Connect with us

Business

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት

Published

on

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት

ከኤርትራዊው ባለሐብት ጋር የተደረገ ውይይት | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስኃጽዮኝ

የተገናኘነው በአንድ የመዝናኛ ስፍራ ነው፡፡
‹‹ሰላም አንገሶም እባላለሁ›› (ስሙ ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ተቀይሯል፡፡)
‹‹በኃይሉ እባላለሁ፤ጋዜጠኛ ነኝ፤ኑሮዬን የመሰረትሁት ወሬ በመለቃቀም ነው››
ተሳሳቅን፡፡

‹‹እኔ ባለሃብት ነኝ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጣሁት ለኢንቨስትመንት ነው፤ በሚኒራል ውሃ (ለዚህ ጽሁፍ ሲባል የቢዝነሱ ስም ተቀይሯል) ላይ ለመሰማራት ፕሮሰስ እያደረግሁ ነው››

‹‹ኦው በጣም ደስ ይላል፤ ኢኮኖሚስቶች ስኬርሲቲ (እጥረት) ኢንቨስትመንትን ይጋብዛል ይላሉ፤ ይሄ ሥራ የተሻለ ስኬርሲቲ ባለባት ኤርትራ ላይ ቢሆን አይሻልም ነበር እንዴ… ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የማዕድን ውሃ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ውድድሩ ከበድ ይላል፡፡ እና ይህንን ፕሮጀክት ኤርትራ ውስጥ ብታደርገው አይሻልም ነበር››

ንግግራችን በእንግሊዝኛ ነው፡፡ አማርኛ አይችልም፡፡ እዚህ ከመጣ በኋላ በሚችላት አማርኛ የገበያና የሰላምታ ቃላትን አልፎ አልፎ ይጠቀማል፡፡ ይህንን ሐሳቤን እንዳልተስማማበት ለመግለጽ ሐሳቡን ሰብሰብ ሲያደርግ ታየኝ፡፡

‹‹ቅድም ጋዜጠኛ ነኝ ብለኸኝ ነበር፡፡ ጋዜጠኛ ከሆንህ ይህንን ማወቅ ነበረብህ፡፡ በኤርትራ ውስጥ እኮ እንኳን እንዲህ ያለ ኢንቨስትመንት፣ ሻይ ቤት ለመክፈት፣ ሕግዴፍን አስፈቅደህ ሐጎስ ኪሻን ለምነህ፣ ፕሬዚዳንት ጽ/ቤቱን ደጅ ጠንተህ፣ ተቃዋሚ ዘመድ እና ጓደኛ እንደሌለህ እርግጠኛ ሆነህ ነው፡፡ አሁን እኔ እንዳሰብኳቸው ያሉ ትልልቆቹን ሥራዎች ደግሞ ቀይ ባሕር ኮርፖሬሽን ይዟቸዋል፡፡ አምራችም ቸርቻሪም ሻዕቢያ እራሱ ነው፡፡›› አለ፡፡
በንግግሩ ውስጥ እልህና ብስጭት ይታያል፡፡

‹‹ታዲያ ይሄ መቼ የሚቀየር ይመስልሃል›› አልኩት፡፡
‹‹እንግዲህ የኢሳያስን ግፍ ቆጥሮ እርሱን የሚነቀንቅ ኃይል ሲመጣ ነዋ›› አለኝና ፊቱን በተስፋ መቁረጥ አሸ፡፡
‹‹ይህንን ኃይል እኮ መፍጠር ያለባችሁ በቅድሚያ እናንተ ባለሀብቶችና የአገሪቱ ወጣቶች ናችሁ…›› ሐሳቤን ሳልጨርስ አቋረጠኝ፡፡

‹‹አንተ ልጅ ምን ነክቶሃል… ኤርትራ እኮ የኢሳያስ ፒኤልሲ ነች፡፡ አሁን የሁለቱ ሀገር ሕዝብ ሰላም መጥቶ እኮ ስደቱ ከድሮውም ብሷል፡፡ ኢሳያስና በዙሪያው ያሉ ጋሻ ጃግሬዎቹ ብቻ የቀሩ እስኪመስልህ ድረስ እኮ ወጣቱ ተሰድዷል፡፡ አገሪቱን ጧሪና ቀባሪ የሌላቸው አዛውንቶች የሞሉት ሆኗል እኮ፡፡ አለ የምትለው ወጣትም በወንድሙ በእህቱ በእጮኛው የሚሰለል፣ በሕግዴፍ ታርጌት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ይህንን ወጣት እንዴት ነው አደራጅተህ የፖለቲካ ሥራ የምትሰራው…›› አለኝ፡፡

