Connect with us

Ethiopia

ወ/ሮ ሙፍሪያት ያለቀሱበት ምስጢር ምንድን ነው?

Published

on

ወ/ሮ ሙፍሪያት ያለቀሱበት ምስጢር ምንድን ነው? | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ወ/ሮ ሙፍሪያት ያለቀሱበት ምስጢር ምንድን ነው? | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን@DireTube

እምባ ሐዘንን አለያም ተስፋ መቁረጥን የሚያሳይ የስሜት መግለጫ ነው፡፡ የእኛ መሪዎችም በተለያየ ጊዜ ሲያለቅሱ አይተናቸዋል፡፡  ማልቀሳቸው በማኅበረሰቡ ላይ የሚኖረው አወንታዊና አሉታዊ ሚና መኖሩ አይቀርም፡፡

ከመሪዎቻችን ለመጨረሻ ጊዜ ያለቀሱት የሠላም ሚኒስትሯ ሙፍሪያት ካሚል ናቸው፡፡ አቶ ካሳ ተ/ብርሃንም አልቅሰዋል፡፡ የሁለቱም የእምባ መድረክ መቐለ ነች፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ደግሞ የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሰሞን እምባ ባይወጣቸውም ሲተናነቃቸው ታይተዋል፡፡

ጠቅላይሚኒስትር ዓቢይ ባያለቅሱም፣ ፊታቸው ሲያዝን ተስፋ አስቆራጭ ንግግር ሲናገሩና ስለ ሞት ደጋግመው ሲያወሩ ተደምጠዋል፡፡
እዚህ ጋር ነው ጥያቄው፡፡ በርግጥ መሪዎቻችን የሚያለቅሱት፣ አስለቃሹን ጉዳይ መፍትሔ መስጠት ባለመቻላቸው ነው ወይስ ለእኛ ለሕዝባቸው አዝነውልን የሚለው ቀልብ ይስባል፡፡

President Barack Obama wipes away tears as he delivers his farewell address at McCormick Place in Chicago, Jan. 10, 2017. (Doug Mills/The New York Times)

በመሠረቱ ፈረንጅ መሪዎችም ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አንድ ጊዜ ሳንዲ ሁክ በተባለ ት/ቤት ውስጥ ሕፃናት ተገድለው ሲያለቅሱ ታይተዋል፡፡ የያኔውን እምባቸውን የተመለከቱ የአሜሪካ መገናኛብዙሃንም ‹‹ኦባማ የጦር መሣሪያን የሚቆጣጠር ሕግ እንዲወጣ በእምባው እየተማጸነ ነው›› ሲሉ ዘግበዋል፡፡

ባራክ ኦባማና ፓርቲያቸው ዴሞክራት የጦር መሣሪያ ቁጥጥር የሚያደርግ ሕግ እንዲወጣ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ ዋነኛ የጦር መሣሪያ ነጋዴዎቹ ሪፐብሊካን ይህ ሕግ እንዳይወጣ ይቀሰቅሳሉ፡፡ በዚህ መሀል ሕገ-ወጥ ጠብመንጃ በታጠቁ ሰዎች ንጹሃን ተገደሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ የሳንዲ ሁክ ት/ቤት ሕፃናት ናቸው፡፡ ባራክ ኦባማም ‹‹እስኪ አሁን እንኳ ይህንን አይታችሁ የጦር መሣሪያ መቆጣጠሪያ ሕግ እናውጣ›› ለማለት አለቀሱ፡፡

የዚህ መልዕከቱ የአሜሪካ መሪዎች የሚያለቅሱት ፖሊሲ ለማውጣት ነው የሚል ነው፡፡ የእኛ መሪዎች እምባ ግን ግቡ ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አቶ ካሳ ተ/ብርሃን ከአንድ ዓመት በፊት መቐለ ላይ በተካሄደ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች የሠላም ጉባኤ ላይ ስቅስቅ ብለው አለቀሱ፡፡ እኒህ ሰው በወቅቱ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው ሳለ፣ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ መስጠት የሚያስችል ሥልጣን እያላቸው፣ በቀጣይም ችግሩ እንዳይደገም ለማድረግ የሚያስችል መፍትሔ እያላቸው አለቀሱ፡፡ ታዲያ ሕዝብ ምንን ተስፋ ያድርግ?…ለችግራችን መፍትሄ ይሰጠናል ብሎ የሚያስብ ሕዝብስ መሪዎቹ እንደሱ ቁጭ ብለው ሲያለቅሱ ሲመለከት ምን ሊል ነው?…

የሙፍሪያት ካሚል እምባም ተመሳሳይ ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ወ/ሮ ሙፍሪያት በአሁኑ ሰዓት የተፈጠሩ እና እየተፈጠሩ ያሉ የሠላም እጦቶችን ለማስተካከል በሚል የተሾሙ ሚኒስትር ናቸው፡፡ ይህንን እንዲያደርጉም ፌደራል ፖሊስም፣ ደኅንነትም…በእርሳቸው ሥር ተደርጎላቸዋል፡፡ ሕግ አስከብረው፣ ሰዎችን ከመፈናቀልና ከሞት ያድናሉ ተብለው ሲጠበቅ ጭራሽ ከተፈናቀለውና ከሞተበት እኩል አለቀሱ፡፡

