Connect with us

Art and Culture

ጽዮን ተከበበች | ከዋዜማ-እስከ ንግሡ በርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን

Published

on

ጽዮን ተከበበች | ከዋዜማ-እስከ ንግሡ በርዕሰ አድባራት አክሱም ጽዮን

ይኽ ጽሑፍ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የዛሬ አመት በታሪካዊቷ አክሱም ከተማ በድምቀት እየተከበረ ባለው ዓመታዊው የህዳር ጽዮን የንግሥ በዓል ላይ ታድሞ ድባቡን ያካፈለበት ነወ፡፡ ከዋዜማው እስከ ዛሬ ያለውን ድባብ በተመለከተ የህዳር ጽዮን ንግሥን ምክነያት በማድረግ በድጋሚ ለጥፈነዋል፡፡ | ሄኖክ ስዩም በድሬ ቲዩብ

ዛሬ የትም ቅርብ ነው፡፡ ሩቅ ነኝ ብሎ የሚቀር የለም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናን ጽዮን ለደጅሽ አብቂኝ ብለው የተመኙትን ያገኙ አክሱም ገብተዋል፡፡

ታሪካዊቷ ከተማ በየዓመቱ በዚህ ወቅት ድባቧ ይለያል፡፡ ጥንታዊ መንደሮቿ የሰው አጀብ አይለያቸውም፡፡ የአክሱም እናት ለማታውቀው ልጇ ለምትቀበለው እንግዳዋ ደፋ ቀና ስትል ከርማለች፡፡

ከእናቷ ያየችው ባህል ነው፡፡ እናቷ ደግሞ ከአያቷ፡፡ ወደ ከተማዋ የሚያስገቡት በሮች ላይ ደንኳኖች ተጥለዋል፡፡ የእንግዳ ማረፊያዎች ናቸው፡፡ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ አክሱም የሚገቡ እንግዶች እግር ይታጠባል፡፡ እዚህ ቋንቋ መደማመጥ የግድ አይደለም፡፡

ወንድሙን የሚጠብቅ እንደ አብርሃም እንግዳን የናፈቀ ልብ ከየት መጣህ? ብሎ ሳይጠይቅ ሰው እግር ስር ወድቆ እግር ያጥባል፡፡ ይሄ የአክሱም ወግ ሆኗል፡፡

ትናንት ረፋዱ ላይ ቅዱስ ፓትረያሪኩና ብጹአን አባቶች አክሱም ጽዮን ሲደርሱ እንደ ታሪካዊ ስፍራዋ ዘመን ያስቆጠ እሴት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ትናንት ቀኑን ሙሉ መኪኖች ከየአቅጣጫው ገብተዋል፡፡ እንግዳው ቁጥር የለውም፡፡ እየዘመረ ወጥቶ እየዘመረ የሚገባው ጽዮንን ሳይጠግብ ወደመጣበት ይመለሳል፡፡

የገዳም አባቶች ከየገዳማቸው መጥተው ሰላም ለኪ ለማለት የኪሎ ሜትሩ ብዛትና የእግር መንገዱ ድካም ፈተና አይሆንባቸውም፡፡
ዛሬ ህዳር 21 ነው፡፡ ጽዮን ተከባለች፡፡ ረዣዥም ሐውልቶች በየዓመቱ ቁልቁል ነጠላ የለበሰውን ህዝብ ሲመለከቱ ኖረዋል፡፡

የአክሱም ሊቃውንትን ቃለ እግዚሐር አድምጠዋል፡፡ ሙራደ ቃል በምስጋና ዜማ ከነ ልምላሜው ብዙ መቶ ዓመታትን የኖረ ዋርካ ነው፡፡ የዋርካዋ ከተማ ሞገስ፡፡

እናቶች እልልታቸውን እያሰሙ ከምድር በታች ሌላ ከተማ ናት ተብላ የምትገመተውን አክሱም የአመት የምስጋና ስንቋን ይቸሯታል፡፡

የውጪ ጎብኚዎች የአነበቡትን ፍለጋ የሰሙትን እውነትነት ለማረጋገጥ ካሜራቸውን ወልውለው ከዋዜማው ጀምሮ የማትጠገዋ ጥንታዊት ከተማ ላይ እታች ይላሉ፡፡

ዛሬም እንደ ዋዜማው እንደ ትናንቱ ነው፡፡ ትናንት ከዋዜማው ቅዳሴ በኋላ፡፡ ከቅዳሴ የወጣውን ምዕመን ቤቴ ካልወሰድኩ የሚል የአክሱም ደግ ልብ ደግሶ አብልቶ ነበር፡፡

የአክሱም ሰው አሁንም ቅዳሴው እስኪያልቅ ይጠብቃል፡፡ እንግዶቹን ቤቱ ሊወስድ፤ ቤት ያፈራውን ሊጋብዝ፡፡ ዛሬ ብዙ ቀን ነው፡፡
ታቦተ ጽዮን ዛሬ ዳጎንን የቀጠቀጠችበት ቀን ነው፡፡

በ349 ዓ.ም. የአብረሐ ወ አጽበሐ ባለ አስራ ሁለት ምሰሶ በወርቅ የተለበጠ ቤተ ክርስቲያን የተመረቀበት ቀን ነበር፡፡

ዛሬ በአንበሳ ውድም በ822 ዓ.ም. በዝዋይ ከቆየችበት ወደ አክሱም የተመለሰችበት ቀን ነው፡፡ አንድ ቀን ብዙ መታሰቢያ፤ አንድ ስፍራ የሚሊዮኖች ልብ የሚሻት፤ የአክሱም ጎዳናዎች ሰው ብቻ ናቸው፡፡

ወደ ጽዮን ደጃፍ ለመድረስ የሚጣደፍ፤ የጽዮንን ደጃፍ ረግጦ ዳግም ዓመት ርቆበት የሚመለስ፡፡

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close