Connect with us

Ethiopia

ህዳር 29፡ በለውጥና ነውጥ መካከል

Published

on

ህዳር 29፡ በለውጥና ነውጥ መካከል

ህዳር 29፡ በለውጥና ነውጥ መካከል | ሬሞንድ ኃይሉ @DireTube

24 ዓመትታ በህዳር 29 ፊት ምንም ናቸው፡፡ በኢትዮጵያውያን መንደር ሁለት አስርታት አንዲት ቀን ላይ ለመግባባት አይበቁም፡፡ እናም ስለ ህዳር 29 ከትናንቱ የበለጠ ንትርክ ዛሬ ይሰማል፡፡ የነገው ደግሞ ከዚህም ይብስ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪከ ውስጥ የውዝግብ ፌርማታ ለመሆን ከበቁት ዕላታት አንዷ የሆነችው የህዳሯ ፍጻሜ መባቻ አሁን 24 ዓመት ሞልቷታል፡፡ ነግር ግን ውዝግቧ ትኩስ ነው፡፡ ዛሬም አፍለኝነቷ ሀገር ይረብሻል ፡፡ ለሀገራዊ መግባባት ስትታሰብ ለሀገራዊ መጠፋፋት ምክንያት መሆኗም ያስገርማል፡፡

ህዳር 29 በታሪክ ውስጥ ያላት ሚና ፕሮፖጋናዳ የተጫነው ነው፡፡ ገዥውም ተቃዋሚውም ስለቀኗ ሲያወራ ከሀቁ ይልቅ ግነቱ ይበዛል፡፡ ኢህአዴግ 1987 ላይ የተገኘችው ያች ቀን ሀገር ታዳጋለች ብሎ ስግዱላት ይላል፡፡ ተቃዋሚው በአንጻሩ ኢትዮጵያ የምር ሞቷን የሞተችው በዚህ ቀን ነው እያለ ሙሾ ማውረድ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ የዛሬዋ ቀን በርግጥ በታሪካችን ውስጥ የት ትቀመጣለች? ህዳር 29 ለኢትዮጵያውያን ምን ትርጉም አላት?

ህገ-መንግሰት እንጅ ህገ-መንገስታዊ ስርዓት የሌላት ሀገር

ኢትዮጵያ ለህገ-መንግስት በይተዋር ሁና የኖረች ሀገር አይደለችም፡፡ ፍተሃ ነገስትን ተትን የቀርብ ጊዜ ታሪክ ላይ ብናተኩር እንኳ ስምንት አስርታትን በህገ-መንግስት ሀዲድ ተጉዘናል፡፡ ሰማኒያ ዓመትት የቻይና እና የምስራቅ ኢሲያ ሀገራትን ለውጥ ላየ ሰው ብዙ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ተመጽዋች ከመሆን ተነስታ ታሪክ የቀየረችው ከላይ ከጠቀስኩት ጊዜ ባነሰ ወቅት መሆኑን ስናስብ ምናልባት ቁጭጥ ይሰማንም ይሆናል፡፡ ነገር ግን መጓዝን እንጅ ወዴት እንጓዝን ያልጠየቀ ህዘብ መዳረሻው ከዚህ እንደማይሻል ስናውቅ ቁጭታችን ይረግባል፡፡

