Connect with us

Ethiopia

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ሜቴክ

Published

on

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ሜቴክ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሀፅዮን

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና ሜቴክ | በኃይሉ ሚዴቅሳ ፍስሀፅዮን

ሜቴክ ይፋዊ ዝርፊያ ጀምሯል የተባለው ከ2004 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ መሆኑን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ዘመን ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያረፉበትና፣ አቶ ኃይለማርያም ወደ መሪነት የመጡበት ጊዜ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ደግሞ ቀጥተኛ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው፡፡ ሜቴክን በቦርድ ሰብሳቢነት ይመሩት የነበሩት ደግሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ናቸው፡፡

አስገራሚው ነገርም ይህ ነው፡፡ የሀገሪቱ አንደኛና ሁለተኛ ሰዎች በቀጥታ የሚቆጣጠሩት ተቋም በዚህ ደረጃ ተንኮታኩቶ ሲታይ እነዚህ ሰዎች የትነበሩ ያስብላል፡፡ ሀገሪቱ የፕሮጀክት ማናጅመንት ቀውስ ውስጥ በወደቀችባቸው ባለፉት ዓመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምና ምክትላቸው ምንም ነግረውን አያውቅም፡፡ ኦዲት ተደርጎ የማያውቅ፣ ሕገወጥ ግዥ ሲፈጽም፣ ሚኒስትሮችን ሲሰድብና ሲያስፈራራ ወዘተ እነዚህ ሰዎች የትነበሩ፡፡

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በተደጋጋሚ የሚሏት አንድ ነገር ነበረች፡፡ ‹‹ሕዝብን ማገልገል መሰጠት ነው›› የምትል፡፡ ሕዝብን ማገልገል ማለት ሌባንና ዘራፊን ቅጣት እንዲያገኝና ልጓም እንዲበጅለት ማድረግ አይደለምን፣ ታዲያ የዚህ ድርጊት ልጓምና፣ የመቅጪያ ሕግስ ከአቶ ኃይለማርያምና ምክትላቸው ውጭ ማን እጅ ነበረ?

አቶ ኃይለማርያም የለውጥ አካል ለመሆን ሥልጣኔን ለቀቅሁ ካሉ በኋላ፣ ምንም ወንጀል የሌለባቸው ሐገር ወዳድ ተብለው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ተወደስው፣ አንገት ሙሉ ወርቅ ተሸልመው ተሸኙ፡፡ አቶ ደመቀም ከቦርድ ሰብሳቢነት እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት አሁንም ሥልጣን ላይ ናቸው፡፡

ትናንት ሜቴክን ከፔትሮብራስ ጋር አነፃፅሬ በፃፍሁት ጽሁፍ ላይ እንዳሳየሁት፣ ማይክል ቲመር እነ ሉላ ዳሲልቫን ሲያስር ከፔትሮብራስ ገንዘብ ወስደዋል ብሎ አይደለም፡፡ ይህ ፕሮጀክት ሲከስር መንግሥታዊ ኃላፊነታችሁን ተጠቅማችሁ አላዳናችሁትም ብሎ እንጂ፡፡

አቶ ኃይለማርያም ግን ሥራ ላይ ሳይሆን ጸሎት ላይ እንደከረሙ በቴሌቭዥን እየመጡ እየነገሩን ነው፡፡

አኬልዳማ ቁጥር ሁለትን አየሁት!

