Connect with us

Ethiopia

የህወሓት ሁለት ቀሪ ሀብቶች

Published

on

የህወሓት ሁለት ቀሪ ሀብቶች | ከፀጋው መላኩ

ህወሓት ሁለት ወሳኝ የፖለቲካ ሀብቶች አሉኝ ብሎ ያስባል፡፡ የመጀመሪያው የትግራይ ህዝብ ሲሆን ሁለተኛው የቅራኔ ፖለቲካ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንደኛውን የፖለቲካ ሀብት ተነጥቆ በሁለተኛው የፖለቲካ ሀብቱ ላይ ወሳኝ ትግል እያካሄደ ይገኛል፡፡

የመጀመሪያው ሀብቱ የሆነው የቅራኔ ፖለቲካ ህወሓት የፖለቲካ የዘር ሀረጉ ከሚመዘዝበት ኮሚኒስታዊ እሳቤው የመነጨ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በኮሚኒስታዊ ፈላስፎች እሳቤ መሰረት በማህበረሰብ ውስጥ እርስ በእርሳቸው የሚፃረሩ ኃይሎች የመኖራቸው ጉዳይ የተፈጥሮ እውነታ ነው፡፡ በእነዚህ ተፃራሪ ኃይሎች መካከል ደግሞ ምንጊዜም ተቃርኖ አለ፡፡ ተቃርኖውም የፖለቲካ ትግሉ ማዕከላዊ ነጥብ ሆኖ ያገለግላል፡፡

በማርክስ አሰተሳሰብ የተቃኙት የሌኒን፣የማኦ እና የስታሊን ፖለቲካዊ እሳቤዎች በዚህ አይነቱ የቅራኔ ፖለቲካ ምሶሶ ላይ የቆሙ ናቸው፡፡ እናም ተቃርኖ ከሌለ የፖለቲካ ጨዋታው ስለሚያበቃ ማርኪስዝም፣ ሌኒንዝም፣ ማኦኢዝም የሚባል የፖለቲካ አስተምህሮ ያከትምለታል፡፡ በመሆኑም ኮሚኒስቶች የተቃርኖ ፖለቲካን የሚታረቅና የማይታረቅ በማለት በሁለት ይከፍሉታል፡፡

የሚታረቅ ቅራኔ ሲሉ ጥልቀት የሌለው ተቃርኖ ሆኖ በውይይትና በድርድር ሊፈታ የሚችል ማለታቸው ሲሆን የማይታረቅ ተቃርኖ ሊፈታ የሚችለው ግን በማሸነፍ እና በመሸናነፍ ብቻ ነው፡፡ በኮሚኒስቶች የፖለቲካ ዶክትሪን መሰረት የፖለቲካ ድርጅት ከሆንክ በህይወት ለመኖር የምትታገለው ደመኛ ጠላት ሊኖርህ ይገባል፡፡ የሚፈረጅ ጠላት ከሌለ ትግል፣ ፖለቲካ፣ ርዕዮተ ዓለም፣ መታገል፣ ማታገል የሚባሉ ነገሮች የሉም፤ አይኖሩምም፡፡ ለዚህ የሚሆን ጠላት ከሌለህ ደግሞ በራስጌም በግርጌም ብለህ አንድ ጠላት መፈጠር አለብህ፡፡ ማርክሲስት ሌኒንስትነት ያለተቃርኖ በህይወት ሊኖር የማይችል ፖለቲካ ነው፡፡

እናም በኮሚኒስታዊው የፖለቲካ ጨዋታ የግድ ነገሮችን በመደብ ከፍለህ ማህበረሰቡን በበዳይና ተበዳይ ጎራ በመለየት ራስህን የተበዳዩ ጠበቃ አድርገህ በማቆም ድምፅህን ከፍ አድርገህ እያሰማህ ፖለቲካኽን ታስኬደዋለህ፡፡

ለፈጠርካቸው ጠላቶችህም፤ ቡርዣው ፣ ንዑስ ቡርዣው ፣ ከበርቴው፣ ፊውዳሉ፣ ባላበቱ፣ ቀልባሹ፣ አድሃሪው፣ አቀባባዩ ወ.ዘ.ተ እያልክ የህዝቡን ጠላት ታበዛውና ቆምኩለት በምትለው ማህበረሰብ ዘንድ የፍርሀት ጡዘቱን ታንረዋለህ፡፡

