊላንድ፣ በሱዳን፣ በኬኒያና በአንዳንድ ሀገራት የሚገኙ የፖለቲካ ስደተኞች በአፈና መዋቅሩ እየታሰሱ ታፍነው ሀገር ውስጥ እዲገቡ ተደረገ፡፡

የህወሓት የስለላ ተቋም ዜጎችን ከውጪ ሀገራት አፍኖ ሀገር ውስጥ በማስገባት ዘብጥያ መወርወር እንደሚችል በአንዳራጋቸው ፅጌ በተፈጠረው አፈናም አሳየ፡፡ እናም በሀገሪቱ የሞት ጣረሞት ነገሰ፡፡ መንግስታዊው አሸባሪ ኃይል በጥቁር ጣረሞት ኢትዮጵያ ላይ አጠላ፡፡ ፀጥታና ዝምታም ሰፈነ፡፡

ከዚያ በተቃራኒው የስርዓቱ አቀንቃኞች በዜጎች ሞትና ስደት መሳለቅ ጀመሩ፡፡ ዘረፋውና የኢኮኖሚ አሻጥሩም ተስፋፋ፡፡ ፓርቲው የአባላት ምልመላውን ቢያጧጡፍም፤ አባል እንጂ ደጋፊን ማግኘት የሚችልበት እድል ዜሮ ሆነ፡፡ የፓርቲ አባልነትና የሊግ አባልነት ሳይሰሩ የሚበሉበት የቅምጥ ፖለቲከኞች ማዕድ በመሆኑ፤ በርካቶች በዚህ ማዕድ ዙሪያ ከበው ቁጭ አሉ፡፡

ይህ ሁሉ እየሆነ ግን የነገን ነፃነት አሻግረው የሚያዩ ዜጎች አርፈው የተኙበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ እናም ኢትዮጵያዊያን ፍርሀትን ፈርተው አልተኙም፡፡ ቢያንስ በውጪ ያሉ ኢትዮጵያዊያን የቀደመ ጩኸታቸውን ማሰማታቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ሰልፉ፣ ተቃውሞው፣ በየኢምባሲ በሩ ማንኳኳቱ፣ ለተጎዱ ወገኖች በየአውራ ጎዳናው ሻማ ማብራቱ አልቆመም፡፡ ትግሉ እየጠፋም እየበራም ቀጥሏል፡፡

እንደ ሂውማን ራይተስ ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የዓለም አቀፍ የሰብኣዊ መብት ድርጅት ተሟጋቾችምም ቢሆኑ የህወሓት መራሹን መንግስት የሰብአዊ መብት ረገጣን ማጋለጥ አላቆሙም፡፡ ሀገር ውስጥ መግባት ባይችሉ እንኳን በጎረቤት ሀገራት በማንዣበብ በቂ መረጃን ሰብስበው መደበኛ ሪፖርቶቻውን ያወጡም ነበር፡፡ ሆኖም አሜሪካም ሆነ ሌሎች የምዕራባዊያን ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ የፀነሱት የፀረ ሽብር ዘመቻ እንዳይነጨግፍባቸው በመስጋት የሆነውን ሁሉ እንዳላዩ አይቶ ማለፉን መረጡት፡፡

እናም አሜሪካዊያን ዜጎች ከሽብር ሥጋት ነፃ ይሆኑ ዘንድ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው አፋኝ ኃይል መሸበር ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ተሸበሩ፣ ተጨነቁ፣ አለቀሱ፣ ተሰደዱ፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ልጆች መፍትሄው ከምዕራባዊያን ሳይሆን ከመዳፋቸው ሥር መሆኑን በተረዱበት ዕለት፤ የነፃነታቸው ጎህ ተስፋ እውን የሚሆንበት መንገድ አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡

ይህንን እውነታ በተረዱበት ቅፅበት ግን እጣ ፈንታቸውን በእጃቸው ለመወሰን ቆርጠው ተነሱ፡፡ እጃቸውንም በማጣመር ጭቆና እና አፈና በቃ አሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ አፋኙ ኃይል የበለጠ እንደሚያፍን፣የበለጠ እንደሚገል፣ የበለጠ እንደሚጨክንም ያውቁ ነበር፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ትግሉ በአፈናም ውስጥ ሆኖ መቀጠል ነበረበት፡፡
እናም ቀጠለ፡፡

“ ትግሉን ላንጨርሰው አልጀመርነውም” ያለው የወጣት ኃይል፤ በጨካኞች ላይ ጨቀከነ፡፡ የተፈራው አለቀረምና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ለማሰማት የወጡ ወጣቶች አነጣጥሮ በሚተኩሰው ኃይል ነፍሳቸው ተበላ፡፡ አካላቸውም ጎደለ፡፡ በገፍ ተግዘውም በበርሃ ተወረወሩ፡፡ ነገር ግን ደምን ደም እያፈላው፣ ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ ሄደ፡፡

አሁን አሜሪካ፣ ጣሊያን ፈረንሳይ፣ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ም.ን.ት.ስ.ዮ ምናምን የሚባል ነገር የለም፡፡ ….. አይሰራምም፡፡

መደበኛው የጨዋታ ጊዜ በማለቁ በቀረችው ጥቂት ደቂቃ ነጥብ ይዞ መውጣት ግድ ይላል፡፡

በየፈረንጁ አደባባይ እየዞሩ ማለቃቀስ በቃ፡፡ ለራስ ነፃነት ማንንም መለማመጥ አያሻም፡፡ እናም አሁን የመነጋገሪያ ቋንቋው ሌላ ሆኗል፡፡ ቋንቋው ገዢዎች የሚገባቸው አግባባዊ ቋንቋ ነው፡፡
ህዝባዊ ማዕበል ይባላል…….፡፡

ይህ የተቃውሞ የነውጥ ርዕደ መሬት ነው፡፡ ይህ ቋንቋ የገዢዎችን ልብ እያሸበረ ልባቸው ጎሮሯቸው ስር እንዲወተፍ ያደረገ ምድር አንቀጥቅጥ ህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ነው፡፡ እናም ይህ ህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ነውጥን ፈጠረ፡፡ የነውጡ የርዕደ መሬት ልኬት የህወሓትን የ27 ዓመት የንግስና ዙፋን ሰነጣጠቀው፡፡

ገዢዎች አንዲት ጋት ነፃነትህን በነጠቁህ ቁጥር፤ ተጨማሪ ነፃነቶችህን የሚነጥቁህ ቀድሞ በነጠቁህ ነፃነት ላይ ቆመው በመረማመድ ነው፡፡

በመሆኑም የተገፈፈው ነፃነትህ የመጨረሻው የነፃነት አፈና ጥግ ላይ ሲደርስ ለአንተ ሞትም ህይወትም ልዩነት አይኖራቸውም፡፡ እናም የሞትና ህይወትን ድንበር ላጠፋ ጥይት፣ እስር፣ ድብደባ፣ ግድያ ምኑ ነው? በሞት ላይ የጨከነ ትውልድ ለጨቋኙም አይራራም፡፡ እናም ደግሞ አልራራም፡፡

በጊዜው ህወሓት ያልተረዳው እውነታ ቢኖር ይህንን ነበር፡፡ ሞትም ህይወትም አንድ ለሆነበት ህዝብ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መጣል ትርጉም አልነበረውም፡፡ ግን ህወሓት የትግሉ ጥልቀትና ስፋት ደመናው ሊያስከትለው የሚችለው ዶፍ ዝናብና ጎርፉን በሚገባ ባለመረዳቱ በድሮ በሬ ማረሱን ቀጠለበት፡፡

ያም ሆኖ ከአንድም ሁለት ጊዜ የተጣለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወረቀት ሳያልፍ ቀረ፡፡ ዛቻው ማስጠንቀቂያው፣ ግድያው እስሩ፣ ማሸበሩ ሞትና ህይወትን አንድ አድርጎ ለሚያይ ህዝብ ትርጉም አጣ፡፡

