Connect with us

Ethiopia

ኘረስ ካውንስሉ የት ገባ?

Published

on

ኘረስ ካውንስሉ የት ገባ? | ጫሊ በላይነህ

ኘረስ ካውንስሉ የት ገባ? | ጫሊ በላይነህ

ኘረስ ካውንስል (የመገናኛ ብዙህን ምክር ቤት) የት ገባ? የበርካታ የሚድያ ባለሙያዎች ወቅታዊ ጥያቄ ነው። ለችግሩ መልስ ሰጪ፣ ያገባኛል የሚል አካል መታጣቱ ደግሞ ነገሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል።

ጥር 3 ቀን 2008 ዓ.ም በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ካውንስሉ ተመሰረተ። ምስረታው ከስምንት ዓመታት በላይ መጓተቱ ራሱን የቻለ ትልቅ ችግር ሆኖ መንግስት በካውንስሉ ምስረታ ጣልቃ ባለመግባቱ የተደሰቱ ወገኖች በወቅቱ ብዙ ነበሩ።

ምስረታውን ተከትሎ የሪፖርተሩ፣ አቶ አማረ አረጋዊ፣ የሸገሯ፣ ወ/ሮ መዓዛ ብሩ እና ሌሎችም ፈልገውም ይሁን ተገፍተው ወደፊተኛው ረድፍ ሲመጡ በጉዳዩ ባለቤቶች ዘንድ የተደበላለቀ ስሜትን ፈጥሯል።

አንዳንድ ወገኖች የካውንስሉ መመስረት ዋና አላማ ኘረሱ ውስጣዊ ችግሩን በራሱ አቅም እንዲፈታ እገዛ ማድረግ ከመሆኑ አንፃር የአመራር ቦታው በኘረስ ባለቤቶች መያዝ አላስደሰታቸውም። እነዚህ ወገኖች ቦታው ጋዜጠኛውን ጨምሮ በነፃና ገለልተኛ ወገኖች መያዝ ነበረበት በሚል ግልፅ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

ሌሎች ወገኖች ደግሞ ካውንስሉ ከእነጉድፉም ቢሆን ወደፊት እንዲራመድ ብርቱ ፍላጎታቸውን አሳይተው ነበር። ይህም ሆኖ ካውንስሉን ከተመሰረተ ሶስት ዓመታት በኃላም ግልፅ ባልወጣ ምክንያት ከተጎለተበት መነቃነቅ አልቻለም። እነሆ ካውንስሉን የበላው ጅብ አልጮህ ብሎ ጋዜጠኛውን በከፍተኛ ግራ መጋባት ውስጥ ጥሎታል።

አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ባለፉት አመታት ካውንስሉ ከምዝገባ ጋር ተያይዞ በመንግስት በኩል ችግሮች አጋጥሞታል። ይህ እውነት ነው ቢባል እንኳን ሶስት ዓመት ሙሉ ለምን ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቶ አንድ አቋም መያዝ እንዳልተቻለ ለማንም ግልፅ አይደለም።

የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ሉካንዳ ተገኘ እንዲሉ ፤ የት ይደርሳል የተባለውና በእነአቶ አማረ አረጋዊ እና በወ/ሮ መዓዛ ብሩ የሚዘወረው የኘረስ ካውንስል ስንዝርም መራመድ ተስኖት በተወለደበት አልጋ ላይ መሞቱን እነሆ ዛሬ ላይ መደበቅ አልተቻለም።

መንግስት ከ15 ዓመታት በፊት “ኘረስ ካውንስልን መመስረት ያለብኝ እኔ ነኝ” ባለበት ወቅት “አያገባህም፤ የካውንስል ምስረታ ጉዳይ የባለሙያው ነው” ብለው ሽንጣቸውን ገትረው ከተሟገቱት መካከል እነአቶ አማረ አረጋዊ አንዱ ነበሩ። ምን ዋጋ አለው!…ፈረሱም ሜዳውም ይኸው ሲባሉ ተዝረክርከው መቅረታቸው በሰፊው የሚድያ ባለሙያ ዘንድ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት “በካውንስሉ መመስረት የመጀመሪያው ተጠቃሚ መንግስት ነው” በሚል ቀና መንፈስ ለምስረታው ግልፅ ድጋፋቸውን የቸሩት የቀድሞ የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ ነበሩ። ዛሬ፤ ካውንስሉ በአመራር ድክመት ተሽመድምዶ ሲያዩት ምን ይሰማቸው ይሆን? የሚድያ ባለሙያውስ ምን ይሰማው ይሆን?

በግሌ በአሁኑ ወቅት የኘረስ ካውንስሉ የምስረታ ጉዳይ በእስካሁኑ አካሄድ ወደፊት ሊራመድ የሚችልበት ዕድሉ የተሟጠጠ ነው ብዬ አስባለሁ።

እናም ምን ይሁን? እንዴት ይቀጥል? የሚለው ውይይት የሚፈልግ ነጥብ ነው። በእኔ እምነት፤ በቀጣይ በፍጥነት መተግበር ያለበት በአመራር ላይ የተቀመጡት የኘረስ ባለቤቶች ራሳቸውን ከአመራርነት እንዲያገሉ ማድረግ ነው። ከባሰም ማሰናበት ነው። ከዚያም ኃላፊነቱን ባለቤቱ (ጋዜጠኛው) እንዲረከበው ማድረግ ነው። የኘረስ ባለሀብቶቹ ከፈለጉ ተሰባስበው የባለቤቶች ማህበር የመመስረት መብታቸውን መጠቀም እንጂ የኘረስ ካውንስልን ማገት ለስማቸውም፣ ለክብራቸውም አይመጥንምና ጉዳዩ ከዘገየም ቢሆን ቢያስቡበት?!

(ይህ ፅሑፍ የፀሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪያል አቋም አያሳይም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close