ከዚያም በሌላ አቅጣጫ ደግሞ አርሶ አደሩ፣ ላብ አደሩ፣ ወዝ አደሩ፣ ጭሰኛው እያልክ ደግሞ ከኢኮኖሚውና ከፖለቲካው የተገለለውን የህብረተሰብ ክፍል የብሶተኝነት ስሜት በመኮርኮር ለጨዋታህ የምትመች ቅራኔን ትፈጥራለህ፡፡ ቅራኔዋ ይበልጥ አድጋ በህብረተሰቡ መካከል ክፍተት መፍጠር ስትጀምር ደግሞ ራስህን የተበዳዩ የህብረተሰብ ክፍል ጠበቃ አድርገህ በማቆም የትግሉ ፍታውራሪ ሆነህ የፖለቲካው ዘፋኙም ተቀባዩም ያው አንተ ብቻ ሆነህ ታርፈዋለህ፡፡

“በአንድ ልቦለድ የታሪክ አወቃቀር ውስጥ ግጭት ወይንም ኮንፍሊክት ከሌለ ታሪክ የለም” እንደሚባለው በሌኒንስታዊ አስተሳብህም ቅራኔዋ ከሌለች የአንተም ፖለቲካ ሊኖር አይችልም፡፡ እናም በዚህ እሳቤ መሰረት የቅራኔዋን የፖለቲካ ከሰል እያራገቡ እሳቱን ማቀጣጠል የፓርቲ ህልውና ጉዳይ ነው፡፡

ህወሓትም በቀደመው የትግራይ ማርክሲስት ሌኒንስት ወይንም ማሌሊት አስተሳሰቡ ይህች የቅራኔ ፖለቲካ በሚገባ ተክኖባታል፡፡ የቀድሞው ህወሓት መራሹ ኢህአዴግም ቢሆን ይህችን የቆየች ዘመን ያለፈባት የፖለቲካ ካርድ ይዞ በቅራኔ ፖለቲካ ጨዋታ እድሜውን ሲገፋ ቆይቷል፡፡ ነፍጠኛው ፣ትምክህተኛው፣ ጠባቡ፣ ኒኦሊብራሉ የሚሉት ፍረጃዎችና የፖለቲካ ብሂሎች ከዚሁ ከድርጅቱ ኮሚኒስታዊ ባህሪ የመነጩ ናቸው፡፡

እናም ህወሓት በተካናት የቅራኔ ፖለቲካ በተለይ ትምክህተኛና ጠባብ ብሎ በፈረጃቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል በተፈጠረው የተካረረ ቅራኔ የፖለቲካ የኃይል ሚዛኑን ለሶስት አስርት ዓመታት ያህል አስጠብቆ ማስኬድ ችሏል፡፡ ሆኖም የቅራኔ ፖለቲካው ሴራ ዘግይቶም ቢሆን የገባቸው የቀድሞው የፖለቲካ አጋሮቹ፤ በተለይ በኦሮሞና በአማራ መካከል ምንም አይነት ቅራኔ እንደሌለ በማሳየት የትግሉን አቅጣጫ ከቅራኔ ፖለቲካ መስመር ማውጣታቸው የህወሓትን የቅራኔ ፖለቲካ የበርሊን ግንብ ንዶታል፡፡

እናም ህወሓት እንደኮሚስት ፓርቲነቱ በቅራኔ ፖለቲካ ውስጥ ራሱን ፈጥሮና አሳድጎ ሲኖር የህልውናው ቀጣይነትም ከቅራኔ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በኦሮማራ የትግል ስልት የቅራኔ ፖለቲካው ስስ ብልት ሲመታ በስልታዊ ማፈግፈግ ከመሀል ሀገር ጠቅልሎ ትግራይ የገባው ህወሓት፤ አሁን የቀረው ብቸኛ የፖለቲካ ካርድና የመጫዋቻ ሜዳ የትግራይ ህዝብና የትግራይ ምድር ናት፡፡

የህወሓት አመራሮች የትግራይን ህዝብ እንደ ምሽግም እንደ ደጀንም፣ እንደ ሰብአዊ ጋሻም እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ አሁን ባለው የህወሓት አካሄድ የፖለቲካው አቅጣጫ በነበረበት የመርገጥ አዝማሚያ ስለሚታይበት በትግራይ ህዝብ ውስጥ የተፍታታ የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚፈጠርበት ሁኔታ ከሌላ በስተቀር ሁኔታዎች ይበልጥ እየተውሳሰቡ ይሄዳሉ፡፡

የተፍታታ አስተሳሰብ ሲባል ነገሮችን አሁን ካሉበት ወቅታዊ ፖለቲካ በላይ አርቆ ማሰብ፣ ፖለቲካውን በደረቅ የሂሳብ ስሌት ብቻ አለማየት፣ ካሉበት የሥጋት ቆፈን መላቀቅና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ባለፉት ዓመታት የነበረውንና አሁን ያለው ሀገራዊ ፖለቲካ ብቻ ታሳቢ አድርጎ መንቀሳቀስ የነገውን አካሄድ የሚያበላሸው ይሆናል፡፡ የትናንቱን ሀገራዊ ብልሽትና የዛሬውን ችግር ተገንዝቦ ስለነገው መፍትሄ ማሰብ እንጂ፤ በትናንት ችግር ላይ ቆሞ መቆዘም የትግራይን ህዝብ ቀጣይ ፖለቲካዊ አካሄድ አንድ ጋት ወደፊት ሊያስኬደው የሚችል አይደለም፡፡

