Connect with us

Ethiopia

ከንቲባዬን ኢንጅነር ታከለ ኡማን እደግፋለሁ፤ ግዜያዊ መታወቂያ ሀሳብ እቃወማለሁ …

Published

on

ከንቲባዬን ኢንጅነር ታከለ ኡማን እደግፋለሁ፤ ግዜያዊ መታወቂያ ሀሳብ እቃወማለሁ ...

ከንቲባዬን ኢንጅነር ታከለ ኡማን እደግፋለሁ፤ ቋሚ አድራሻ ለሌላቸው ግዜያዊ የአዲስ አበባ መታወቂያ ይሰጥ የሚበለውን ሀሳብ እቃወማለሁ፡፡ *** ከስናፍቅሽ አዲስ

የከተማዬ ከንቲባ ደጋፊ ነኝ፤ ኢንጅነር ታከለ ኡማ በሚሰሯቸው ስራዎች ሁሉ ቀናውን በመደገፍ ለከተማዬ እድገት የበኩሌን እወጣለሁ፤ የጠመመው እንዲቀና ሀሳቤን እሰነዝራለሁ፡፡ መንጋ ደጋፊ አይደለሁም፤ ዘረኛ ተቃዋሚነትም የለብኝም፡፡ በምክንያት እጠይቃለሁ፡፡

አዲስ አበባ በከተማዋ ለሚኖሩ ነገር ግን ቋሚ የመኖሪያ አድራሻ ለሌላቸው ሰዎች ጊዜያዊ መታወቂያ ልትሰጥ መሆኑን ሰምተናል፡፡ አጠራጣሪም አነጋጋሪም ሀሳብ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታወቂያ እድሳት ጉዳይ ዜግነትን አማክሎ የሚዘጋጀው መታወቂያ እስኪታደል በይደር ይቀመጥ በሚል ማደስና አዲስ ማውጣት መቆሙ ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን የምንሰማው ዜና በብዙ መልኩ ግልጽነት ይጎድለዋል፡፡ ቀድሞውኑ መታወቂያ ማለት ቋሚ አድራሻ ያለው ተመዝግቦ በአድራሻው የሚሰጠው የነዋሪነት ማረጋገጫ ነው፡፡ ቋሚ አድራሻ የሌለው ሰው የከተማዋ ቋሚ ነዋሪ አይደለም፡፡

አንድ ዜጋ የአንድ ስፍራ ቋሚ ነዋሪነት መታወቂያ ሲሰጠው በስፍራው ይመርጣል ይመረጣል፤ መሠረተ ልማት እና መሰል የሀገር ጥቅሞችን ያገኛል፡፡ ሀገር እሱን አንድ ብላም የምትቆጥረው በዚህ በቋሚ አድራሻው መዝገብ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም አንድ ዜጋ ከአንድ ስፍራ ወደ ሌላ ስፍራ ሲንቀሳቀስ በህጋዊ መልኩ አካባቢ ቀይሮ የነዋሪነት መታወቂያውን መቀየር ከፈለገ ቀድሞ ከነበረበት ስፍራ መልቀቂያ ያመጣና በአዲሱና በመረጠው አካባቢ ነዋሪ ለመሆኑ ማረጋገጫ ይቀበላል፡፡ ከዚህ ውጪ ቋሚ አድረሻ የለኝም ማለት የትም አምታትቼ እኖራለሁ ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ይመስለኛል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ በነዋሪነት አድራሻውን ካስመዘገበው ህዝብ ቁጥር ቀላል የማይባል ምናልባትም በመቶሺዎች የሚቆጠር የሁለት እና ከዚያ በላይ አካባቢዎች የነዋሪነት መብት የተጎናጸፈ ባለጸጋ ነው፡፡

ይህ ቋሚ አድራሻ ለሌላቸው ጊዜያዊ መታወቂያ መስጠት የሚለው ሀሳብም በተመሳሳይ መልኩ አዲስ አበባም መቐሌም፣ አዲስ አበባም ባህር ዳርም፣ አዲስ አበባም ሀዋሳም፣ አዲስ አበባም አዳማም ነዋሪ ነኝ ባይ ዜጋ ይፈጥራል፡፡

የሁለት ከተማ ነዋሪን ፍላጎላት ለማሟላት የሚሰራ ስራ መቀመጫቸው አንድ ስፍራ የኾኑ ንጹሃን ዜጎችን ይጎዳል፡፡ በሌላ በኩል መምረጥ መመረጥ ለመኖር በመረጡት ስፍራ በሚያገኙት የነዋሪነት መብት የሚሰጥ የዜግነት መብት ነው፡፡

አንድ ነዋሪ የትም የሚኖር የትም የሚመዘገብ የትም መብት ያለው ከሆነ ስርዓት አልበኝነት እንጂ ስልጣኔ አይደለም፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ ዜጋ በስራ ምክንያት ይኖራል፤ ለተለያዩ ጉዳዮች መጥቶም የከተማዋ ኑሮ ማርኮ ያስቀረው ግና መርጦ አዲስ ልኑር በሚል መኖሪያው ያልቀየረውም ብዙ ነው፡፡

ቋሚ አድራሻ የሌላቸው የሚለው ቃል ከመታወቂያ አሰጣጥ ፍልስፍና ጋር የሚቃረን ሀሳብ ነው፡፡ መታወቂያ መለያ ነው፤ ለመለያ ደግሞ መሰረታዊ የሚባሉ መርሆች መከበር አለባቸው፡፡

የዜግነት መታወቂያው በመላ ሀገሪቱ አንድ ካልሆነ በመላ ሀገሪቱ ያሉ አስተዳደሮች የመታወቂያ አሰጣጣቸው የተቀናጀ፣ ዜጋውን መዝግቦ በቋሚ አድራሻ የለየ ሊሆን ይገባል፡፡

ብዙ ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ ባለ የዘር ፖለቲካ በሚቀነቀንበት ሀገር እንዲህ ያሉ አሰራሮች ከቅንነት መንጭተው ቢተገበሩ እንኳን የአንዱን ብሔር ቁጥር ለመጨመር፣ ለማስፈር፣ ህጋዊ ባልሆነ ስልት ወገንን ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበ ነው በሚል በዜጎች ዘንድ ጥርጣሬን የሚፈጥር ነው፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close