Connect with us

Ethiopia

ሃያ ቢሊዮኑን ብር ያያችሁ!

Published

on

ሃያ ቢሊዮኑን ብር ያያችሁ! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን 

ሃያ ቢሊዮኑን ብር ያያችሁ! | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሃጽዮን

ሀገሪቱ ሥራ አቁማለች፡፡ ከሚከፈቱ ፋብሪካዎች የሚዘጉት እየበለጡ ነው፡፡ ከሚሠራው ከተሜ ፌስቡክ ላይ ተጥዶ ሰበር ዜና የሚጠብቀው ይበልጣል፡፡ የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት አንገላትተውት ለተቃውሞ አደባባይ የወጣው ሕዝብ ዛሬም ፊቱን ወደ ሥራ አላዞረም፡፡ ሥራ ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔዎችና ሥራዎች ጸጉር ለመንጨትና ለመደሰት ቤተመንግሥቱን በዓይነ-ኅሊናው ሲቃኝ የሚውል ሕዝብ በዝቷል፡፡ ፖለቲከኛ ማህበረሰብ አሻቅቦ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አሀዙ አሽቆልቁሏል፡፡

በነዚህ መሀል ምክንያትና ውጤት አይጠየቅም፡፡ ወሬው ‹ታሰረ እና ይታሰር› የሚል ብቻ ይመስላል፡፡ እየሆኑ ያሉ እና ሊሆኑ የሚገባቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች የትደረሱ ብለን አንጠይቅም፡፡ 70 በመቶው የሀገሪቱ ሕዝብ የሚጠይቀው የሀብት ማፍራትና የሥራ ዕድል አጀንዳ ምላሽ ያገኘ ይመስል ቄሱም ዝም መጽሐፉም ዝም ብሏል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ፓርላማ 10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ መመደቡ ይታወሳል፡፡ ይህንን በጀት ክልሎችም ጨምረውበት ዳብሯል፡፡ እናም 20 ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ በተዘዋዋሪ ፈንድ ሰበብ በመላ ሀገሪቱ ተረጭቷል፡፡

ይህ ገንዘብ አሁን የት እንዳለ እንጃ! መንግሥትም፣ ወጣቶቹም ይህንን ጉዳይ ሲያነሱት አይታዩም፡፡ የመንግሥት ሹመኞችን ኪስ እያደለበ ነው ወይስ፣ እንደታቀደው ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ነው…ሥራችንና እድላችን መጠየቅ ብቻ ነው፡፡

ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ በዚህ አብዮት ይሁን ለውጥ፣ ማሻሻያ ይሁን ነውጥ ባልተለየ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ የተረጨው 20 ቢሊዮን ብር ላለመዘረፉ ምን ዋስትና አለ?!

ይህንን ጉዳይ በበላይነት የሚመራው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ወደ ኮሚሽን ማነሱ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ ባለቤት አልባ ያደርገዋል፡፡ የሥራ ዕድል ፈጠራን ለመምራት የተቋቋሙ መንግሥታዊ ኤጀንሲዎችም አንዳንዶቹ ኃላፊ ሳይሾምባቸው ተንሳፍፈዋል፡፡

በአመጽ አስተዳደርንና አስተዳዳሪን የቀየሩ ወጣቶች የተሰጣቸውን (ተሰጥቷቸው ከሆነ) ገንዘብ ምን አደረጉት?

በአንዳንድ ወረዳዎችና ዞኖች የመንግሥት መዋቅር ፈርሷል፡፡ በተለይ በምዕራብና ሰሜን ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ ያሉ ወረዳዎችና ዞኖች መንግሥትን አባርረው ካስወጡ ዓመት አልፏቸዋል፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ደግሞ የታችኛው የመንግሥት መዋቅርና ወጣቱ ተናንቋል፡፡በተለይ በምዕራብ አማራ ክልል ባሉ ከተሞች በቃፍ የተያዘ ጸጥታ ነው ያለው፡፡ አፋርና ሱማሌ፣ ደቡብና እነ ጋምቤላም ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡

ታዲያ በቢሊዮን አሀዝ የተረጨ ገንዘብ በትክክል ለልማት መዋሉንም ሆነ አለመዋሉን የሚከታተለው ማነው? የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርም ይህን የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በብዛት መድቧል፡፡ ይሁን እንጂ አዲሱ ከንቲባ በዘላቂነት የወጣቶችን የሀብት ችግር ይፈታል የተባለው ይህ ገንዘብ ለምን እየዋለ እንደሆነ ነግረውን አያውቁም፡፡

ጥያቄውም የ20 ቢሊዮን ብራችንን እናት ያያችሁ የሚል ነው!!

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close