ሁለተኛው በትግራይ መምጣት ያለበት ለውጥ ነገሮችን ከፓርቲ ቁመና በላይ መመልከት ነው፡፡ ይህች ህወሓት የማይፈልጋት ጎምዛዛ ሀቅ ናት፡፡ በአሁኑ ሰዓት በትግራይ አድራጊ ፈጣሪ የሆነው የክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት ነው፡፡ ህወሓት ደግሞ የፖለቲካ ድርጅት ነው፡፡ እንደ ማንኛውም በሰው የተፈጠረ ድርጅት ህወሓት መጀመሪያ ነበረው፤ መጨረሻም ይኖረዋል፡፡ የራሱ የፖለቲካ ፕሮግራምና አላማን አግንቦ የሚንቀሳቀስ አንድ ክልላዊ ፓርቲ ነው፡፡ ህወሓት ከትግራይ ህዝብ ተገኘ እንጂ፤ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አልተገኘም፡፡ የትግራይ ህዝብ ጥንታዊነት ከህወሓት አርባና እና ሀምሳ ዓመት የጎልማሳነት እድሜ በእጅጉ የራቀ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ የአስተሳሰብ ብዝሀነት ያለው ሲሆን፤ ሕወሓት እንደ ፓርቲ የፖለቲካ አስተሳሰቡ የሚቀዳው ከፖለቲካ ፕሮግራሙና ከርዕዮት ዓለሙ ብቻ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ የአንድ ህዝብ የአስተሳሰብ ብዝሃነትም ሆነ የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብ በርዕዮትና በፕሮግራም መታጠር ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ነገር ግን ስህተቱ የሚፈጠረው የአንድ ፓርቲ ፕሮግራምና አላማ የአንድ ህዝብ አስተሳሰብ ሙሉ ውክልና ያለው አድርጎ ማሰቡ ላይ ነው፡፡

ይህ ማለት አንድን ህዝብ በፓርቲ የፖለቲካ ፕሮግራም ቁመና ልክ ዝቅ ብሎ እንዲያስብ መፈለግ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነቱ አካሄድ ራስን የሁሉም ህዝብ ብቸኛ ተጠሪና ተወካይ አድርጎ የማሰብ የጠቅላይ አስተሳሰብ አባዜ ሲሆን በውጤቱም የተለያዩ ተፈጥሯዊ የአስተሳሰብ ፀጋዎችን በአንድ ቅርጫት ውሰጥ ገብተው እንዲጨመቁ ማድረግ ነው፡፡

ህወሓት ፈፅሞ ሊሰማው የማይፈልገውም ጥሬ ሀቅ ቢኖር በትግራይ ምድር ውስጥ ከብዙዎቹ አንዱ ተደርጎ ሊቆጠር የሚገባው መሆኑን ነው፡፡ ራሱን ብቸኛ የስለት ልጅ አድርጎ ማሰቡ በክልሉ ያለውን የፖለቲካ ከባቢ አየር የታፈነ አድርጎታል፡፡ በክልሉ ከህወሓት ሌላ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ እናም ህወሓት ከብዙዎቹ እንደ አንዱ ይሆናል ማለት ነው፡፡

የትግራይን ህዝብ በተጠቂነት የሥነ ልቦና ጫና ውስጥ ከቶ ራስን የዚህ ጥቃት መድህን አድርጎ በመሳል የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ወንዝ የሚያሻግር አይደለም፡፡ እናም ህወሓት ከዚህ ከተቸነከረ ቀኖናዊ አስተሳሰቡ ተላቆ ተነቃናቂና ተራማጅ መሆን ካልቻለ ለፖለቲካ መቅሰፍት የመዳረግ እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ኦዴፓና አዴፓ ከፖለቲካ መቅስፍቱ ለመዳን በለውጥ ማዕበል በመታጀብ በማራመድ ላይ ይገኛሉ፡፡ አንድ ፓርቲ ይብዛም ይነስም በአንድ ህዝብ ውስጥ የራሱ የሆነ ማህበራዊ መሰረት ይኖረዋል፡፡ ይህ የፓርቲ ማህበራዊ መሰረት ሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነትን ካገኘ ደግሞ የአንድ ክልል ወይንም ሀገር ገዢ የፖለቲካ መስመር ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ በዚህም ያ ፓርቲ ተከታታይ ምርጫዎችን እያሸነፈ ቅቡልነቱን የሚያረጋግጥበትን ዕድልንም ያገኛል፡፡ ፓርቲው በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ማህበራዊ መሰረቱ እየሳሳ ሲሄድ ደግሞ በሌላ ተፎካካሪ ፓርቲ ብልጫ ተወስዶበት ከገዢነት መንበሩ በመሰናበት በተራው የተፎካካሪነቱን ቦታ ይይዛል፡፡ ይሄ የዲሞክራሲ ተፈጥሮ ባህሪና መለያ ነው፡፡

