Connect with us

Ethiopia

የአምዶም ዓይነቱን ወለጋም ጎንደርም ሐዋሳም ካበዛልን …

Published

on

የአምዶም ዓይነቱን ወለጋም ጎንደርም ሐዋሳም ካበዛልን ...

የትክክለኛ ትግራዋይ ባህሪ አምዶም ገብረስላሴ ዘንድ ያየነው ለእውነት የመቆምና ስለ ሀቅ መሞት ነው፡፡ አደባባይ ላይ በጥይት ታስቆም የነበረችው ህወሃት አዳራሽ ውስጥ በጭብጨባ መታገል ጀምራለች፡፡

የአምዶም ዓይነቱን ወለጋም ጎንደርም ሐዋሳም ካበዛልን፤ ኢትዮጵያ የተተኪው ትውልድ ትሆናለች፡፡ *** ከስናፍቅሽ አዲስ

አቶ በረከት ስምዖንን አማናቸው እንጂ ሁላችንም መቀሌ ነው የከረምነው፡፡ አንዴ ድምጸ ወያነ አንዴ ደግሞ ትግራይ ቲቪን ቀያይረን እያየን የመቀሌ ዩኒቨርሲቲውን ፓናል አብረን ታድመንበታል፡፡ ብዙ ችግር የታየበት መድረክ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይልቁንም አቦይ ስብሐት ራሳቸው የፈረሰው ኢህአዴግ ሲሉ ያደመጥኩበት ኩነት ነው፡፡

አቶ በረከት ካነሷቸው ብዙ ሀሳቦች ብዙው እንዳለፉት ሃያ አምስት አመታት ሰውን የሚያበሳጭ ቢሆንም አሁን ላለው መንግስት የጠቆሟቸው የቢሆን ሀሳቦች ግን የሚናቁ አይደሉም፡፡ በሌላ በኩል ከአቶ ሃይለማርያም ወዲህ የተፈጠረ ችግር እንደሆነ ለማሳየት የሞከሩበትንና የአቶ መለስን ቅድስና ደጋግመው የገለጹበትን አግባብ አቦይ ስብሐት ቁጣ ባዘለ ድምጽ በዘጠና ሰባትስ ጦርነት አልነበረም፤ ችግር አልነበረም ብለው ችግሩ የመለስ ብቃት ሲመክተው የኖረ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

የጀኔራል አበበ እና የአንድ ስማቸውን የዘነጋሁት ሰው ሀሳብ ልቆ የያየሁት ሀሳቦችን የያዘ መልካም አስተያየት ነበር፡፡ በተቃራኒው በተቃዋሚ ስም ዛሬም ከዚህ ሁሉ ቅሌት በኋላ ነውር ሳይጠሉ መቀሌ የገቡ አንዳንዶች አሁንም ተቃዋሚ ነን ብለው አደባባይ መታየታቸው ህወሃትማ አይን አፋር ነው እንድልን አድርጎናል፡፡

መድረኩን የነገሰበት አምዶም ነው፡፡ አምዶም አራቱም የኢትዮጵያ ጥግ ተቀባይነት ያለውና የሚከበር ሀሳብ አንስቷል፡፡ የእውነተኛ የትግራይ ሰው ባህሪ የአምዶም ይመስለኛል፡፡ የትግራይ ሰው ውሸትን ይታገላታል፡፡ እውነትን ይጋፈጣታል፡፡ ለሀቅ ይቆማል፡፡ ከዚያ የመጣውን ለመቀበል ዝግጁ ነው፡፡ በራሴ ባሉት ሰው የራሳቸውን ሰው የማይመስሉ መሆናቸው ሲነገራቸው ሀሳቡን ማስጨረስ አልቻሉም፡፡ እንደ አምዶም ያሉ ሰዎች ባህር ዳርና ጎንደር ያስፈልጉናል፡፡ ይህ ሀሳብ የወለጋና የጅማ ልጆች ሀሳብ መሆን አለበት፡፡ ሀሳዋሳና ወላይታም ቢሆን ወገናቸው እውነት የሆነ ወጣቶች ያስፈልጓቸዋል፡፡ እናም አምዶም ህወሃት ከስልጣን ከመባረሯ ውጪ ለደሃው ትግራይ አበሳ ሊሆን የሚችል አደጋ ኢትዮጵያ ውስጥ አለመኖሩን በአደባባይ ሲናገር መድረኩ ተርበደበደ፡፡ ድሮ ድሮ ሀሳብን እንዲህ እገልጻለሁ ብሎ የወጣ ሰው በጥይት ይቆላ ነበር፡፡