ኢትዮጵያ ህገ-መንግስት ስታጸድቅ የኖረችው ለመጓዝ ያህል ነው ፡፡ ቀዳመዊ ኃይለስላሴ የመጀመሪያውን ህገ-መንግስት እንዳሻቸው ካጸደቁ በኋላ የግላቸው ድርሰት ይመስል መታሰቢያነቱን ለኢትዮጵያ ህዝብ አብርክቸዋለሁ መለታቸው የታሪካችን ስላቅ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ ይህ የታሪክ ስላቅ በጊዜ ሂደት የሚያመረቀዝ ሁኖ ንጉሱን መፈናፈኛ አሳጣቸው፡፡ ጄነራል ታደሰ ብሩ የእኔ ብሄር ከዚህ በላይ ሲሰቃይ አላይም ብለው ሸፈቱ፡፡ ሜጫና ቱለማ ማህበርም ድንቁርናን አጠፋለሁ ብሎ ንጉሱን ለማጥፋት ማሴር ጀመረ፡፡ የባህረ ነጋሸ ሰዎች የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴን ፖለቲካ ተቃውመው የተደራጀ ትግላቸውን ቀጠሉ፡፡ አስመራ በፌደሬሽን መተዳዳሯ አብቅቶ ኢትዮጵያ ሆነች ቢባልም መረብ ምለሽ ከእናት ሀገሯ ለመለየት ከወሰነች ግን የቆይች ትመስል ነበር፡፡

በዚህ የታሪክ ሂደት የዋለልኝ መኮንን ትውልድ የብሄሰቦች መብት ይከበርና መሬት ላራሹ እያለ በማዕበል ፍጥነት አራት ኪሎ ደጃፍ ደረሰ፡፡ ከመጣው ማዕብል ለማምለጥ ደፋ ቀና ማለት የጀመሩት ቀዳማዊ ኃይለስላሴም በወታደሩ ገፋ ተደርገው በቀላሉ ለመውደቅ ቻሉ፡፡ ደርግ ባለተራ ሁኖ ሀገር መምራት ጀመረ ፡፡ የኢትዮጵያን የዘመናት ጥያቄ ለመፍታት ባለተለ ፡፡ ሶሻሊዝም የሁሉም ነገር መፍቻ ነው አለ፡፡ የኤርትራም ሆነ የሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥያቄ የሚፈታው በአብዮት ብቻ መሆኑን አወጀ፡፡ አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይንም ሞት ብሎ የብሄሮችን ጥያቄ በአፈሙዝ መመለሱን ቀጠለ፡፡ የረገጠው ሁሉ ጦርነት እየሆነበትም 17 ዓመታትን ወደፊት ተራመደ፡፡

ከዚህ በኋላ ግን ታሪክ ለሱ የሰጠውን ዕድል ነጠቀው፡፡ በደርግ ወቅት ይታገሉ ከነበሩ አስራ ሰባት የብሄር ድርጅቶች አንዱ የምንሊክን ቤተ-መንሰግትን ተቆጣጠረ፡፡ ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ አዲስ ህገ-መንግስት እንዲረቀቀ ከተቃዋሚዎቹ ጋር ወሰነ፡፡

በሽግግር መንግስቱ ውስጥ የሚኒስትርነት ቦታዎችን ተቆናጦ የነበረው ኦነግ ሳይቀር የህገ-መንግስቱ ዋና አርቃቂ ሁኖ ከፊት ተሰለፈ፡፡ የኦነግ ናቸው የሚባሉ አንቀጾችን ሳይቀር በህገ-መንግስቱ ውስጥ እንዲካተቱ አደረገ፡፡

ሌሎችም ግራ ዘመም የፖለቲካ ኃይሎች እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ጥቅም የሚስጠብቁ አነቀጾች እንዲካተቱ የየራራሳቸውን ሚና ተወጡ፡፡ በሚለዮኖች የሚቆጠር ህዝብም እንዲወያየ ተደረገ፡፡ በዚህ ህገ-መንግሰት ውስጥ የሚያወዛግው አንቀጽ 39 ይህ ነው የሚባል ቅሬታ ሳቀርብበት የህገ-መንግስቱ አካል ሆነ፡፡ የኢትዮጵያን የዘመናት ጥያቄ ይፈታል የተባለው የኤፌዴሪ ህገ-መንግስት በህዝብ ውይይት ታጅቦ ለመጽደቀወ በቃ፡፡

የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የራሱ ውስንነቶች የነበሩበት መሆኑ አያከራክርም ፡፡ በተለይም ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ኃይሎችን ተሸናፊ አድርጎ መጀመሩ ለዚህ ዋቢ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ በሀገሪቱ ሁለተኛውን አብላጭ ብሄር የሚይዘው አማራ በአግባቡ አለመወከሉም ህገ-መንግስቱን እጅ ሰባራ አድርጎታል፡፡ ከፊሉ ወገን ለዘመናት የተደራጀና የብሄሩን መብት የሚያስጠብቁ የፖለቲካ ልሂቃን ይዞ ወደ ህገ-መንግስት ማርቀቁ ሲገባ አማራ ግን ብሄር ነው አይደለም የሚለው ጥያቄ እንኳን በውሉ የተመለሰ አልነበረም፡፡

በዚህ የተነሳም የብሄር ሜዳ በሆነው ህገ-መንግሰት ውስጥ የአማራ ተወላጅ ልሂቃን አሀዳዊነትን ይሰብኩ ነበር ፡፡ ይህ ደግሞ የብሄር ጭቆና ድርሶብኛል ለሚለው አብዛኛው የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰብ የሚዋጥ አልሆነም፡፡ እናም ገና ከጅምሩ አሃዳዊት ኢትዮጵያን የሚሰብከው የፖለቲካ ኃይል ከሜዳው ተሰናባች ሆነ፡፡ እሱ የሚያነሳቸው ሀሳቦችም ከቀደመው ስርዓት ጋር ተያያዙ፡፡ የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ከመነሻው ልዩነት ያለበት ሁኖ ጉዞ መጀመሩ ለዛሬው ሽንፈቱ ምክንያት ነው፡፡

ህገ-መንስግስት እንጅ ህገ-መንገስታዊ ስርዓት እንዳይኖረንም የራሱን ሚና ተጫውቷል፡፡ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት የሌለው ሀገር ደግሞ ፖለቲካው የትም ሊደርስ አይችልም፡፡ የኢፌድሪ ህገ-መንግስት ከቀደሙት ብቻ ሳይሆን ዛሬም ዓለም ላይ ካሉት ጋር የሚፎካከር ቢሆንም ህገ-መንገስታዊ ስርዓትን ግን የመፍጠር አቅም አልነበረውም ፡፡ይህ ባህሪው ደግሞ ከንጉሱና ከደርግ ዘመን ህገ-መንገስታት ጋር ያመሳስለዋል፡፡

ህዳር 29 ለኢትዮጵያውያን ምን ትርጉም አላት ?

ህዳር 29 የጸደቀው የኢፌዴሪ ህገ-መንገስት ከታሪክ አንጻር ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ያሉት ነው፡፡ የመጀመሪያው የብሄር ብሄረሰቦችን ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ የሰጠ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛው እንደከዚህ ቀደሞቹ በሹማምንት ብቻ ጸድቆ የተተገበር አይደለም ፡፡ የህገ-መንገስቱ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት አንቀጾች ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር የሚያትቱ መሆናቸውም ከቀደሙት እንዲለይ ያደርገዋል፡፡

ይህ ብቻም አይደለም የኢፌዴሪ ህገ-መንገግሰት ለቡድን መብቶች ያደላ ነው ተብሎ ተደጋጋሚ ትችት ቢቀርብበበትም እውነታው ግን ለግለሰብ መብቶች አብላጫውን ቦታ ሰጥቶ እንመለከተዋለን፡፡ ከላይ የጠቀስከኩት ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያብራራው የህገ-መንግሰቱ አንድ ሦስተኛ ክፍልም በብዛት ስለ ግለ መብቶች መከበር የሚሟገት መሆኑም ጥሬ ሀቅ ነው፡፡ ከዚህ እንጻር ህዳር 29 በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የግልና የቡደን መብቶትችን የሚከብር ህገ-መንገስት የጸደቀባት ቀን ናት፡፡

ማስታወሻ ፡- የጸሀፊው ትኩረት የህገ-መንገስቱ ሰንድ እንጅ ህገ-መንገስታዊ ስርዓቱ ላይ አይደለም፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close