Connect with us

Business

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት | ክፍል ሁለት

Published

on

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት | ክፍል ሁለት

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት | ክፍል ሁለት
በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሀጽዮን

‹‹እና ይሄ ነዳጅ በኤርትራ መንግሥት አማካኝነት ተመልሶ ወደ ጎረቤት ሐገራት እየሄደ ነው እያልከኝ ነው›› አልኩ የምለው እየጠፋኝ፡፡

‹‹ስማ አንዳንድ ኤርትራዊያን ሲያወሩ የሰማሁትን ነገር ይልቅ ልንገርህ….እኔ ስላላረጋጥሁት ነው ሲያወሩ ሰማሁ የምልህ…ነዳጃችሁ ወደ ኤርትራ፣ ኬኒያና ጅቡቲ ብቻ አይደለም እየሄደ ያለው፡ ፡ሱማሊያም ገብቶ ለአልሸባብ እየተቸበቸበ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡ ይህ በእውነት አደገኛ ይመስለኛል››

እዚህ ጋር ስደርስ ደነገጥሁ፡ ፡አልሸባብን ለመዋጋት ሱማሊያ በረሃዎች ውስጥ ያሉ የአገሬ ወታደሮች ትዝ አሉኝ፡፡ እነርሱ ለሚዋጉት ጠላት የአገራቸው ነዳጅ እየተሸጠ መሆኑን ሲሰሙ ምን ሊያስቡ እንደሚችሉ አሰብኳቸው፤ እዚህ ከኤርትራ መንግሥት ሕገወጥ ሰዎች ጋር ተባብረው ነዳጁን ለአልሸባብ የሚሸጡ ባንዳዎች ደግሞ ክፋታቸው በዓይነ-ኅሊናዬ ታየኝ፡፡
ከአንደበቴ የወጣው ቃል ‹‹ማይ ጋድ ›› የሚለው ብቻ ነው፡፡

‹‹ይሄ እኮ በቀጥታ ወደነበርንበት ቀውስ የሚከተን ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ለምን ከትናንት ስህተታቸው አይማሩም..›› ብዬም ተንተፋተፍሁ፡፡

‹‹ሰውዬው ስትራቴጂስት አይደለም፡፡ የዕለት ስሜቶች ያበሳጩታል፤ ቀላል ነገሮች ያስደስቱታል፤ ቅርብ ቅርብ ነው የሚያስበው›› ብሎኝ ወንበሩ ላይ ተመቻቸ፡፡

‹‹እኔ እንደውም የትግራይ አክቲቪስቶች ኢሳያስ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እየገባ ነው እያሉ ሲንጫጩ እና የክልሉ መንግሥትም ይህንኑ ደግፎ መግለጫ ሲሰጥ ተራ መወራጨትና ሥልጣን ሲጠፋ ያደረጉት የተስፋ መቁረጥ እንቅስቃሴ አድርጌ አይቼው ነበር፡፡በዚህ ደረጃ ግን እጅ ሰጥተናል ብዬ አልጠብቅም ነበር፡፡›› ስለው

‹‹የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ብሽሽቅ ላይ ያላችሁ ይመስለኛል›› አለኝ፡፡
ሳቅሁና
‹‹እኔ ፖለቲከኛ እንዳልሆንሁ ነግሬሃለሁ፤ተራ ጋዜጠኛ ነኝ››
‹‹አይ አንተ ጋዜጠኛም እኮ ፓርላማ አልገባም፤ ወይም ወንበር የለውም እንጂ ያው ፖለቲከኛ በለው››
በሐሳቡ በከፊል እንደምስማማ ነግሬው ‹‹ለምን ብሽሽቅ ላይ ናችሁ አልከኝ›› አልኩት

‹‹ለምን መሰለህ…አሁን ኢሳያስን የነፍስ አባት አድርጎ የሚያይ ፖለቲከኛ ሳይ ተገርሜያለሁ፡፡ እኔና መሰል ኤርትራዊያን ዓቢይ አሕመድን የነፍሳችንም የስጋችንም አባት አድርገን ብንቆጥረው፣ ከዘመዶቻችን ጋር ስላገናኘን፣ ከኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻችን ጋር ስላስታረቀን፣ እዚህ አዲስ አበባ ድረስ መጥተን እንድንዝናና ስለፈቀደልን ነው፡፡ እናንተ ኢሳያስ ምን ስላደረገላችሁ ነው ይህንን ያህል የተነጠፋችሁለት››