ከወራት በፊት በኢትዮጵያ የነፈሰው የለውጥ ነፋስ ቀጣዩን የኢትዮጵያን መፃዒ ፖለቲካዊ በዚህ አቅጣጫ የሚያስኬደው ይመስላል፡፡ ኦዴፓም ሆነ አዴፓ በየክልላቸው እየተንቀሳቀሱ ካሉት እንደ ኦነግና አብን ካሉ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠብቃቸው ብርቱ ፉክክር ቀላል እንዳለሆነ ገና ከመነሻው የፖለቲካ መጫወጫ ሜዳውን ክፍት ሲያደርጉ ያውቁታል፡፡ እናም ሜዳውን ከፍተው ብቻ ዝም አላሉም፡፡ ሁለቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የምርጫ ጊዜ ሲቀርብ ነገ የሚጠብቃቸውን ብርቱ ፉክክር ታሳቢ በማድረግ ህዝባዊ መሰረታቸውን ሊያሰፉ የሚችሉላቸውን ሰፊ ሥራዎን በመሥራት ላይ ናቸው፡፡

እነዚህ ሁለት ፓርቲዎች ያለፈውን ጥፋት አምነው በቀጣይ ህዝቡን በመካስ መንፈስ በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከሀገር ውስጥ እስከ ውጪ ሀገራት ላሉ ኢትዮጵያዊያን ያለፈውን የለውጥ ስኬትና መፃኢውን የፖለቲካ አካሄድ በማስረዳት ሥራ ተጠምደዋል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ የፖለቲካ መደላድልን በመፍጠር የተቀባይነት አድማሳቸውን በማስፋት ላይ ይገኛሉ፡፡

የህወሓት አካሄድ ከዚህ ይለያል፡፡ ህወሓት ራሱን እንደ ብቸኛ ሞልቃቃ የትግራይ ልጅ አድርጎ ራሱን ያስባል፡፡ ራሱን ከትጥቅ ትግሉ የታሪክ ቁርኝት ጋር በማስተሳሰር ታሪካዊ የውለታ ድርሻውን አክሊል በራሱ ላይ መጫኑ ባለበት ቆሞ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ እናም አዴፓና ኦዴፓ እያደረጉ እንዳሉት ሁሉ ህወሓት በክልሉ ካሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ በጤናማ የውድድር መንፈስ ከመስራት ይልቅ ዛሬም ራሱን እንደ ብቸኛ ልጅ እየቆጠረ ይገኛል፡፡

ህወሓት ራሱን ለትግራይ ህዝብ በልኩ እንደተሰፋ የፖለቲካ ድርጅት አድርጎ ያስባል፡፡ ይህም አስተሳሰብ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርፅ አጥብቆ ሰርቷል፡፡ አካሄዱም ይህ አይነቱን አስተሳሰባዊ ቅኝትን የያዘ ነው፡፡ ህወሓት በተቻለው መጠን ትግራይ ማለት ህወሓት፤ ህወሓት ማለት ትግራይ ማለት መሆኑን ለማሳየት ቀላል የማይባል ሥራን ከውኗል፡፡ ፓርቲውና ህዝቡ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ እንደሆኑ እንዲታወቅለት ብርቱ የማስረፅ ሥራን ሰርቷል፡፡

ይህም አስተሳሰቡ ባለፉት ሶስትና አራት አስርት ዓመታት በሚገባ ሰርቷል፡፡ እስከዛሬም የነበረው ፖለቲካ በቀጣይም እስከምን ያህል ርቀት እንደሚያስኬድ አይታወቅም፡፡ ህወሓት የወጣበትን ህዝብ እንደሰብዓዊ ጋሻ የመጠቀም ፖለቲካው በእሱ ላይ የሚደርሱት ማናቸውም አስተሳሰባዊ ሥነልቦናዊ ጥቃቶች በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲደርስ በማድረግ ላይ ነው፡፡ እናም አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ህወሓት የትግራይ ህዝብ ብቸኛ ቀሪ ሀብቴ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ይህ አስተሳሰብ እስከምን ያስኬዳል የሚለውን ጉዳይ ጊዜ የሚፈታው ይሆናል፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** የተለያዩ ኢትዮጵያን የተመለከቱ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዝኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close