Connect with us

Business

ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ፈተና?

Published

on

ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ፈተና? | ከእርቅ ይሁን ሽ.

ሚዲያዎች የኢትዮጵያ ፈተና? | ከእርቅ ይሁን ሽ.

ይቺ ኢትዮጵያ በአንዱ ስትሞላ ባንዱ እየፈሰሰባት የተቸገረች ምስኪን ፍጥረት እደሆነች ነው የሚገባኝ፡፡ በተለይም በመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በኩል እጅጉን ያልታደለች ነች፡፡ ሚዲያዎቹ እጅ ሲያወጣና ሲያጨበጭብ ብቻ በሕይወት እንዳለ ያስታውሰን የነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተሻሻለ በመጣበት ወቅት እንኳን ከማጨብጨብ አልተላቀቁም (ሑሉንም በጅምላ ማለቴ ባይሆንም)፡፡

አንዳንዴ ሚዲያ እንደነዱት የሚፈስበት አገር ኢትዮጵያ ብቻ ትመስለኛለች፡፡ አንድ ባለስልጣን የተናገረው ሁሉ ዜና ሆኖ ይቀርባል፤ በዚህ ሂደት ግን የዜና ባህሪይ ከሚባሉት አንዱ የሆነውን ‹‹እውነትነት›› ሚዲያዎቹ ማስታወስ አይፈልጉም፤ በቃ ባለስልጣን ያለው ሁሉ ለእነሱ እውነት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ምን ተብሎ ነበር፣ አሁን የተባለውስ ምን ያክል እውነት ነው ብሎ መመርመር የለም ብቻ ከቦርጫም ባለስልጣን አፍ እየቀለቡ ማሰራጨት ሆኗል ስራቸው፡፡

ለምሳሌ ካላችሁ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አዲሱን ካቢኔያቸውን ጥቅምት 6/2011 ለሕዝብ ተወካዮች ምከር ቤት አቅርበው ሲያጸድቁ ‹‹በአፍሪካ ምናልባትም የመጀመሪያ ሊባል በሚችል ሁኔታ 50 በመቶ ወይም ከ20ዎቹ እጩ ካቢኔዎች 10ሩ ሴት እንዲሆኑ ተደርጓል›› ሲሉ ምክር ቤቱ ንግግራቸውን በጭብጨባ ቀማቸው፡፡ ጠቅላዩ ግን ምናልባትም የሚል ቃል ተጠቅመዋል፤ ይህ ማለት እውነት ላይሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬን አመላካች ነው፡፡ ሚዲያዎቹ ግን በጭብጨባው ስሜታዊ በመሆን ብሔራዊ ጣቢያው ሳይቀር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ካቢኔዎቿን 50 በመቶ አደረገች ብሎ ዘገበ፡፡

ይሁንና ከዓመታት በፊት ሩዋንዳ ኢትዮጵያን ቀድማ ይህን አድርጋ ነበር፤ የተባለውን ሁሉ ሰምቶ አጃኢብ ነው በሎ ከመገረም ባለፈ እውነታውን የሚፈትሹ አድማጭ ተመልካቾች ይህን ጉዳይ ወዴት ወዴት ሩዋንዳ እኮ ቀድማናለች ሲሉ በማሕበራዊ ትስስር ገጾች የሚዲያዎቹን አላስተዋይነት (ቅሌት) አደባባይ አወጡት፡፡ ሚዲያዎቹ ግን የሚያፍሩ አልነበሩም፡፡ ዜናቸውን ያስተካከሉ መስሏቸው እና እንዳልተሳሳቱ ሊነግሩን በመድፈር ‹‹ኪጋሊ የአዲስ አበባን ተሞክሮ በመከተል የሴት ካቢኔዎቿን ቁጥር 50 በመቶ አደረገች›› አሉን፤ አሁን ነው አጃኢብ ማለት፡፡

ሌላው የኢትዮጵያ ሚዲያ ፈተና እጅግ ጥራዝ ነጠቅ መሆን ነው፡፡ ይህ በሁለት መልኩ ይታያል፡፡ አንዱ በመንግሥት በኩል ያሉትና የፈለጉትን ለማለት ከልካይ የሌላቸው የሚመመስሉት (የሚመስላቸው) ናቸው፤ ከልካይ ቢኖርማ አንዱ የክልል ሚዲያ ሌላውን ክልል በጠላትነት እየፈረጁ የዋሑን ሕዝብ ስሜታዊ ለማድረግና ከሰላም ይልቅ ጦርነትን ሲሰብኩ ውለው አያድሩም ነበር፡፡ እነዚህ ሚዲያዎች በእቅድ አይሰሩም፤ ይልቁንም ጠላት የተባለው ወገን ሚዲያ ለሰራው ዘገባ ማስተባበያ ወይም የመልስ ምት ላይ የተጣበቁ ናቸው፡፡ እንዲያውም በቅርቡ ገና ያልተላፈ ፕሮግራም በሚዲያ ሲተዋወቅ አዘጋጁ ፕሮግራራ ላይ የቀረበው ሰው ምን ምን እንዳለ ቀድሞ እንዲነግራቸውና ‹‹ጥሩ›› የመልስ ምት ለመዘጋጀት የሚሯሯጡ የሚዲያ ሰዎች እንዳለሉ ከታማኝ ምንጭ መረጃ ደርሶን ተገርመናል፤ አዝነናል፡፡