ከሚሊኒየም ወዲህ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን እንደ ዶክመንተሪ ደጋግመው የሰሩት ሥራ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ብቻ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ብዙ ፖለቲካ እና ፖለቲከኞችን የተመለከቱ ሥራዎች በዘጋቢ ፊልም ቀርበዋል፡፡ ጂሃዳዊ ሀረካት፣ አኬልዳማ፣ አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ ወዘተ የሚሉትን የሃይስኩልም የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆነን አይተናል፡፡

አብዛኞቹ ዶክመንተሪዎች ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ፡፡ ከሁሉም ግን አኬልዳማን መርሳት የለብንም፡፡

እስክንድር ነጋ፣ አንዷለም አራጌ…ወዘተ የተባሉ ፖለቲከኞች ገና በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ፣ ክስ እንኳ ሳይመሰረትባቸው ነበር አኬልዳማ የቀረበው፡፡ አኬልዳማ የደም መሬት ነው፡፡ እነዚህን ከእስኪብርቶ በላይ የጨበጡት ነገር የሌላቸው ፖለቲከኞች ባንክና ታንክ ላለው መንግሥት ሥጋት ናቸው ተብሎ አገርን የደም መሬት ሊያደርጉ ነበር ተባለ፡፡

እዚህ ጋር ልብ ሊባለው የሚገባው ነገር አለ፡፡ መንግሥት ይህንን ሲያደርግ ሰዎቹን ፍርድ ቤት አልበየነባቸውም፡፡ በመጨረሻም አንድነት ፓርቲ ይህ ዶክመንተሪ ስም ማጥፋት ነው ብሎ ከሰሰ፡፡ ፍርድቤትም አዎ ስም ማጥፋት ነው አለ፡፡ ቴሌቭዥኑም ይቅርታ እንዲጠይቅ ታዘዘ፡፡

በፍርድቤት ጥፋተኛ ያልተባለን ሰው ወንጀለኛ ብሎ መፈረጅ፣ በሚዲያ ሕግም ሆነ በሌሎች ሕጎች ያስጠይቃል፡፡ ምክንያቱም በፍርድ ሂደቱ ላይ ተጽእኖ ያሳርፋል ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ የትናንቱ ዶክመንተሪም ምናባዊው ወዘተ ከሚባል አኬልዳማ ቁጥር ሁለት ቢባል ይሻላል፡፡

በይዘት ካልሆነ በስተቀር በአቀራረብም ሆነ በአፈራረጅ (በቅርጽ) ልዩነት የለውም፡፡ ገና ለገናው ሕዝብ ብንነግረው ከመደነቅ አልፎ ምንም አይለንም ተብሎ ከሆነ ያስተዛዝባል፡፡ ተፈጽሟል የተባለው ወንጀል፣ ከአሁን በፊት በተለየዩ መንገዶች ሲወራና ሲራገብ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጉዳዩ ከሕዝብ የተሰወረ ላለመሆኑ ቢያንስ ፓርላማው እማኝ ነው፡፡ በተደጋጋሚ ፓርላማው ይህንን ጉዳይ ሲናገር ነበር፡፡ የሜቴክ አመራሮችም አንዳንዴ አምነው ‹‹መሰዋት ካለብኝ ልሰዋ›› እያሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በምንም አታመጡም መንፈስ ሲከራከሩ ነበር፡፡ እናም ጉዳዩ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የትናንቱ ዶክመንተሪ የነገረን አዲስ ነገር የለም፡፡

ይህንን ዘጋቢ ፊልም ከአኬልዳማ ጋር የሚያመሳስለው በፍርድቤት ጥፋተኛ ያልተባሉ ሰዎችን ስምና ድርጅቶች ወንጀለኛ ሲል ማምሸቱ ነው፡፡ ይህ እስከዛሬ ከነበሩት አሰራሮች የቀጠለ ክፉ ድርጊት ነው፡፡ ‹‹የጠሉትን ለመምታት ዘጋቢ ፊልም መሥራት›› የሚል ብሒል ቀጥሏል፡፡

(ከአዘጋጁ፡- ይህ ጹሑፍ የጸሐፊውን እንጂ የድሬቲዩብን ኤዲቶሪል አቋም አያንጸባርቅም)

Trending

By continuing to use the site, you agree to the use of cookies. more information

The cookie settings on this website are set to "allow cookies" to give you the best browsing experience possible. If you continue to use this website without changing your cookie settings or you click "Accept" below then you are consenting to this.

Close