በርግጥ እምባ በእኛ ትዕዛዝ የማይመጣ፣ ተፈጥሯዊ ስሜት ነው፡፡ ለምን አለቀሱ ብሎ መወንጀል ነውር ሊሆን ይችላል፡፡ መሪ ግን ተስፋ ሲሰጥና ችግሮች የሚፈቱበትን መላ ሲዘይድ እንጂ፣ ታንክና ባንክ ያለው መንግሥት ከሕዝብ እኩል ድንኳን ጥሎ ሐዘን መቀመጥ የለበትም፡፡ ሰው እኮ ተስፋ የሚያደርገው መሪውን ነው፡፡ መሪው ተስፋ ቆርጦ ሲያለቅስ ሕዝብ እጣፈንታውን መወሰን የማይችል መናኛ ይሆናል፡፡

በርግጥ በባሕላችን የሚያለቅስ ሰው ይታዘንለታል፡፡ ሕፃን ልጅ እንኳ ከረሜላ እንድገዛልህ ተብሎ የሚለመነው እንዳያለቅስ ነው፡፡ ትልቅ ሰው ሲያለቅስ ደግሞ በጣም እናዝናለን፡፡ የወ/ሮ ሙፍሪያት እምባም ልባችንን ነክቶት ይሆናል፡፡ እርሳቸው ግን የችግሩንም መፍትሔ አውቀውት፣ ምንጩንም ለይተውት ሲያበቁ፣ ከሕዝብ ፊት ቀርበው‹‹ሕዝቡን ያጣለነው እኛ ነን›› ብለው እራሳቸውንና መንግሥታቸውን ኮንነው አለቀሱ፡፡ ደኅንነቱንም ፖሊሱንም የሚያዙት ሚኒስትር ሲያለቅሱ ተራው ሕዝብ ምን ተስፋ አድርጎ ሊረጋጋ ይችላል?…

በርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ሲያለቅሱ ታይተው አይታወቁም፡፡ የሰኔ 16ቱ ቦንብ ፍንዳታ ዕለት እንኳ እንደዚያ ሲያደርጉ አልታዩም፡፡ ምንም እንኳ ባልተጣራ መረጃ ላይ ተመስርተው የተቻኮለ መግለጫ ቢሰጡም፣ ፊታቸው ተክዞና ተበሳጭቶ ቢታዩም ‹‹መግደል መሸነፍ ነው›› ከሚል ቃል ውጭ ዓይናቸው ሲያነባ አልታየም፡፡

ይሁን እንጂ ደጋግመው ስለሞት አውርተው በማውራት ይታወቃሉ፡፡ አቶ ኢሳያስን በጋበዙበት የሚሊኒየም አዳራሽ ፕሮግራም ላይ ‹‹እኔ ብሞትም ሚሊዮን ዓብዮች አሉን›› ብለው ተናገሩ፡፡ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ሰብስበው ‹‹ከብዙ ሞቶች አምልጫለሁ፤እኔን ማንም አይገድለኝም››አሉ፡፡ አሜሪካ ሄደው፣‹‹እኔ ቢያንስ መሸታ ቤት አልሞትም›› ብለው ሲናገሩም በቴሌቭዥን ታዩ፡፡ ሰሞኑን በቤተመንግሥት በተካሄደ ‹‹የኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት›› በሚል መድረክ ላይም በተመሳሳይ ሞትን ከእርሳቸው ጋር አገናኝተው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህ በእውነቱ ሌላኛው ተስፋ አስቆራጭ ነገር ይመስለኛል፡፡

መንግሥቱ ኃይለማርያም

ብዙ ጠላቶች እንዳሏቸው የሚነገርላቸው መንግሥቱ ኃይለማርያም እንኳ ይህንን ያህል ሞትን ፈርተው ሲናገሩ አልተደመጡም፡፡ ከኢሕአፓና ሻዕቢያ የጥይት ውርጅቢኝ (ከግድያ ሙከራ) ያመለጡት ኮሎኔል መንግሥቱ እንኳ ‹‹ትንሽ ሙሃይቴን መቱኝ እንጂ በጣም ደህና ነኝ›› ብለው ነበር ሕዝቡን ያረጋጉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ግን ስለሞት የሚናገሯቸው ነገሮች በሙሉ ተስፋ የሚሰጡ አይደሉም፡፡ እርሳቸው በስንት ኮማንዶና ወታደር

እየተጠበቁ፣ በሰው እጅ መሞትን እንዲህ ከፈሩ፤ እኛ መንግሥትን አምነን የምንኖር ሰዎች እንዴት ነው ተስፋ የሚኖረን?

እዚህ ላይ ደግሞ የሚኒስትሮቹ (በተለይም የሠላም ሚኒስትር) እምባ ሲጨመርበት የበለጠ ሕዝብን ተስፋየለሽ ያደርጋል፡፡ ግን ማልቀስ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ አቶ ካሳም ሆኑ ወ/ሮ ሙፍሪያት ቢያለቅሱ ሰውኛ ባሕሪያቸው ተጭኗቸው መሆኑ አይካድም፡፡ እምባቸው በማኅበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው አሉታዊ ተጽእኖ ግን ሊታሰብበት ይገባል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close