በሁለተኛው በኩል የግሉ ሚዲያ ነው የሚገኘው፤ ይህም ቢሆን ነጻነትን ረስቶታል፡፡ በተለይም መጽሔቶች የሚያሳስባቸው ፊት ገጽ ላይ እንዴት እንደሚጮኹ አንጂ እውነት ነው ወይ ሕዝብንስ ይጎደው? (ይጠቅመው) ይሆን የሚለው አይደለም፡፡ መጽሔቱ ይሸጥ እንጂ የሚጠቀሙት ነገር አያሳስባቸውም፡፡ መጽሔቱ መሸጥ ስላለበት አንድ አወዛጋቢ (አከራካሪ) ሰው ያለውን ብቻ ሳይሆን ሊል ያላሰበውን ሁሉ ‹‹አለ›› ተብሎ ይቀርብልናል፡፡ ከዚያማ እኛ ሚዲያዎቹን እንደእግዜር እያመንን አለ በተባለው ሰውና ብሔሩ ዙሪያ ስንነታረክ እንሰነብታለን፤ ሳምንት ቅዳሜ ሲደርስ መጽሔቶቹ ለነሱ ገንዘብ የሚያጋብሱበትን ለእኛ ደግሞ ሌላ መነታረኪያ የሚሆነንን ቅጥፈት ይዘውልን ይመጣሉ፡፡ ደግሞ በሚዲያ የተዛባ ተረክ ቅስቀሳ ስለመጣው የሩዋንዳው የዘር ጭፍጨፋ በየቀኑ ይነግሩናል እኮ! እነሱ ምን እየሰሩ እንደሆነ ግን አያስተውሉም፤ ደግነቱ ኢትዮጵያዊ ጨዋ ስለሆነ እንደፈለጉ የሚነዱት (በተለይ ወደ ርስ በርስ ጦርነት) ሕዝብ አይደለም፡፡

እኔ አንድ ነገር ልምከር ሚዲያዎች እባካችሁ በእቅድ ስሩ፣ ጥሩውን አሞግሱ፣ መጥፎውንና መታረም ያለበትን በድፍረትና መረጃ ላይ ተመስርታችሁ ተቹ፤ አርቁ፡፡ አቅዳችሁ ብትሰሩ እኮ እዚህ አገር ላይ ስንት ጉድ አለ፣ ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶው (ከ85 ሚሊዮን በላይ) አርሶ አደር ኑሮው የት ነው? ጠይቁት እስኪ፡፡ መንግሥት በሚለው ልክ እየሰራ ነው ወይ? ጅምር ላይስ ከሆነ እንዴት ነው አካሄዱ ወዴት የሚወስደን ይሆን? ይህንንም በባለሙያ እያስተቻችሁ አንቁን እንጂ፡፡ ሌላው ጋዜጠኝትና ብሔርተኝት (ዘውጌነት) ተለያተው ይቁሙ እንጂ፡፡ ይህ ካልሆነ ዐቢይን በመደገፍ ‹ከኛ ወዲያ ላሳር› የሚሉ አሽቃባጭ ሚዲያዎች የመጨረሻ ውጤታቸው ዐቢይንና ሕዝቡን መጉዳት ነው፡፡

የዐቢይንና የከንቲባ ታከለን የእለት ከእለት ጉዞ እየተከታተሉ ብቻ ዜና በመስራት (አሁን የሚታየኝ አካሄድ ይህ ስለሆነ ነው) እንዘልቃለን ብለው ያሰቡ ሚዲያዎች በጊዜው ከእንቅልፋቸው ሊባንኑ ይገባቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሚዲያዎች የጠፋውን እየተከታተሉ ሊያርሙና ጉደለቶችን ሊያሳዩ ይገባል እያሉ በተደጋጋሚ ቢናገሩም እንኳን ሚዲያዎቹ ፈርተዋል፤ አንዱ ምክንያት በእውቀትና ትንተና ላይ የሚሰሩ በሳል ጋዜጠኞች እጥረት እንደሆነ ይገባኛል፡፡ ምክንያቱም ለመተቸት በቂ መረጃና አመዛዛኝነት ሲያስፈልግ ለመደገፍ ግን ማጨበጨብ ብቻ በቂ ነውና፡፡

ለመሆኑ በዚሁ ሁሉ መሐል ለተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው ብሮድካስት ባለስልጣን ምን እየሰራ ነው? አለወይስ? ሚዲያ እንደፈለገው እየቀባጠረ ሕዝብና አገርን ሲያምስ ባለስልጣኑ እንደኛው ቁጭ ብሎ መታዘብ ሆነ ስራው; የዐቢይን የመስቀል አደባባይ የድጋፍ ሰልፍ በቀጥታ ስርጭተ አላስተላለፋችሁም ብሎ ሚዲያዎችን ማብራሪያ ሲጠይቅና ሲያዋክብ የነበረ ባለስልጣን ዛሬ ላይ ሚዲያዎች ከእውነታው በተቃራኒ እንዳሻቸው ሲጨፍሩ፣ ያልተባለን ተባለ ብለው ሲዘግቡና ሕዝቡን ሲያቧድኑ ምን እየሰራ ነው ጠይቁልኝማ!

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close