Connect with us

Business

ያኔ ቦሌዎች ምነው ሠፈራችን ጨርቆስ በኾነ ይላሉ!

Published

on

ያኔ ቦሌዎች ምነው ሠፈራችን ጨርቆስ በኾነ ይላሉ! | ከሄኖክ ስዩም

ያኔ ቦሌዎች ምነው ሠፈራችን ጨርቆስ በኾነ ይላሉ! ያኔ አዲስ አበባ የጨርቆስን እድሜ ከዛሬዋ ጋር በሰጠኝ ትላለች፡፡ ያኔ አብሮ መኖር የሚችሉት ጨርቆሶች አብሮ ማደግ እንዴት እንደኾነ ያሳያሉ፡፡ *** ሄኖክ ስዩም በድሬቲዩብ

የባቡሩ ድምጽ ጠፍቶ ነበር፡፡ የደመቀውን መንደር ያፈዘዘው ማን ነው? አራተኛ ስለኢትዮጵያ የተመከረበት ስፍራ አልነበረም? ታቦቱን ብሎ ስለቱን ያልከተተ የጨርቆስ ወዳጅ ማን ነበር? ታዲያ ጨርቆስ የድህነት ምልክት ኾና አንድ ሥርዓትን ስለምን ኖረች?

ጨርቆስ አሁን ሌላ ዘመን መጥቶላታል፡፡ የባቡሩ ድምጽ ቢጠፋም የብስራት ድምጽ አስተጋብቶባታል፡፡ ያ ድምጽ ድፍን አዲስ አበቤን ጮቤ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ማን ያውቃል? ይኼ ድምጽ ተክለሃይማኖት ይሰማ ይኾናል፤ ቄራ ይደመጥ ይኾናል፤ ልደታን ያዳርስ ይኾን ይኾናል፤ የአራት ኪሎን እንባ በአማኑኤል መሳለሚያ ክሶ ሌላ ዘመን ያመጣ ይኾናል፡፡

ጨርቆስ የአዲስ አበባ ወካይ ስፍራ ናት፡፡ የዛሬን አያድርገው ለገሃር አየናት ብለን ከጥላሁን ገሠሠ ጋር አብረን የዞርንባት ከተማ ናት፡፡

ድንቅ የከተማ ተረክ ከጨርቆስ ተፈጥሮ አዲስ አበቤን በሀሴት አሳብዷል፡፡ ብዙ መጽሐፍ ጨርቆስ ባይኖር ጭብጡ ምን ይኾን ነበር? ፊልሞቻችንስ? አሁን ጨርቆስ ታላቅ ስፍራ ትኾናለች፡፡ ያኔ ቦሌ ወዮ ለኔ ስትል አደምጣለሁ፡፡

ጨርቆስ ዱባይ ኾና ስናይ የቦሌ ቅንጡ ህንጻዎች አንሰው ጥፍራችን ውስጥ ይገባሉ፡፡ ድህነት በስፍራው ይሸነፋል፡፡ ማጣት ቦታ ባልለቀቀ ህዝብ ድል ይነሳል፡፡ ጨርቆስ ነኝ ማለት ቅንጡነት ይኾናል፡፡ ጨርቆስ ነኝ እንላለን፤ አዲስ አበባም ብትኾን አድራሻሽ ስትባል ጨርቆስ የምትልበት ቀን ሩቅ አይኾንም፡፡

ከጨርቆስ የኢትዮጵያ የንዋይ ማዕከላት ቅርብና ትይዩ ናቸው፡፡ የመድን ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤቶች ፊታቸውን ወደ ጨርቆስ ያዞሩት ለትንቢት ነበር? ብለን እንጠይቃለን፡፡

የንብ ባንክ ግዙፍ ሕንፃ፣ የንግድ ባንክ ተንጠራርቶ ማየት፣ የብሔራዊ ባንኩ ማሻቀብ፣ የዘመን ፊት ለፊት ማፍጠጥ የአዋሽ ባንክ መሽኮርመም፣ የወጋገን ትከሻ መስጠት ቀድሞውኑ ስለ ጨርቆስ ብሩሕ ቀን አስበው ይኾን? የለገሃር ስሟ በማይጠፋ ቀለም ይጻፋል፡፡

የንጉሠ ነገሥታችን አሻራ በድንቅና ውብ ከተማ ማካከል ህያው ኾኖ የመጣውን ያናግራል፡፡ የማያረጀው ባቡር በልጅነቱ እንደተቀጨ የሚያጋልጠው እውነት ከጨርቆስ ሰማይ ላይ ድምጹ በቀረ ድባብ ነግሶ ይኖራል፡፡

ቸርችል ማዶ ቆመን ቁልቁል ስናይ ከዚህ በኋላ ቁጭት ደረቱን ገልብጦ አይፈታተነንም፡፡ ይመጣል ስንለው ስለ ቀረ ባቡር ህመም የሚጠዘጥዘን ስሜት ፍቱን መድሃኒት ያገኘ መስሎኛል፡፡ እውነት ያድርገው፤ ያየነውን መሬት አርፎ መሬት ቆመን ለመመስከር ያብቃን፡፡

ሃምሳ ቢሊዮን ብር ሃምሳ ቢሊዮን ተስፋ ይዞ መጥቷል፡፡ ያኔ አዲስ አበባ አድራሻዋ ጨርቆስ ይኾናል፡፡ እድሜ ደግ ነው፡፡ መሠንበት መልካም መኾኑን የሚመስክሩ ቱሩፋቶች እናይ ይኾናል፡፡ ከሽሮ ሜዳ እስከ በሰቃ እናይ ይኾናል፡፡ ከካራቆሬ እስከ ካራአሎ እናይ ይኾናል፡፡ ከአባዶ እስከ አሽዋ ሜዳ እንዲህ ላለው ተአምር ሜዳ ኾነው ጉድ ያስብሉን ይኾናል፡፡ ኢትዮጵያ ኾይ ትንሳኤሽን ያሳየን፡፡

** የቪዲዮ ዘገባዎችና መዝናኛዎችን ለማግኘት www.diretube.com ይጉብኙ
** ኢትዮጵያን የተመለከቱ የተለያዩ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ዜናዎችን ለእንግሊዘኛ ለማንበብ www.ethio.news ይጉብኙ

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close