እናም ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በጭንቅ ጥብ ስብሰባ መታመስ ግድ ሆነበት፡፡ ግን እዚህም ጋር ጠብ የሚል አንዳች ነገር ጠፋ፡፡
ገዢዎች ህዝብን ያሸበሩትን ያህል፤ እነሱ መሸበር ጀመሩ፡፡ ህዝብን ያስጨነቁትን ያህል እነሱ መጨነቅ ጀመሩ፡፡ እነሱ ሲጨነቁና ሲጠበቡ ታጋዩ ህዝብ ከፈሰሰው የወገኑ ደም ባሻገር የነፃነትን ጎህ ማየት ጀመረ፡፡

የተስፋ ጭላንጭል፡፡…. ተስፋ…..!
ጥቂት ተስፋ…!፡፡ ተስፋዋን ማስፋት ደግሞ ግን ግድ ይላል፡፡

እናም ትግሉ ቀጠለ፡፡ የገዢዎች የተፈሪነት ግርማ ሞገስ ተገፏል፡፡ የፓርቲ የሚስጥር ካዝና ሳይቀር ተዘርግፎ የድብቅ ጨዋታዋች የአደባባይ ፀሀይ ይሞቃቸው ገብቷል፡፡ በከፍተኛ አመራሮች መካከል እዚህም እዚያም መዝርክረኮችና እርስ በእርስ መካሰሶች መታየት ጀምረዋል፡፡ በዚህም ወቅት ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ በአጥንቱ ቆሞ ብቻውን ማውራት ጀመሯል፡፡

የዛሬ 27 ዓመት እንደቀልድ አራት ኪሎ ላይ ወድቃ የተገኘችው ሥልጣን ፤ አሁን እንደቀልድ ከእጅ እየወጣች ነው፡፡ ነገርየው ሥልጣን የመምለጡ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ከስልጣን መልቀቅ ጀርባ ያለው ውጥንቅጥም አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህች ውጥንቅጥ ደግሞ የ27 ዓመቷ ዶሴ ናት፡፡

ከ27 ዓመቷ ጥቁር መጋረጃ ጀርባ ግድያው፣ ዘረፋው፣ መድሎው፣ ሀገራዊ ጥፋቱ፣ … እረ ስንቱ…!
የታሪኩ ማጠናቀቂያም እየደረሰ ስለሆነ ህልም የመሰለው ታሪክ እውን ሆኖ መታየቱ አይቀሬ ሆኗል፡፡ ባለቤቱ ቤቱን እንደሚያስለቀቀቀው ተከራይ የአዲስ አበባው እቃ መሸከፍም ግድ ብሏል፡፡

ይህንን ተከትሎም የ27 ዓመቱ የፖለቲካ ቲአትር መቋጨቱም አይቀሬ ሆነ፡፡ እናም በደደቢት በርሀ ተጀምሮ በአራትኪሎ የሚንልክ ቤተ መንግስት የታሪኩ ጡዘት ላይ የደረሰው የህወሓት የፖለቲካ ድርሰት በመቀሌው ሽሽት ተጠናቀቀ፡፡ በኮሎኔል መንግስቱ የሀራሬ ሽሽት ሲሳለቁ የነበሩት ህውሓቶች እነሱ በተራቸው ነቅለው መቀሌ ሸሹ፡፡ “አትፍረድ ይፈረድብሃል ይሏል” ይህ ነው፡፡
ምን አልባት ከዚህ በኋላ የህወሓትን ቅፅ ሁለት ታሪክ የሚያስነብበን ካገኘን “ሕወሓት ከመቀሌው ምሽግ በኋላ……” የሚል ይሆናል፡፡

ቻው…ቻው………ሸገር….! ቻው.. አዲስ አበባ…..!
በአደባባዮችሽ የታፈሩብሽና የተከበሩብሽ ፈርዖኖች አፈር ሆነዋል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close