‹‹ይሄ የዘረዘርከው በሙሉ እኮ በዓቢይ አሕመድ ብቻ አልመጣም፤ ያለ ኢሳያስ አፈወርቂስ ይህ ሁሉ ይሆን ይመስልሃል››
‹‹አይደለም አይደለም…ኢሳያስ ያንን ካደረገም ቀድመን ማመስገን ያለብን እኛ እኮ ነን፡፡ 13 የፖለቲካ ድጅቶችን ሲያስታጥቅና ሲያሰለጥን የነበረ ሰው ነው፡፡ ሊበታትናችሁ የነበረ ሰው ነው፡፡››

‹‹እኮ እሱን ነገር እኮ ትቼዋለሁ፤ ይቅር እንባባል ብለው ነው ይሄ ሁሉ ሽር ጉድ››
‹‹ወይ መተው…አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ካለው ቀውስ ጀርባ ሻዕቢያ እንደሌለበት ምን ማስረጃ አቅርበህ ትሞግተኛለህ…›› ሲለኝ ምላሽ አጣሁ፡፡

‹‹ስማ የኢትዮጵያዊያን የእርስበርስ ማኅበራዊ ትስስር ጠንካራ ስለሆነ እንጂ እንደ ኢሳያስ ፍላጎት ቢሆን ኖሮ ዱሮ ፈራርሳችሁ ነበር፡፡ ይሄኔ እኔና አንተም የምንገናኘው በአንድ የአውሮጳ አለያም የአሜሪካ ከተማ ውስጥ ነበር፡፡ ወይም አንገናኝም ነበር፡፡››
‹‹እና ሕግዴፍ የደገፈው ቀውስ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ አለ እያልከኝ ነው…››
‹‹ስማ …›› የሚል አማርኛ ተጠቀመ፡፡እዚህ ጋር ሲደርስ አማርኛ፣ትግርኛና እንግሊዝኛው ተቀላቀለበት፡፡

‹‹ስማ ነገርኩህ…የእናንተ ማኅበራዊ ግንኙነት፣ የሕዝቡ ፍቅር ጠንካራ መሆኑ እንጂ እንደ ፖለተከኞቻችሁ ገመድ ጉተታ እና እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ዱላ ማቀበል ቢሆን ኖሮ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ አብቅቶላችሁ ነበር፡፡›› አለኝ ፊቱ ላይ መሰላቸት ታየኝ፡፡ከዚህ በላይ በጉዳዩ ላይ የማውራት ፍላጎት አላየሁበትም፡፡

‹‹ሻዕቢያ ሻዕቢያ አትበል ለማንኛውም፣ተረጋጋ አልኩት››
‹‹ይልቅ አንተ ተረጋጋ፣ እንዲህ እየለፈለፍህ አንተንም አፍነው ሀውላ ሰውራ እንዳያስገቡህ›› አለኝ፡፡ ሀውላ ሰውራ ኤርትራ ውስጥ ከታወቁ እስር ቤቶች አንዱ መሆኑን አውቃለሁ፡፡

ወዲያው ሚስቱ ከደቡብ ሱዳን ደወለች፡፡ እርሱ በትግርኛው ወሬውን ቀጠለ፡፡ እኔ ግን በድብልቅልቅ ስሜት ውስጥ ሆኜ ሰማይ ሰማይ እያየሁ ነበር፡፡ በተለይ መጨረሻ ላይ ‹‹አፍነው ሀውላ ሰውራ እንዳያስገቡህ›› ያላት ነገር ጎመዘዘችኝ፡፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ እርቅ ካወረዱ በኋላ፣ የሻዕቢያ ደኅንነቶች አፍነው ይወስዱኛል ብሎ ወደ ክፍለ-ሐገር ገጠር ውስጥ የገባው ጋዜጠኛ ትዝ አለኝ፡፡ ይህንን ጉዳይ ተመስገን ደሳለኝ በፍትሕ መጽሔት ላይ ጠቀስ አድርጎት አልፏል፡፡

አይ አንተ ምሥራቅ አፍሪቃ አትረፍም አይለፍልህም ያለህ ሪጅን!!
ስልኩን አውርቶ ሲጨርስ አንድ ደብል ጂን አስቀዳልኝ፤ ኤርትራዊው ባለሃብት!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close