ይህ ኤርትራዊ ባለሀብት ገንዘብ ያሰባሰበው በደቡብ ሱዳን በሰራው ቢዝነስ ነው፡፡ ሆኖም በሀገሩ ተስፋ የቆረጠ ይመስላል፡፡የጠየቅሁትን ጥያቄ በጥያቄ ሲመልስልኝ፣ መፍትሔ የመሰለኝን ነገር አቀረብሁለት፡፡

‹‹አሁን እኮ አቶ ኢሳያስ ከዚህ በኋላ ሰበብ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ እስከዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር ጸብ ስላለን ነው ዴሞክራሲያዊ የማንሆነው ሲሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እርቅ አውርደዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ውስጥ ጉዳያቸው ሊያተኩሩ ይችላሉ፡፡››
ተንከትክቶ ሳቀ፡፡

‹‹ኢሳያስን አታውቀውም፡፡ ወደራስ ተመልክቶ ለውስጥ ችግር ምክንያቱ እኛ ነን የሚለው እኮ ጤነኛ መሪ ነው፡፡ ይሄ ሰው እኮ ታሟል፡፡ አሁንም ከዚህ ከኢትዮጵያና ኤርትራ እርቅ ምን እንደሚያተርፍና ከኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ እንዴት እንደሚጠቀም ነው የሚያሰላው… ለምሳሌ ልንገርህ ነዳጅ ወደ ኤርትራ በሕገ-ወጥ መንገድ እየተሻገረ ነው የሚሉ ወሬዎች አሉ አይደለም›› አለ ሐሳቡን ለመቀጠል የኔን አዎንታዊ ምላሽ እየተጠባበቀ፡፡ ልክ እንደሆነ በፊቴ እንቅስቃሴ ገለጽሁለት፡፡

‹‹አየህ…ነዳጁ በርግጥ ወደ ኤርትራ እየሄደ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በተራ ኤርትራዊያን ነጋዴዎች አይደለም፡፡ በሕግዴፍ (ሻዕቢያ) ነው፡፡ አስገራሚው ነገር ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ነዳጅ የሚወስደው ወደ ኤርትራ ብቻ አይደለም የሚያሻግረው…ወደ ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሐገሮች እየወሰደም ይሸጠዋል፡፡ …ኢትዮጵያ ነዳጅ የምታቀርበው ከአካባቢው ሐገራት አንፃር በጣም በርካሽ ነው፡፡ ለምሳሌ ኬኒያ አንድ ሊትር ቤንዚን የምትሸጠው በኢትዮጵያ ብር ሲሰላ 38 ብር ነው፡፡ ጅቡቲ እስከ 50 ብር በሊትር ታስከፍላለች፤ በኤርትራ 60 ብር ነው፡፡ አየህ ይህንን የኢትዮጵያ ነዳጅ የምትገዛው ከ20 ብር በታች በሆነ ወጪ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት ይህንን ነዳጅ ወደ ሌሎች ጎረቤት ሐገሮች እየወሰደ ቢሸጥ እንደሚያዋጣው ያወቀው ቀደም ብሎ ነው፡፡ ይህንን ተግባር እያደረገው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውድ ዋጋ የገዛችው ነዳጅ ከሕዝቡ ተነጥቆ በሌሎች ሀገራት እየተቸበቸበ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ያለ ኢሳያስ ትዕዛዝ እና እውቅና አይሆንም››

እውነት ለመናገር በዚህ ኤርትራዊ ንግግር ደንግጫለሁ፡፡ በሀገሬ ጉዳይ ባይተዋር የሆንሁ መሰለኝ፡፡ አገሬን የማላውቃት ያህል ተሰማኝ፡፡ አንዲት የገጠር ነፍሰ-ጡር፣ በነዳጅ እጥረት ምክንያት አምቡላንስ አጥታ በምጥ ስትሞት ታየኝ፡፡ በታክሲ ሥራ ሶስት ልጆቹን የሚያሳድግ አባት፣ ነዳጅ ቸግሮት ቆሞ የዋለበትን ቀን በብስጭት ሲያወራ በዕዝነ-ኅሊናዬ ሰማሁት፡፡ የአገሬ ሕዝብ በማያውቀው ችግርና እርሱ ባልፈጠረው ስህተት ሲቸገር ተሰማኝ፡፡

‹‹የአቶ ኢሳያስ መንግሥት እንዲህ ያለ ሥራ ውስጥ ከገባ ከኢትዮጵያ ጋር መጋጨቱ አይቀሩም›› ስለው አስፈሪ ነገር ጨመረልኝ፡፡
(ይቀጥላል…)

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close