ህወሃት ሀሳብ ትፈራለች፡፡ ልዩ ሃሳብ ያነሱ ሰዎች ዛሬ የት ናቸው? ግደይ ለምን ተባረረ? አረጋዊ በርሄ ለምን ትግራይን ለቆ ወጣ? እነ ስዬ እስር ቤት ምን ወረወራቸው? ሀሳብን ማድመጥ ልዩነትን መስማት ቡድናዊ ደባውን የሚበጣጥስ ማየት የማይፈልግ ፓርቲ ስለሆነ ያኔ ጠመንጃ ስላለው ገድሏል አፍኗል፡፡ ዛሬ ደግሞ አቅም አልባ ነው፡፡ አዳራሽ ውስጥ በጭብጨባ ሀገር የሚገነባ ሀሳብ ያስቆማል፡፡ አዳራሹ ውስጥ ጀሌዎችን እያንጫጫ በቅዱስ ሀሳብ ያላግጣል፡፡

አምዶም ምድረ በዳውን ለማቅናት ጥራጊውን አቅኑ ብሎ የወጣ የበርሃ እረኛ ነው፡፡ ወጣት ነው፡፡ እውነትን ፊት ለፊት የተጋፈጠ ጀግና ነው፡፡ አባቶቹን ይመስላል፡፡

የአምዶም አባት መለስ ሳይሆን አሉላ አባ ነጋ ነው፡፡

የአምዶም አባት አቦይ ስብሐት ሳይሆኑ ዐፄ ዩሐንስ ናቸው፡፡

አምዶም እስረኛ ፊት የምትሸና ገበና የለሽ እናት ሳትሆን ደሃዋ ኢትዮጵያዊት ትግራይ የወለደችው ነው፡፡ የአምዶም ዓይነቱ ቁጥሩ ብዙ ነው፡፡

አንዳንዱ እንዳይናገር ዛሬም ባልተለወጠ ዛሬም በሚያፍን ዛሬም በጭብጨባ ሳይቀር ተናገር ብሎ የጋበዘውን ሰው እንዳይናገር በሚከለክል አፋኝ ክልል የሚኖሩ በመሆናቸው ይሄንን እድል አላገኙም፡፡

ትናንት ብዙ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ወጣቶች የህወሃት አቃጣሪዎች ይመስሉን ነበር፡፡ ዛሬ ጥቂት መቶ ሺ የትግራይ ወጣቶች የህወሃት አቃጣሪ የሚመስሉን ነጻነት እስኪመጣ ነው፡፡ የአምዶም ሀሳቦች በሙሉ በመቀሌ ባይሰሙ የሚመረጡ ነበሩ፡፡

ህወሃት አዲስ አበባ ያለችውን ሀዋሳ ያወራችውን ባህር ዳር የደጋገመችውን መቀሌ ሲሰማ መስማቱ አብግኖታል፡፡ ግን ይሄ ገና በአዲግራት መነጋገሪያ ይሆናል፡፡ የአክሱም ወጣቶች አንድ ቀን ሌቦች አይደለንም ሌባም ወንድም የለንም ብለው ሰልፍ ይወጣሉ፡፡

ማይጨው እኛ የኢትዮጵያ ታላላቅ ጀግኖች የወለዱን እንጂ ኢትዮጵያን ለመጉዳት ምሽግ የምንሆን አይደለንም ብለው ይናገራሉ፡፡ የህወሃት ምሽግ ይፈርሳል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close